1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአሸባቡ ጦር መሪ ግድያ እና አሚሶም

ማክሰኞ፣ ጥር 20 2006

የኬሚካል ባለሙያ የሆነው እና የኣጥፍቶ ማጥፋት ጥቃቶችን በባቀድ እና በማቀነባበር የሚታወቀው ኣህመድ መሓመድ ኣሜ እስኩ ዱቅ በሚል መጠሪያው ይበልጥ ይታወቃል። ካለፈው ኣንድ ዓመት ወዲህ በተለይ በሞቃዲሾ እና በተለያዩ አካባቢዎች ከተሰነዘሩ የኣጥፍቶ መጥፋት ጥቃቶች በስተጀርባ መኖሩ የሚነገርለት ኣሜ

https://p.dw.com/p/1AyWX
Karte Somalia mit Puntland

የተገለው ከትላንት በስተያ እሁድ ነበር፣ ደቡብ ሶማሊያ ውስጥ፤ በታችኛው ሸበሌ ክ/ሀገር፣ በረዌ በተባለችው የጠረፍ ከተማ አካባቢ። ስፍራው ባለፈው ጥቅምት ወር የአሜሪካ ኮማንዶዊች እክሪሚ የተባለውን የአልሸባብ የጦር ኣዛዥ ለመግደል ያልተሳካ ሙከራ ያደረጉበት አካባቢ ሲሆን ኣሜ በመኪና እየተጉዋዘ ሳለ ነበር ከኣሜሪካ ኃይሎች ተተኮሰ ሚሳዔል የተመታው። ሚሳዔሎቹ የተተኮሱት ከሰው ኣልባ ኣውሮፕላኖች (ድሮኖች) መሆኑን የአሜሪካ ወታደራዊ ባለሥልጣናትተናግረዋል።

ኣሜ የአልሸባቡ መሪ የኣህመድ አብዲ ጎዳኔ የቅርብ ኣማካሪም እንደሆነ ይነገርለታል። ይበልጥ የጎዳኔ ቀኝ እጅ እየሆነ የመጣው ደግሞ ባለፈው ዓመት ሌላኛው የኣጥፍቶ መጥፋት ጥቃቶች መሀንዲስ አል አፍጋኒ መገደሊን ተከትሎ ሲሆን ከኣል ኣፍጋኒ ይልቅ ኣሜ ለጎዳኔ በጎሳ ትስስር ጭምር ይበልጥ ታማኝም ነበር ተብሏል። ሁለቱም ከድር ጎሳ ናቸውና።

Mogadishu Flugzeugabsturz
ምስል Reuters

የሶማሊያው መንግስት ባለስልጣናት የመረጃ ሰራተኞችን እና የዓይን እማኞችን በመጥቀስ ኣህመድ መሐመድ ኣሜ መገደሉን ይግለጹ እንጂ፣ ከኣልሸባብ ወገን የተገኘ ማረጋገጫ ግን የለም። የUS አሜሪካ ባለስልጣናትም ቢሆኑ የሚሳዔሎቹ ዒላማ ውጤት እየተጣራ ነው ከማለት ያለፈ ያረጋገጡት ነገር ባለመኖሩ ግድያውን የሚጠራጠሩ ወገኖችም ኣልታጡም። ከደቡብ ኣፍሪካ የዓለም ዓቀፉ የቀውስ ኣስወጋጅ ተቐም ባልደረባ የሆኑት ሚ/ር አንድሩስ አታ አሳማዋ ግን እርግጠኛ ነኝ ይላሉ።

«በእርግጥ ሞቷል። ግን እስከ ኣሁን አልሸባብም ያለው ነገር ባለመኖሩ እና አሜሪካም ይህንኑ ባለማረጋገጧ ኣስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። የሶማሊያ መንግስት የመረጃ ሰራተኞች ብቻ ናቸው ግለሰቡ መገደሉን የሚናገሩት። ነገር ግን ምንም እንኩዋን አልሸባብ ባያምንም ትላንትና ኃይላቸው በበረዌ አካባቢ ይተራመስ ነበርና ይህንኑ ኪሳራ የሚያመለክት ነው የሚሆነው።»

