1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአማራ ክልል ግጭትና ዉዝግቡ

ረቡዕ፣ ጥር 17 2015

"በተፈጸመው ድንገተኛ ጥቃት፣ከመቶ በላይ የሚሆኑ የዐማራ ልዩ ኀይል ተዋጊዎች እንደተገደሉ መረጃዎች ደርሰውናል።እንግዲህ እዚያ አካባቢ ተመሳሳይ ጥቃት ሲሰነዘር ቢያንስ እኔ እንኳን የማስታውሰው፣ለሰባተኛ ጊዜ ነው።በተደጋጋሚ አካባቢው ጥቃት ይደርስበታል።

https://p.dw.com/p/4MgOQ
Äthiopien | Binnenvertriebene aus der Oromia Region in Debre Birhan
ምስል North Shewa Zone communication Office

«በጥቃቱ ከ100 በላይ የአማራ ልዩ ኃይል ባልደረቦች ተገድለዋል»የአማራ ማሕበር

በአማራ ክልል በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደርና በሰሜን ሸዋ ዞን አዋሳኝ ወረዳዎች ሰሞኑን የተቀሰቀሰዉ ግጭት በአንዳንድ አካባቢዎች ቀዝ ቀዝ ያለ ሲሆን በሌሎች ግን ዛሬም የተኩስ ድምፅ እንደሚሰማ ነዋሪዎች አስታዉቀዋል።ስለ ግጭቱ መነሻ፣ ሥለደረሰዉ ጉዳት መጠንና ተጠያቂ ስለሚባሉ ወገኖች የሚሰጠዉ አስተያየት ግን የተለያየ ነዉ።የዓማራ ክልላዊ መስተዳድር ጥቃት ያደረሱትን ወገኖች «ያልታወቁ ታጣቂዎች» ብሏቸዋል።መንበሩን ዩናይትድ ስቴትስ ያደረገዉ የሰሜን አሜሪካ የአማራ ባሕመበር በበኩሉ ጥቃት የከፈተዉ የኦሮሞ ነፃ አዉጪ ጦር ነዉ ይላል።ማሕበሩ «ድንገት ተከፈተ» ባለዉ ጥቃት ከ100 በላይ የአማራ ልዩ ኃይል ባልደረቦች ለመገደላቸዉ መረጃ አለኝ ባይ ነዉ።የኦሮሞ ነፃ አዉጪ ጦር ቃል አቀባይ ኦዳ ተርቢ ግን ለግጭቱ የአማራ ኃይልን ተጠያቂ አድርገዋል።

በሰሜን አሜሪካ የዐማራ ማኀበር እንዳስታወቀው፣ ግጭቱ የተጀመረው ጥር 13 ቀን 2015 ዓ.ም በዐማራ ልዩ ኀይል ካምፕ ላይ በኦሮሞ ነጻ አውጪ ሠራዊት ተፈጸመ ባለው ጥቃት ነው።በዚሁ ጥቃት የደረሰውን ጉዳት አስመልክቶ የማኀበሩ የአድቮኬሲ ዳይሬክተር አቶ ሆነ ማንደፍሮ፣ የሚከተለውን ለዶይቸለ ተናግረዋል።

"በተፈጸመው ድንገተኛ ጥቃት፣ከመቶ በላይ የሚሆኑ የዐማራ ልዩ ኀይል ተዋጊዎች እንደተገደሉ መረጃዎች ደርሰውናል።እንግዲህ እዚያ አካባቢ ተመሳሳይ ጥቃት ሲሰነዘር ቢያንስ እኔ እንኳን የማስታውሰው፣ለሰባተኛ ጊዜ ነው።በተደጋጋሚ አካባቢው ጥቃት ይደርስበታል።በአካባቢው በተደጋጋሚ ከተማዎች ይወድማሉ፣በርካታ ዜጎች ይፈናቀላሉ።በዚህም ከዚህ አካባቢ የተፈናቀሉና ከኦሮሚያ አካባቢ በኦነግ ሸኔ በተመራው ጥቃት የተፈናቀሉ ዐማራዎች፣በብዛት ደብረ ብርሃን አካባቢ ተጠልለው እንደሚገኙና በቅርቡም የመንግስት ኃላፊዎችምእንኳን ጓብኝተው ምክት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ሄደው ያዩበትን

ሁኔታ እናስታውሳለን።"

