1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአሸባሪዎች ጥቃት በፓሪስ

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 30 2007

ፈረንሣይ መዲና ፓሪስ ውስጥ «ቻርሊ ኤብቶ» በተሰኘው፥ ምፀታዊ ምስሎችን በሚያወጣ ሣምንታዊ መፅሔት ዋና ጽ/ቤት ላይ በተጣለ ጥቃት 12 ሰዎች ተገደሉ። ፈረንሳይ ዛሬ የሃዘን ቀን አዉጃለች። በርካታ ተጠርጣሪዎችም እየተያዙ ነዉ።

https://p.dw.com/p/1EGXX
Frankreich Terror Presse Anschlag auf Charlie Hebdo in Paris
ምስል Reuters/J. Naegelen

ከሟቾቹ መኻከል ሁለት ፖሊሶች እንደሚገኙበት የጀርመን ዜና አገልግሎት ዘግቧል። ሌሎች 7 ሰዎች የቆሰሉ ሲሆን አራቱ ለሕይወታቸው በሚያሰጋ መልኩ በፅኑዕ መጎዳታቸውም ታውቋል። የግድያ ጥቃቱ በተሰነዘረበት ወቅት ከባድ ጦር መሣሪያዎችን የታጠቁ ቢያንስ ሁለት ሰዎች ጽ/ቤቱ ውስጥ መገኘታቸው ተጠቅሷል። የፈረንሣይ ፕሬዚዳንት ፍራንሷ ኦሎንድ የተኩስ ጥቃቱ «የሽብር ጥቃት ለመሆኑ ጥርጥር የለውም» ብለዋል። «በርካታ የሽብር ጥቃቶች ባለፉት ሣምንታት መክሸፋቸውንም» ፕሬዚዳንቱ አክለው ተናግረዋል። በጀርመን የሚታተመው ታይታኒክ የተሰኘው ምፀታዊ መጽሔት ዋና አዘጋጅ የሆኑት ቲም ቮልፍ በፈረንሣይ የደረሰው ጥቃት ጀርመን ውስጥ እሳቸውን እና የሥራ ባልደረቦቻቸውን እንደማያሰጋ ተናግረዋል።

«በፍፁም፤ ይህ ነው የተባለ ምንም አይነት ዛቻ አልደረሰብንም፤ ስለዚህም ምንም ከፍተኛ ጥበቃ አላስፈለገም»

ጥቃቱን ተከትሎ የፈረንሣይ መንግሥት ከፍተኛውን ደረጃ «የሽብር ማስጠንቀቂያ» ማወጁን ይፋ አድርጓል። የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ለፈረንሣዩ ፕሬዚዳንት ፍራንሷ ኦሎንድ የቴሌግራም መልእክት አስተላልፈዋል። በመልእክታቸውም፦ጥቃቱ በፈረንሣይ የውስጥ ደኅንነት ላይ የተቃጣ ብቻ ሳይሆን ሀሳብን በነፃ የመግለጽ መብት፣ የፕሬስ ነፃነት እና የዲሞክራሲ ባህል ላይ የተሰነዘረ ነው ብለዋል። ጥቃት የተሰነዘረበት መፅሔት እስልምናን ጨምሮ በጳጳሳት እና በፕሬዚዳንቶች ላይ ምፀታዊ ምስሎችን የሚያወጣ እንደሆነ ይነገራል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