የአልሸባብ መሪዎችን ለመግደል ስልታዊ እቅድ ኣውጥታ የምትንቀሳቀሰው አሜሪካ ይህ ተሳካላት ማለት ይላሉ ሚ/ር አሳማዋ ቀጣዩ ጽዋ የማን እንደሆነ ስለማይታወቅ በአልሸባብ ኣመራሮች ውስጥ ትልቅ ውጥረት ይፈጥራል። ኣሜን ለመግደል አሜሪካኖቹ መረጃውን እንዴት እና ከማን እንዳገኙ ለማጣራትም በቡድኑ ውስጥ ከሚፈጠረው ጥርጣሬ በተጨማሪም የአካባቢውንም ህብረተሰብ እያተራመሱ ይበልጥ ያርቁታል። ሚ/ር አሳማዋ እንደሚሉት ታዲያ ይህ ለአሜሪካኖቹም ሆነ ለሶማሊያው መንግስት መልካም ኣጋጣሚ ነው።

በተያያዘ ዜና ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ በሶማሊያ ያለው የኢትዮጵያ ጦር በዚያች ኣገር ከሚገኘው የኣፍሪቃ ህብረት የሰላም ተልዕኮ ሰራዊት ( AMSOM) ጋር መቀላቀሉ ይታወሳል። አልሸባብ ይህንኑ በመቃወም ኣጥብቆ መዛቱ ሲታወቅ የህብረተሰቡ ኣመለካከት ግን ሚ/ር አሳማዋ እንደሚሉት ከሁለት የተከፈለ ነው ።

Somalia Äthiopien äthiopische Soldaten auf dem Weg zu Mogadishu
ምስል PETER DELARUE/AFP/Getty Images

«እንደ ኣጠቃላይ ግንዛቤ ለዓመታት የሶማሊያ ህዝብ ኣመለካከት ከሁለት የተከፈለ ሆኗል። የኢትዮጵያ ኃይሎችን ሁሉም ኣይደሉም የሚደግፉት። ዘላቂውን የሶማሊያ መረጋጋት ኣስመልክቶ የኢትዮጵያ ኃይሎችን ለመቀበል ስጋት ያላቸው ወገኖች ኣሉ። ሆኖም ግን እስከ ኣሁን የተገኘው መሻሻል መቀጠል ኣለበት ብለው የሚያምኑ እና ይህንኑ የሚደግፉ ወገኖችም በእርግጥ ኣሉ። ምክኒያቱም ይህ ካልሆነ አልሸባብ በደካማው የሶማሊያ መንግሥት ላይ በቀላሉ የበላይነትን ሊይዝ ይችላልና።»

ባሳለፍነው ሳምንት የተቀላቀሉትን 4000 የኢትዮጵያ ወታደሮችን ጨምሮ አሚሶም ኣሁን የተሻለ ኃይል ይኖረዋል ተብሎ ይታመናል። እናም ይበልጥ ተቀናጅቶ ኣልሸባብን ማጥቃት እና የተቆጣጠራቸውን አካባቢዎችም መጠበቅ ይቻለዋል ተብሎ ይገመታል። አልሸባብ በኣሁኑ ጊዜ የቀውስ ኣስወጋጅ ተቐም መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በጥቅሉ 5000 ያህል መደበኛ ታጣቂዎች ኣሉት። ሚ/ር አሳማዋ እንደሚሉት በእርግጥ የታጣቂዎቹ ቁጥር ሳይሆን የሚጠቀምበት የጥቃት ስልቱ ነው ወሳኙ። ከሁሉም በላይ ግን ከእንግዲህ የሶማሊያው ቀውስ ይላሉ አሳማዋ በኣልሸባብ ድክመት ሳይሆን በሶማሊያው መንግስት ጥንካሬ ነው መለካት ያለበት።

ጃፈር ዓሊ

ኂሩት መለሰ