1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ እጩዎች የዉጪ መርሕና ማንነት

ሰኞ፣ ጥቅምት 19 2005

ማን፥ ምንም አለ ምን፥አሜሪካ አለምን ትመራለች እንጂ አለምን የምትመራዉን ሐገር መሪ የሚመርጠዉ አሜሪካዊ ያዉም መምረጥ የሚችለዉ ሁለት መቶ አርባ ሚሊዮኑ ሕዝብ ብቻ ነዉ።

https://p.dw.com/p/16Z8Z
Republican presidential candidate, former Massachusetts Gov. Mitt Romney and President Barack Obama walks past each other on stage at the end of the last debate at Lynn University, Monday, Oct. 22, 2012, in Boca Raton, Fla. (Foto:Pablo Martinez Monsivais/AP/dapd)
ማን ይሆን?ምስል AP


29 10 12


አሜሪካኖች ትናንትና ዛሬ ምናልባትም ነገ ከተፈጥሮ ቁጣ ጋር ይታገላሉ።በመጪዉ ሳምንት የነገን ዕለት ደግሞ የአራት ዓመት መሪያቸዉን ይመርጣሉ።ድምፅ የሚሰጠዉ 240 ሚሊዮን ሕዝብ ነዉ።ሥልጣኑን የሚይዘዉ አንድ ሰዉ።ያ አንድ ሰዉ በአራት ዓመታት ዉስጥ የሚያደርግ፥ የሚያቅድ የሚወስነዉ የድፍን ዓለምን አብዛኛ ፖለቲካዊ፥ምጣኔ ሐብታዊ እዉነት፥ሒደትንም መዘወሩ  ሐቅ ነዉ።የዚያችን የዓለም መሪ ሐገር፥የመሪነት ሥልጣን ለመያዝ ሁለት ጠንካሮች እየተፎካከሩ ነዉ።ኦባማና ሮምኒ።ተመራጩ ዓለምን የመዘወሩ ሐቅ ምክንያታችን፥ የምርጫ ዘመቻቸዉ ሒደት መነሻ፥ የሁለቱ ጠንካሮች ማንነትና የዉጪ መርሕ መድረሻችን ነዉ ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።

ባለፈዉ መስከረም ማብቂያ ቬኑዙዌላ ዉስጥ በተደረገዉ ምርጫ ለአራተኛ ዘመነ-ሥልጣን ያሸነፉት የሐገሪቱ ፕሬዝዳት ሁጎ ራፋኤል ሻቬዝ በምርጫ ዘመቻቸዉ መሐል «አሜሪካዊ ብሆን ኖሮ የምመርጠዉ ኦባማን ነበር» አሉ።ከአራት ዓመት በፊት የያኔዉን የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ዳብሊዉ ቡሽን በሰይጣን መስለዉ፥ ቡሽ የቆሙበትን ሥፍራ ድኝ፥ ድኝ ይሸታል ያሉት ሻቬዝ ለዋሽግተን መሪዎች «የአፍንጫ ስር መዥገር» አይነት ናቸዉ።አክራሪ ኮሚንስት።

ፕሬዝዳት ኦባማም ለኮሚንስቶቹ ከብዙዎቹ የአሜሪካ መሪዎች ብዙ የተለየ አቋም አላቸዉ ማለት ያሳስታል።ያም ሆኖ የደቡብ አሜሪካ ኮሚንስቶች አባት የሚባሉት አንጋፋዉ የኩባ መሪ ፊደል ካስትሮ ወይም ሥልጣናቸዉን የወረሱት ታናሽ ወንድማቸዉ ራዑል ካስትሮ ቢጠየቁ ኦባማን እንደሚደግፉ መገመት አያሳስትም።

የዩናይትድ ስቴትስ የዉጪ በጣሙን የንግድ ግንኙነት ከቻይና ይልቅ ደቡብ አሜሪካ ላይ ማተኮር አለበት ያሉት ግን ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ አይደሉም።የሪፐብሊካኑ እጩ ተቀናቃኛቸዉ አገረ-ገዢ ሚት ሮምኒ እንጂ።
             
«ንግዳችንን እናሳድጋለን።ንግዱ በየዓመቱ በአስራ-ሁለት ከመቶ ያድጋል።በየአምስት አመቱ ደግሞ በእጥፍ ያድጋል።ከዚሕ የተሻለ ማድረግ እንችላለን።በተለይ ከደቡብ አሜሪካ ጋር።ደቡብ አሜሪካ ለኛ ያለዉን ምቹ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ አልተጠቀምንበትም።እንደ እዉነቱ ከሆነ የደቡብ አሜሪካ ምጣኔ ሐብት ከቻይና ምንም አይተናነስም።ቻይና ላይ ብቻ ነዉ ያተኮር ነዉ።»
              