በሰሜን ሸዋ ዞን አጣየና አካባቢው፣ በኤፍራታና ግድም ወረዳ በጀውሃ ቀበሌ በሚገኘው የዐማራ ልዩ ኀይል ላይ በተፈጸመው በዚሁ ጥቃት፣ አምስት የፌዴራል ፖሊስ አባላትና ሁለት ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውንም ማኀበሩ ገልጿል።

የአርጡማ መንደር
የአርጡማ መንደርምስል Eric Lafforgue/imago images

ቢያንስ ዐስር የዐማራ ልዩ ኀይል አባላትና ዐስር የፌዴራል ፖሊስ አባላት በጽኑ ቆስለው ህክምና በመከታትተል ላይ እንደሚገኙ ተመልክቷል።የማኀበሩ የአድቮኬሲ ዳይሬክተር ከመረጃ ምንጮቻቸው ባረጋገጡት መሰረት፣ ከ250 ሺ በላይ ነዋሪዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል።"አሁን ባለው ሁኔታ ከሩብ ሚሊየን በላይ የሚሆን ህዝብ መፈናቀሉን እስከ ትናንት ድረስ ተረድተናል።በርካታ የሆኑ ዜጎች ተገድለዋል። ቁጥሩን እንዲህ ነው ብሎ ለመናገር የማያስችል ሁኔት ነው ያለው፤ምክንያቱም አሁንም ጥቃቱን እንደቀጠለ ነው።አስከሬን ማንሳት ያልተቻለበት ሁኔታ ስላለ ለመቁጠርም አዳጋች ሆኗል።"

ጥቃቱ በሰንበቴ፣ አላላ፣ አጣዬ፣ ሸዋሮቢት፣ ካራ፣ ጀባጀባ፣በባልቺ እና በዙሪያው በሚገኙ የሰሜን ሸዋ አካባቢዎች በንጹህ ዜጎችና በፀጥታ ኃይሎች ላይ በማነጣጠር ተስፋፍቶ መካሄዱን ለመረዳት ተችሏል።በጥቃቱ ለተፈናቀሉ ንጹሐን ዜጎች አስቸኳይ የሰብዓዊ ዕርዳታ ጥሪም ቀርቧል።"ጥቃቱ ተጠናክሮ በመቀጠሉ፣አሁንም አስቸኳይ የሆነ ሰብዓዊ ዕርዳታ ለተፈናቀሉት ወገኖች እንዲያደርሱ የሰብዓዊ ረድዔቶች ጥሪ እናቀርባለን።

እንደ የዐማራ ማኀበር በአሜሪካ፣የዚህ ጥቃት ከዳዌ ሐረዋ እስከ አጣዬ የዘለቀው ግጭትዓላማ፣ የፀጥታ ኀይሎቹ ከቦታው ለቀው እንዲወጡ በማድረግ ንጹሃን ዜጎችን ለመጨፍጨፍ ያለመ ነው።ስለጉዳዩ ዶይቸ ቨለ አስተያየት እንዲሰጡ የጠየቃቸው መንግስት "ኦነግ ሸኔ"በሚል የፈረጀው፣የኦሮሞ ነጻነት ስራዊት ቃልአቀባይ አቶ ኦዳ ተርቢ በሰጡት የጽሑፍ ምላሽ፣ለጥቃቱ የዐማራ ኃይሎችን ተጠያቂ አድርገዋል።በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደርና በሰሜን ሽዋ ዞኖች ግጭት አለ መባሉ

አቶ ኦዳ እንደሚሉት፣ የዐማራ ዐይሎች ጅሌ ድሙጋ በተባለ አካባቢ ከብቶቾ በሚያግዱ ኦሮሞዎች ላይ ተኩስ በመክፈት ጥቃት ፈጽመዋል።ይህም በኦሮሞ ገበሬዎችና በፀጥታ ኀይሎቹ መኻከል ከፍተኛ ወዳሉት የለየለት ግጭት ማደጉን ቃል አቀባዩ በሰጡን አጭር ምላሻቸው ገልጸው ዝርዝሩን ከመናገር ግን ተቆጥበዋል።አቶ ኦዳ ከዚህ ቀደም ቀደምም፣ የኦሮሞ እና ዐማራ ማኀበረሰቦችን ግንኙነት ለማበላሸት ሆን ተብሎ የሚፈጸሙ ናቸው ያሏዋቸውን ጥቃቶች ለማስቆም ውይይት እንዲካኼድ ጥሪ ማቅረባቸው አይዘነጋም።

ታሪኩ ኃይሉ

ነጋሽ መሐመድ

ታምራት ዲንሳ