1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአራት አመት ነጻነት፤ ጦርነትና ስደት-ደቡብ ሱዳን

ረቡዕ፣ ሐምሌ 1 2007

ደቡብ ሱዳን ከአስራ ስምንት ወራት በላይ በዘለቀ የርስ በርስ ጦርነት ተዘፍቃለች። ከተሞቿ ፈራርሰዋል። መንደሮች ተቃጥለዋል። በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች መርጃ ከፍተኛ ኮሚሽነር (UNHCR) መሰረት 2.25 ሚሊዮን ደቡብ ሱዳናውያን በአገራቸው ተፈናቅለዋል። አሊያም ድንበር አቋርጠው ስደተኛ ሆነዋል።

https://p.dw.com/p/1FvH6
Äthiopien Flüchtlinge aus Südsudan
ምስል Getty Images/AFP/Z. Abubeker

[No title]


በዚህ ውስጥም የዛሬዋ የደቡብ ሱዳን ሪፐብሊክ ከሰሜን ሱዳን ነጻ የወጣችበትን አራተኛ አመት ልታከብር ዝግጅት ላይ ነች።

የቀድሞ የትግል አጋሮች ፤የደቡብ ሱዳን መስራቾችና የቀድሞ የፖለቲካ ጓዶች፤ የዛሬ ባላንጦች ፕሬዛዳንት ሳልቫ ኪር እና ሪየክ ማቻር የአገሪቱን የነጻነት ቀን ሐምሌ 2/2007 የሚያከብሩት ኩርፊያቸው ሳይበርድ የአስራ ስምንት ወራቱ የርስ በርስ ጦርነት ሳይሰክን ይሆናል።የሁለቱ ሰዎች አለመግባባት እና ጦር መማዘዝ ከ2.25 ሚሊዮን በላይ ደቡብ ሱዳናውያን ህይወት ማመሳቀሉን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን የአፍሪካ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ካሪን ደ ግሩይል ይናገራሉ።
«ደቡብ ሱዳን ከ2, ሚሊዮን 225 ሺ በላይ ሰዎች በማያባራ ግጭት ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው የነጻነት በዓሏን ለማክበር ተዘጋጅታለች። 730,000 ሰዎች አገራቸውን ጥለው ተሰደዋል።ብዙዎቹ የደቡብ ሱዳን አጎራባች ወደ ሆኑት ኢትዮጵያ፤ኬንያና ኡጋንዳ የተሰደዱ ናቸው። 1.5 ሚሊዮን ዜጎች ደግሞ በዚያው በአገራቸው ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው በደቡብ ሱዳን የድንበር አካባቢዎች ይገኛሉ።»
ምዕራባውያን አገራትም ይሁኑ ዓለም አቀፍ ተቋማት የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኞችን ከመተቸት ባለፈ ወደ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ምስቅልቅል የምትምዘገዘገውን አገር ለማዳን የወሰዱት ሁነኛ እርምጃ የለም። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከዚሕ ቀደም የአውሮጳ ህብረትና አሜሪካ የጉዞና የሃብት ማዕቀብ በጣሉባቸው ስድስት የጦር መሪዎች ላይ ድጋሚ ማዕቀብ ጥሏል። ማዕቀቡም ይሁን በአዲስ አበባ ለወራት የዘለቀው የድርድር ሂደት እንስቶችን ከመደፈር ልጆችን ከግዳጅ ውትድርና አልታደጋቸውም። ካሪን ደ ግሩይል ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው በዚያው በደቡብ ሱዳን የሚገኙ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ኑሮ ፈታኝ መሆኑን ይናገራሉ።
«ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው በደቡብ ሱዳን የሚገኙ ዜጎችን መርዳት ከፍተኛ ፈተና ሆኖብናል።ከፍተኛ የሆነ የአቅርቦት ችግር አለ።ደቡብ ሱዳን አዲስ አገር ነች። መሰረተ ልማት የላትም። ብዙዎቹ እርዳታ ፈላጊ ተፈናቃዮች የሚገኙት ደግሞ በገጠራማ አካባቢዎች ነው። የተወሰኑት ደግሞ ጥበቃ በሚያገኙበት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መጠለያ ጣቢያዎች ይገኛሉ። የደህንነቱ ሁኔታ በጣም ፈተና ነው።»
አሁን በስልጣን ላይ የሚገኘው የፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ፓርቲ የአገሪቱን የነጻነት በዓል ለማክበር ሽር ጉድ ላይ መሆኑ ተሰምቷል። ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት አለበት የተባለው መንግስት የገንዘብ ኖቶችን ከኢኮኖሚው አቅም በላይ በማተም ወደ ገበያ አስገብቷል የሚል ትችትም ይሰነዘራል። የአገሪቱ ኢኮኖሚ ዋንኛ የገቢ ምንጭ የነበረው የነዳጅ ምርትም ቢሆን በርስ በርሱ ጦርነት ጫና ውስጥ መውደቁን የዓለም ባንክ አስታውቋል። ካሪን ደ ግሩይል እና ተቋማቸው የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን መፍትሄ ያጣው ቀውስ አሁንም ዜጎችን ለስደት መዳረጉን ይቀጥላል የሚል ስጋት ገብቷቸዋል።
«እንደ አለመታደል ሆኖ ግጭቱን ለመፍታት የሚደረገው ጥረት ሲመክን ተመልክተናል።የሰብዓዊ ቀውሱም አስከፊ እየሆነ ነው። አሁንም የመኖሪያ ቀያቸውን ጥለው ወደ ጎረቤት አገሮች የሚሰደዱ ደቡብ ሱዳናውያን ቁጥር እየጨመረ ነው። በመጪዎቹ ጊዜያትም ይህ ቁጥር ይጨምራል የሚል ስጋት አለን። ከፍተኛ ቁጥር ያለው ስደተኛ ለመቀበልም ራሳችንን እያዘጋጀን ነው።በኢትዮጵያና በኬንያ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎችን እያዘጋጀን ነው።
በደካማ ኢኮኖሚ፤ስራ አጥነት እና የኑሮ ውድነት ውስጥ የምትዋዥቀው ደቡብ ሱዳን ለአስራ ስምንት ወራት ለዘለቀው ጦርነት መፍትሄ መፍጠር ተስኗታል።ነገ-የሚከበረዉ የነጻነት ዉጤትም ለብዙዎች ከንቱ ነዉ።
እሸቴ በቀለ
ነጋሽ መሐመድ

Rebellen ethnische Massaker in Südsudan
ምስል AFP/Getty Images
Südsudan Waffenstillstand 01.02.2014 Addis Abeba
ምስል Reuters/T. Negeri