እርግጥ ነዉ ሮምኒ፥ የፕሬዝዳት ባራክ ኦባማን የንግድ መርሕ ከቻይና ጋር «አለቅጥ የተጣበቀ ነዉ» እያሉ በተደጋጋሚ መተቸታቸዉን አጣትለዉታል።በተለይ ቱጃሩ ፖለቲከኛ እንደ ነጋዴ ኩባንዮቻቸዉን ቻይና እና ከቻይና ጋር እያሰሩ፥ እንደ እጩ ፕሬዝዳት አሜሪካ ከቻይና ጋር ያላትን ግንኙነትን መቀነስ አለባት ማለታቸዉ ለፕሬዝዳት ኦባማ የመልስ ምት ጥሩ ዱላ ብጤ ነዉ-የሆነዉ።
                  
«አገረ ገዢ ሮምኒ በቻይና አንፃር ጠንካራ መሆን አለብን ሲሉ፥ ቻይና ዉስጥ በግንባር ቀደምትነት በሚሰሩ ኩባንዮች ላይ መወረታቸዉን እንዳትዘነጉት።በአሁኑ ጊዜ እንኳን ለቻይና የቃኚ መሳሪያዎችን በሚያመርቱ ኩባንዮች ላይ ገንዘባቸዉን እያፈሰሱ ነዉ።አገረ-ገዢ ሆይ! በቻይና ላይ ጠንካራ መሆን አለብን ለማለት የመጨረሻዉ ሰዉ በሆኑ ነበር።»

የቻይና የምጣኔ ሐብት፥ የቴክኖሎጂ፥ የዲፕሎማሲና የወታደራዊ ጡንጫ ፈጣን እድገት ያቺን የቢሊዮኖች ሐገር ወደፊት የት እንደሚያደርሳት ከመላምት ባለፍ አሁን በትክክል መተንበይ አይቻልም።በቀዝቃዛዉ ጦርነት ወቅት አሜሪካ፥ እና ሶቬት ሕብረትን ቀርቶ ጃፓንና ምዕራብ አዉሮጶችን በሩቅ ርቀት ታማትር የነበረችዉ ቻይና አሁን በብዙዉ መስክ ብዙዎቹን ቀድማለች።ዩናይትድ ስቴትስን ግን አሁንም ገና እየተከተለች ነዉ።

ሮምኒ ከቻይና ጋር እየነገዱ፥ ቻይና ላይ ጠንከር፥ ጨከን ማለት አለብን የማለታቸዉ ሚስጥር ምናልባት የቤጂንጎችን ሁለንታናዊ ሩጪ መግታት ይገባናል ማለት ሊሆን ይችላል።
              
«ቻይና ሸሪካችን ልትሆን ትችላለች።ይሕ ማለት ግን እኛ ላይ እንዳሻቸዉ ይፈንጩ፥ ሥራችንን ያለ አግባብ ይስረቁን ማለት አይደለም።»

በዚሕም ይሁን በሌላ ምክንያት የቻይናዉ ፕሬዝዳት ሁ ጂንታኦ እንደ ሁጎ ሻቬዝ ቢጠየቁ እንደ ዲፕሎማሲዉ ወግ ካለበሉ በስተቀር ከሻቬዝ የተለየ መልስ የሚጠብቅ የለም።ለነገሩ ሁ እራሳቸዉ ሥልጣን ለማስረከብ የአስር ዓመት ፕሬዝዳንታዊ ጠረጴዛቸዉን እየወለወሉ ነዉ።

የአሜሪካኖቹ ፕሬዝዳንታዊ እጩዎች የዩናይትድ ስቴትስ ቀንደኛ ጠላት ሥለሚባሉት ሥለ ኢራን እና ሥለ ሶሪያ መንግሥታት የሚከተሉት መርሕ ተመሳሳይ ነዉ።ኢራን፥-ፕሬዝዳት ኦባማ ከሰወስት ዓመት በላይ ያሉትን ደገሙት።«እኔ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት እስከ ሆንኩ ድረስ ኢራን የኑክሌር ጦር መሳሪያ ሊኖራት አይችልም።»

