1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በባህር ዳር ከታሰሩት የዩኒቨርስቲ መምህራን እና ጋዜጠኞች ይገኙበታል

ሰኞ፣ መጋቢት 17 2010

በአማራ ክልል ባህር ዳር ከተማ ባለፈው ቅዳሜ በቁጥጥር ስር የዋሉ 19 ሰዎች “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ድንጋጌ በመጣስ በጋራ ተንቀሳቅሳችኋል” በሚል እንደተያዙ ተነገረ፡፡ በፖሊስ ጣቢያ በእስር ላይ ከሚገኙት ሰዎች መካከል አምስት የዩኒቨርስቲ መምህራን፣ ሁለት ጋዜጠኞች እንደሚገኙበት በቅርብ የሚያውቋቸው ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል፡፡

https://p.dw.com/p/2v1wj
Äthiopien Ausnahmezustand
ምስል James Jeffrey

በባህር ዳር ከታሰሩት የዩኒቨርስቲ መምህራን እና ጋዜጠኞች ይገኙበታል

በባህርዳር ከተማ “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጥሳችሁ በጋራ ተንቀሳቅሳችኋል” በሚል  ከትላንት በስቲያ ቅዳሜ በቁጥጥር ስር የዋሉ 19 ሰዎች እስከ ዛሬ ፍርድ ቤት አለማቅረባቸውን እና ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝ እስረኞቹን የጎበኟቸው ግለሰቦች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡ ከታሳሪዎቹ ውስጥ አብዛኞቹ አዲስ ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ ለመቋቋም በእንቅስቃሴ ላይ የነበሩ ናቸው ተብሏል፡፡

በቁጥጥር ስር የዋሉትን ግለሰቦች በትላንትናው ዕለት የጎበኙት የባህርዳር ዩኒቨርስቲ መምህር አቶ ጌትነት አልማው ከታሳሪዎቹ  የሰሙትን እንዲህ አካፍለዋል፡፡ “የእራት ፕሮግራም ነበራቸው፡፡ ከዚያ በኋላ ጣና ያለበትን ወቅታዊ ሁኔታ ለማየት በሚል ወደ ጣና ጉዞ አድርገው ነበር፡፡ በእምቦጭ ላይ ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት እና የባህር ዳር ዩኒቨርስቲው መምህር  ዶ/ር ደሳለኝ [ጫኔም] አሉ፡፡ አይተው ሲመለሱ ከጀልባ ሲወርዱ እንደያዟቸው ነው የነገሩኝ፡፡ ከታያዙ በኋላ ትላንት በአካል ሄደን አይተናቸዋል፡፡ ባህር ዳር ላይ ዘጠነኛ ፖሊስ ጣቢያ ነው ያሉት፡፡ እነ አቶ ጋሻው [መርሻ]፣ እነ በለጠ [ሞላ] አሉ፡፡ ቁጥራቸው በትክክል 19 ነን ነዉ ያሉኝ፡፡ እንዲሁ ያለጥፋታቸው እንደታሰሩ ነው የነገሩን እና እንደተያዙም እንደተደበደቡ መረጃ ሰጥተውናል” ብለዋል። 

Äthiopien Ausnahmezustand
ምስል James Jeffrey

በባህርዳር በእስር ላይ ከሚገኙት ውስጥ ከባህርዳር ዩኒቨርስቲው ከዶ/ር ደሳለኝ ሌላ አራት ተጨማሪ የዩኒቨርስቲ መምህራን እንደሚገኙበት በቅርበት የሚያውቋቸው ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል፡፡ ከታሳሪዎቹ ውስጥ በአማራ መገናኛ ብዙሃን ድርጅት ውስጥ በአርታኢነት የሚያገለግለው ንጋቱ አስረስ እና የቀለም ቀንድ ጋዜጣ አዘጋጅ የነበረው በለጠ ካሳም እንደሚገኙበት ጠቁመዋል፡፡ የፕሮፌሰር አስራት ወልደየስን ታሪክ የሚያትተውን “አንጸባራቂው ኮከብ” የተሰኘውን መጽሐፍ የጻፈው መምህር ጋሻው መርሻም ከተያዙት መካከል አንዱ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ 

አስራ ዘጠኙ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ያዋላቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈጸም የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት እንደሆነ የሚናገሩት የቅርብ ሰዎቻቸው ለመታሰራቸው በምክንያትነት የቀረበላቸው “በጋራ ተንቀሳቅሳችኋል” የሚል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ አቶ ጌትነትም ተመሳሳይ ምክንያት ከእስረኞቹ መስማታቸውን ይናገራሉ፡፡ በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት የመቅረባቸው ጉዳይም አጠራጣሪ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡  

“አሁን ካለው ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር በጋራ መንቀሳቀስ አይቻልም እና ይህንን በጋራ ተንቀሳቅሷችኋል የሚል [ምክንያት] ተሰጥቶናል አሉን፡፡ ምክንያት ብቻ እንጂ ክስ እንዳልቀረበባቸው [ነው የነገሩን]፡፡ እንግዲህ አሁን ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር በ48 ሰዓት ውስጥ ይቀርባሉ የሚለውም መታየት ነው የሚኖርበት፡፡ የመደበኛ ሂደቱስ በትክክል ይኖራል ወይ? በትክክልስ ይተገበራል ወይ? የሚለው መታየት ያለበት ይመስለኛል” ሲሉ አስተያየታቸውን ጨምረው ሰጥተዋል። 

