1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአሐዱ ሁለት ጋዜጠኞች መታሰር

ረቡዕ፣ ጥቅምት 17 2014

አርብ ዕለት በደቡብ ወሎ ዞን የሚገኘው «ሐይቅ ከተማ በሕወሓት ታጣቂዎች ቁጥጥር ሥር ገብቷል» የሚል ዘገባ የሠራች ጋዜጠኛ እና በወቅቱ አርታዒ የነበረው የአሐዱ ራዲዮ 94.3 የዜና ክፍል ኃላፊ በወንጀል ተጠርጥረው በፖሊስ ታሰሩ።

https://p.dw.com/p/42G6D
Symbolbild Radiogerät, Stereoreceiver
ምስል picture-alliance/Klaus Ohlenschläger

አርብ ዕለት በደቡብ ወሎ ዞን የሚገኘው «ሐይቅ ከተማ በሕወሓት ታጣቂዎች ቁጥጥር ሥር ገብቷል» የሚል ዘገባ የሠራች ጋዜጠኛ እና በወቅቱ አርታዒ የነበረው የአሐዱ ራዲዮ 94.3 የዜና ክፍል ኃላፊ በወንጀል ተጠርጥረው በፖሊስ ታሰሩ። የኤፍ ኤም ሬድዮ ጣቢያው ለዘገባው ምንጭ የሆነው የመንግሥት የሥራ ኃላፊ ለዘጋቢዋ የሰጠው መረጃ የተሳሳተ መሆኑን ዜናው ከተላለፈ በኋላ ከከተማዋ ከንቲባ እና ከነዋሪዎች እንዳረጋገጠ አድማጮቹን ይቅርታ ጠይቆ እርምት ወስዶ እንደነበር የጣቢያው ዋና አዘጋጅ ሊድያ አበበ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ተጠርጣሪዎቹ ጋዜጠኞች ፍርድ ቤት ቀርበው ለምርመራ ቀጠሮ ተጠይቆባቸዋል። ፓሊስ ተጠርጣሪዎቹን ለምን እንደያዛቸው ለፍርድ ቤት ሲያስረዳ ሁለቱም ጋዜጠኞች ከዜናው መልዕክት ውጪ በሽብርተኛነት ከተፈረጀው ድርጅት ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ጠርጥሯቸው መሆኑን እንዳስረዳ ተገልጿል። የጣቢያው ጠበቃ ደግሞ የኤፍ ኤም ሬድዮ ጣቢያው የተሠራው ዘገባ ላይ እርምት መወሰዱ እንዳለ ሆኖ ጉዳዩ በፍትሃብሔር እንጅ በወንጀል የሚያስጠይቅ እንዳልነበር ተናግረዋል። ስለጉዳዩ ከመንግሥት አካላት በኩል መረጃ ለማግኘት የአዲስ አበባው ዘጋቢያችን ያደረገው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።

ሰለሞን ሙጬ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
እሸቴ በቀለ