ሮምኒ ደግሞ ሥልጣን ከያዙ ኦባማ በዘመነ-ሥልጣናቸዉ ያደረጉትን ወደፊት እንደሚያደርጉት ቀጠሉ።«ሥለ ኢራን ያለን ተልዕኮ ምን እንደሆነ መገንዘብ በጣም ጠቃሚ ነዉ፥ ይሕ ደግሞ ኢራን የኑክሌር ጦር መሳሪያ እንዳይኖራት በሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ መከልከል ነዉ።»

እንደ ቻይና፥ እንደ አሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ሁሉ ዘንድሮ ዘመነ-ሥልጣናቸዉ የሚያበቃዉ የኢራኑ ፕሬዝዳት ማሕሙድ አሕመዲኒጃድ ወይም ጠንካራዉ ክርናቸዉ በአሜሪካና በተባባሪዎችዋ መንግሥታት በሚደገፉት አማፂያን ዉጊያ የዛለዉ የሶሪያዉ ፕሬዝዳንት በሽር ሐፊዝ አል-አሰድ እንደ ሻቬዝ ቢጠየቁ የሚመልሱትን መገመት ከባድ ነዉ።

የኦባማም ሆነ፥ የሮምኒ አቋም ግን ለሁለቱ የአሜሪካ ቀንደኛ ጠላቶች «ያዉ በገሌ» የሚያሰኝ አይነት ነዉ።«ያደረግነዉ ምንድነዉ፥-አሳድ መወገድ አለባቸዉ በማለት ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብን አስተባበርን። በዚያ መንግሥት ላይ ማዕቀብ እንዲጣል አስተባብረናል።እንዲነጠሉ አድርገናል።ሰብአዊ ርዳታ ሰጥተናል።ተቃዋሚዎቹ እንዲደራጁ እየረዳን ነዉ።በተለይ ፍላጎታችን ሶሪያ ዉስጥ ያሉ ለዘብተኞች መደራጀታቸዉን ማረጋገጥ ነዉ።»

                  
ሮምኒ፥-«ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት እንዲኖር አንፈልግም።ከወታደራዊ ግጭት መዘፈቅ አንፈልግም።የጦር መሳሪያዎቻቸዉ ከማይሆኑ ወገኖች እጅ እንዳይገባ ማረጋገጥ አለብን።እነዚሕ መሳሪያዎች ኋላ እኛን ለመጉዳት ሊዉሉ ይችላሉ።----»

እያሉ ፕሬዝዳት ኦባማን ለመተካት የሚፎካከሩት የሪፐብሊካኖቹ እጩ ኦባማ እስካሁን ያሉ፥ ያደረጉትን እንደሚደግሙት አረጋገጡ።የፍልስጤሞቹን የዘመን-ዘመናት የነፃነት ትግል፥ምኞት ገቢር ለማድረግ ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ ሥልጣን በያዙ ሰሞን ብዙ ብለዉ፥ ጥቂት ሞክረዉ ነበር።ያደረጉት ግን ምንም የለም።

ፕሬዝዳት ማሕሙድ አባስ ከሁለቱ እጩዎች የሚደግፉትን ቢጠየቁ-ምርጫቸዉን በትክክል ማወቅ ይከብድ ይሆናል።በልማዱ፥ እስራኤል እንደ ሐገር ከተመሰረተች ጀምሮ የተፈራረቁት የአሜሪካ መሪዎች ከተጨባጩ እዉነት፥ ከገጠጠዉ ሐቅ፥ ምናልባት ከራሳቸዉም ዉስጣዊ ፖለቲካዊ እምነት ይልቅ ብዙ የሚያስጨንቃናቸዉ ሥልጣን የሚይዙበት፥ ወይም የያዙትን ሥልጣን እንደያዙ የሚቀጥሉበት ሥልት ነዉ።

ብዙዎቹ መሪዎች እስራኤል ያደረገችዉን ሁሉ ብታደረግ ከእስራኤል ጎን መቆማቸዉን የሚገልጡት፥ የፍልስጤሞችን ይሁን የሌሎች ሕዝቦችን የመብት ጥያቄ የሚደፈልቁት፥ ወይም ሸንግለዉ የሚያልፉት ከጠንካራዉ እና ከሐብታሙ የአሜሪካ አይሁድ ማሕበረሰብ የሚደርባቸዉን ቅጣት ጠንቅቀዉ ሥለሚያዉቁት ነዉ።