እስረኞቹን ዛሬ በፖሊስ ጣቢያ የጎበኟቸው የቅርብ ሰዎቻቸው እስካሁን ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡ ባለፈው የካቲት ወር አጋማሽ ይፋ የተደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ  የተከለከሉ ተግባራትን በዘረዘረበት ክፍሉ ላይ “በጋራ መንቀሳቀስ” የሚለው መከልከሉን በግልጽ አያስቀምጥም፡፡ ሆኖም ያልተፈቀዱ ሰልፍ እና የአደባባይ ስብሰባዎችን ይከለክላል፡፡ 

ከጋዜጠኛ ንጋቱ አስረስ ውጭ የታሰሩት ግለሰቦች አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ ለመመስረት እንቅስቃሴ ማድረጋቸዉን የአዲሱ ፓርቲ ምስረታ አመቻች ኮሚቴ አባል አቶ ክርስቲያን ታደለ ይናገራሉ፡፡ እንቅስቃሴያቸውን በህጋዊ መንገድ ከጀመሩ አራት ወር እንዳለፋቸው የሚያስረዱት የኮሚቴው አባል ግለሰቦቹ በታሰሩበት ዕለት ተሰባስበው እራት እየበሉ ከመካከር ውጭ ስብሰባ አለማካሄዳቸውን ይገልጻሉ፡፡  

12.06.2013 DW Online Karten Basis Äthiopien Englisch

“የሄዱበት ዋና ዓላማ እውነቱን ለመናገር ስብሰባም አልነበረም፡፡ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ስብሰባዎች ሲካሄዱ አስቀድሞ ማሳወቅ የሚጠየቅ ስለሆነ ለመስራች ጉባኤ የሚያስፈልጉ አንዳንድ ቅድመ ዝግጅቶችን ለማካሄድ፣ ምን ያህል ሰው ነው መገኘት ያለበት? የት ነው ስብሰባው የሚካሄደው? እንዴት ማካሄድ አለብን የሚሉትን ጨምሮ አንዳንድ ነገሮችን ህጉ በሚፈቅደው መንገድ ለመሄድ እንደቤተሰብ ተሰባስበው በሚመካከሩበት ወቅት ነው አጋጣሚ ሆኖ የታሰሩት እና እጅግ የሚያሳዝን ነው፡፡ እኛ ምን ማድረግ እንዳለብን ግራ እንስክንጋባ፣ ሰላማዊነት ወንጀል ነው እንስክንል ድረስ ነው፡፡ ህግን ማክበር ምንድነው ደንብ ከመተላለፍ ተቆጠረ ወይ? የእኛን ምርጫ ቦርድ ያውቃል፣ በየደረጃው ያሉ የመንግስት አካላትም ያውቃሉ እና ምን አዲስ ነገር እንደተገኘ አላውቅም”  ብለዋል አቶ ክርስቲያን።   

የመስራች ጉባኤውን ለማካሄድ በሂደት ላይ የሚገኘው አዲሱ ፓርቲ የአማራን ክልል መሰረት አድርጎ የሚንቀሳቀስ ነው ተብሏል፡፡ በምስረታ ላይ ያለው ፓርቲያቸው ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አባላትን የሚመዝግቡበት ፎርም መቀበሉን የሚናገሩት አቶ ክርስቲያን እስካሁን ወደ አንድ ሺህ አባላት ገደማ መመዝገባቸውን ተናግረዋል፡፡ በቁጥጥር ስር ሥለዋሉት የፓርቲው መስራቾች ጉዳይ የተጠየቁት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ተስፋለም አባይ ጉዳዩን አስመልክቶ አቤቱታ ያቀረበ አካል እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ መመስረት የዜጎች “ህገ መንግስታዊ መብት ነው” ብለዋል፡፡ 

“ማንኛውም ዜጋ የፖለቲካ ፓርቲ እመሰርታለሁ ቢል ፎርማት ለማወቅ ነው ከእኛ የሚወስደው እንጂ ከዚያ በኋላ የመስራች አባላት አሰባስቦ፣ ጠቅላላ ጉባኤ አካሄዶ፣ አመራር አስመርጦ በሙሉ ሲያመጣ ቦርዱ ያየዋል፡፡ በዚህ ሂደት ላይ ያጋጠመ ችግር ካለ ቦርዱ ያየዋል፡፡ ስለዚህ እኛ ጋር ‘እንደዚህ ሆነን፣ ታስረን’ የሚል የደረሰ ነገር የለም” ሲሉ አቶ ተስፋለም አስረድተዋል። 

የአማራ ክልል የመንግስት ኮሚዩኔኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ጸጋዬ በቀለ ጉዳዩን ገና ለማጣራት እየሞከሩ እንደሆነ እና በቂ መረጃ እንዳላገኙ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡ የባህር ዳር ፖሊስ አዛዥን ለማግኘት በተደጋጋሚ ብንደዉልም ምላሽ አላገኘንም፡፡  

ተስፋለም ወልደየስ

ነጋሽ መሐመድ