አነሰም በዛ በእስራኤልን ላይ ጠንከር ያለ አቋም የሚይዙት ወይም ማብቂያ የሌለዉ የፍልስጤሞችና የእስራኤል ድርድር እንዲቀጥል እስራኤሎችን ለመገሰፅ አቅም የሚያገኙት በሁለተኛ ዘመነ-ሥልጣናቸዉ ወቅት ነዉ።ምክንያት፥- ለሰወስተኛ ዘመነ-ሥልጣን ስለማይወዳደሩ ያን በድምፁ፥ በሐብቱ፥በሚቆጣጠረዉ መገናኛ ዘዴ፥ ወይም በደጋፊዎቹ አማካይነት የሚቀጣቸዉን ማሕበረሰብ አይፈሩትምና።

በዚሕ ምክንያት ወይም ከማያቁት «መላዕክ----»አይነት ሆኖ፥ አባስ ምናልባት ከሮምኒ ይልቅ ኦባማን ይደግፉ ይሆናል።ሁለቱን እጩዎች ብዙ ያሳሰበ፥ ብዙ ያናገረዉ ግን አሜሪካ ለእስራኤል የምትሰጠዉ ድጋፍ እንጂ የፍልስጤሞች የዘመነ-ዘመናት የነፃነት ጥያቄ፥ የሰብአዊነት ክብር ከቁብ የሚገባ አይደለም።
                 
«እስራኤል እዉነተኛ ጓደኛችን ናት።በአካባቢዉ ታላቅዋ ተባባሪያችን ናት።እስራኤል ከተጠቃች አሜሪካ ከእስራኤል ጎን ትሰለፋለች።ይሕን በፕሬዝዳትነት ዘመነ-ሥልጣኔ በሙሉ ግልፅ አድርጌያለሁ።»
               
ሮምኒም ሌላ አላሉም።«የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳት ስሆን ከእስራኤል ጋር እንቆማለን።እስራኤል ከተጠቃች ደግሞ ድጋፋችንን ያገኛሉ።ዲፕሎማሲያዊ፥ ባሕላዊ ድጋፍ ብቻ አይደለም።ወታደራዊም ጭምር እንጂ።»

እስራኤል ዘመን የማይሽራት የአሜሪካ ልዩ ወዳጅ ናት።የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እንደ ሻቬዝ ቢጠየቁ ማንን ይሉ ይሆን? የኦባማንና የኔታንያሁን የእስካሁን ግንኙነት የሚያዉቅ፥-መልሱን ለማወቅ ሁለቴ ማሰብ አያሻዉም።ማን፥ ምንም አለ ምን፥አሜሪካ አለምን ትመራለች እንጂ አለምን የምትመራዉን ሐገር መሪ የሚመርጠዉ አሜሪካዊ ያዉም መምረጥ የሚችለዉ ሁለት መቶ አርባ ሚሊዮኑ ሕዝብ ብቻ ነዉ።

የሕዝቡን ፖለቲካዊ ትርታ የሚከታተሉት የአሜሪካ መገናኛ ዘዴዎች የእስካሁን ዘገባ ግን አገረ-ገዢ ሮምኒን ሳያናድድ አልቀረም።«አርዕስተ ዜናዎች፥- ኦባማ በኮርን ፍሌክስ ተከበዋል፥ ሮምኒ የሚበሉት ከሐብታሞች ጋር ነዉ»

እዉነቱ ግን ከዚሕ ብዙም የራቀ አይደለም።ሁለቱ የአንድ ሐገር ዜግነት፥ የፖለቲካ ዝንባሌ፥ አቀራረባቸዉ እንጂ የተቃራኒ ቤተ-ተሰብ፥ የተራራቀ መደብ፥ የሩቅ ለሩቅ ዘመን ዉጤቶች ናቸዉ።ትንሹ፥ ክልሱ ባራክ ሁሴይን ኦባማ በ1962 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎሮጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር ነዉ) ለአንድ ዓመት ልደቱ አንድ ሻሚ ሊበራለት ቀናት ሲሰላለት፥ የአስራ-ስድስት አመቱ ጎረምሳ ፖለቲካን አንድ-ሁለት ማለት ጀመረ።የአዉቶሞቢል ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ አባቱ ለሚችጋን  አስተዳዳሪነት ሲወዳደሩ ዘመቻዉን ያስተባብር ነበር።ዊላርድ ሚት ሮምኒ።

በዚያ ዘመቻ አባቱ አሸነፉ።ሐርቫርድ ዩኒቨርስቲ ለመግባት ሐብቱም፥ችሎታዉም አላነሰዉም።ፖለቲካን ለጊዜዉ ገሸሽ አድርጎ ሞርሞን የተሰኘዉ ሐይማኖታዊ ሐራጥቃ አስተምሕሮትን እንዳጠበቀ በ1975 በሕግ የዶክትሬት፥ በንግድ አስተዳደር ደግሞ ማስተርስ ዲግሪ ይዞ በሁለት ዲግሪ ተመረቀ።

ከኬንያዊዉ ጥቁር አባት የተወለደዉ፥ ያለ አባት ያደገዉ ወጣት የቱጃሩ ልጅ ከገባበት ዩኒቨርስቲ ለመግባት፥ ሐብት ንብረቱ የእናቱ ፅናት፥ የአያቶቹ ድጋፍ፥ የራሱ ጥረት፥ ብቻ ነበር።ግን ገባ።ልክ እንደ ሮምኒ ግን ከሮምኒ በተሻለ ዉጤት በሕግ በዶክተርነት ተመረቀ።1991።

ከእንግዲሕ ሁለቱም አንቱ ናቸዉ።ሮምኒ ከዩኒቨርስቲ እንደ ወጡ ንግዱን ተቀላቅለዉ በሚሊዮን እና ሚሊዮን ዶላር ሲያሰሉ።ወጣቱ ኦባማ የዩኒቨርስቲ አስተማሪ ሆኑ።

ሮምኒ ዳግም ወደ ፖለቲካዉ የዞሩት በ1994 ነበር።ለምክር ቤት እንደራሴነት ተወዳድረዉ ተሸነፉ።በስድስተኛዉ አመት ኦባማ ልክ እንደ ሮምኒ ለምክር ቤት እንደራሴነት ተወዳድረዉ ልክ እንደ ሮምኒ ተሸነፉ።ሮምኒ ሽንፈታቸዉን ለስምንት ዓመት ያሕል አስታመዉ ለማሳቹሴትስ አገረ-ገዢነት ተወዳድሩ።አሸነፉ።ሁለት ሺሕ ሁለት።በሁለተኛዉ አመት ኦባማ ለሴናተርነት ተወዳድረዉ አሸነፉ።ሁለት ሺሕ አራት።በአራተኛዉ ዓመት በተደረገዉ ምርጫ የዲሞክራቲኩ ፓርቲ ወክለዉ  አርባ-አራተኛዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳት ሆኑ።
               
«ለእረጅም ጊዜ ያንቀላፋሁት በመጀሪያዉ ክርክር ወቅት ነበር።»

አሉ በቀደም።ብዙ ባልተመቸ እድገት፥ ሥራ፥ ትምሕርት ኑሯቸዉ መሐል ብዙ ቢያንቀላፉ ኖሮ-ብዙ ላንቀላፉበት ዕለትና ሥፍራ ባልደረሱ ነበር።ኦባማ ከአራት አመት በፊት ያሉትን ያክል በርግጥ አልሰሩም።የወደፊቲም ከኦባማ ወይስ ከሮምኒ ላሁኑ አለየም።የአሜሪካ ሕዝብ ሳምንት ማክሰኞ እስኪወስን ዓለም መጠበቅ አለበት።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ
ሒሩት መለሰ


 

Bilder für eine Reportage zur US-Präsidentschafts-Debatte. Alle Bilder habe ich heute geschossen (Rechte liegen bei der Deutschen Welle). Zulieferer: Hilke Fischer. "Public Viewing der zweiten TV-Debatte von Obama und Romney im Restaurant 'Busboys and Poets' in Washington D.C."
መራጩምስል DW
U.S. Republican presidential nominee Mitt Romney (L) and U.S. President Barack Obama gesture towards each other during the second U.S. presidential debate in Hempstead, New York, October 16, 2012. REUTERS/Mike Segar (UNITED STATES - Tags: POLITICS ELECTIONS USA PRESIDENTIAL ELECTION TPX IMAGES OF THE DAY)
ፍጥጫምስል Reuters
President Barack Obama, left, hugs his wife Michelle while Republican presidential nominee Mitt Romney kisses his wife Ann following the third presidential debate at Lynn University, Monday, Oct. 22, 2012, in Boca Raton, Fla. (Foto:David Goldman/AP/dapd)
ከየባለቤቶቻቸዉ ጋርምስል AP