1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአልበሽር ክስና የቀጠለዉ የንፁሃን ግድያ

ማክሰኞ፣ ግንቦት 6 2011

የቀድሞዉ የሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር አልበሽር በትናንትናዉ ዕለት አዲስ ክስ ተመሰረቶባቸዋል። አልበሽር ክስ የተመሰረተባቸዉ እሳቸዉን ከስልጣን ለማዉረድ  ለተቃዉሞ አደባባይ በወጡ ዜጎች ግድያ ነዉ።ያም ሆኖ ግን በሀገሪቱ ያለዉ ተቃዉሞ፣ ግድያና አለመረጋጋት አሁንም አልቆመም።

https://p.dw.com/p/3IUlc
Afrika | Protests im Sudan
ምስል picture-alliance/dpa/AA/M. Hjaj

የዓልበሽር ክሶችና የቀጠለዉ የንፁሃን ግድያ


ለ3 አስርተ ዓመታት ሱዳንን የመሩት ኦማር አልበሽር ለ4 ወራት በዘለቀ ተቃዉሞ ያለፈዉ ሚያዚያ ወር መንበረ ስልጣናቸዉን ቢያስረክቡም በስልጣን ዘመናቸዉ ፈፅመዋቸዋል በተባሉ ወንጀሎች የሚቀርብባቸዉ ክስና የሀገሪቱ አለመረጋጋት ግን አሁንም ቀጥሏል።
አልበሽር  በጎርጎሮሳዊዉ 2000 ዓ/ም በዳርፉር ግጭት በተፈፀመ የዘር ማጥፋትና በጦር  ወንጀል በዓለም ዓቀፉ  ፍርድቤት ፤ በህገ ወጥ የገንዘብ ዝዉዉርና ሽብርተኞችን በገንዘብ ይደግፋሉ በሚል በሀገራቸዉ ክስ ተመሰርቶባቸዋል። በትናንትናዉ ዕለት ደግሞ የሀገሪቱ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ  ፅ/ቤት ለተቃዉሞ አደባባይ በወጡ ዜጎች ግድያ ክስ መመስረቱን አስታዉቋል።DW ያነጋገራቸዉ ፖለቲካ ተንታኝ አቶ አበበ አይነቴ እንደሚሉት አልበሽር  በሰሩት ወንጀል መጠየቃቸዉ ተገቢ ቢሆንም የክሱ መደራረብ ግን የሚያሳየዉ አንድ ነገር አለ።
«የወደቀ ዛፍ ሆነዋል ፕሬዝዳንት አልበሽር።ከዚህ ቀደም በዳርፉር ጉዳይ የዓለም ዓቀፉ ፍርድ ቤት የክስ «ዋራንት» ቆርጦባቸዉ ነበር።አሁን አሁን አንዱ ክስ ገና በወጉ ታዎቆ ወደ የት ይሄዳል የሚለዉ ሳይለይ በክስ ላይ ክስ  ተደራራቢ ክሶች እየመጡ ያለበት ሁኔታ ነዉ ያለዉ።ሀገሪቱ ወደ ተሻለ አቅጣጫ ከመምራት ይልቅ በቀልና ያለፈ ሂሳብን የማወራረድ አዝማሚያ ያለይመስላል።» ብለዋል።
የሱዳን ጠቅላይ ዓቃቬ ህግ ፅ/ቤት ክሱን የመሰረተዉ ያለፈዉ ጥር በተቃዉሞዉ ወቅት በካርቱም አቅራቢያ በምትገኝ ቡሃሪ በተባለች ከተማ የተፈፀመን  የአንድ ወጣት ሀኪም ግድያን ካጣራ በኋላ ነዉ።   
በሱዳን ህዝባዊ ተቃዉሞ እስካሁን 100 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ፤ ግድያዉና ተቃዉሞዉ አሁንም ድረስ አልቆመም።የአልበሽር ክስ ከተሰማ ከስዓታት በኋላ እንኳ አንድ የጦር መኮንንን ጨምሮ ስድስት ሰወች በፀጥታ ሀይሎች መገደላቸዉን የሀገሪቱ የዜና አዉታር ሱና ዘግቧል።
ምክንያቱ ደግሞ የአልበሽርን ስልጣን መልቀቅና እስር ቤት መዉረድ  ተከትሎ የሀገሪቱን የሽግግር ጊዜ የመምራት ስልጣን የያዘዉ የሀገሪቱ  ወታደራዊ ምክር ቤት በሲቪል አስተዳደር እንዲተካ የሚጠይቁ ተቃዉሞዎች መቀጠላቸዉ ነዉ። ከዚህ የተነሳ መዲናዋን ካርቱምን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች አሁንም ድረስ መንገድ በሚዘጉና የመኪና ጎማ በሚያቃጥሉ የተቃዉሞ ሀይሎች ይታመሳሉ።በፀጥታ ሀይሎች የሚፈጸመዉ ግድያም እንዲሁ።
ካለፈዉ ታህሳስ ጀምሮ ተቃዉሞዉን በማስተባበር ላይ ያለዉ የሱዳን የሙያ ማህበራት አካል የሆነዉ የሱዳን የሀኪሞች ኮሚቴ በበኩሉ ሀገሪቱን የሚመራዉ ወታደራዊ ምክር ቤት በተጠየቀዉ መሰረት ስልጣኑን ለሲቪል ባለማስረከቡ የመጣ ነዉ በሚል  እየደረሰ ላለዉ ጥፋት ምክር ቤቱን ተጠያቂ አድርጓል።
መሪዎች የዕድሜ ልክ ስልጣን በሚፈልጉባት አፍሪቃ በዜጎች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የኢኮኖሚ ጉዳት መድረሱ አይቀሬ ነዉ የሚሉት አቶ አበበ በእያንዳንዱ ጉዳይ ከመካሰስ ይልቅ የሽግግር ሂደቱን የሱዳናዉያንን ህይወት በሚያሻሽል መልኩ መምራት ይበጃል ይላሉ።

Sudan Proteste in Khartum
ምስል Reuters/M.N. Abdallah
Sudan April 2019 | Omar al-Baschir, Präsident
ምስል Reuters/M. Nureldin Abdallah

«ከዚህ ይልቅ መሆን ያለበት የሚመስለኝ ነገር ለሱዳንም የሚበጃት ነገር አሁን የሽግግር ሂደቱ ጤናማ ሆኖ ለሱዳናዉያን ኑሮ መሻሻል፣ ለፍትህ፣ ለዶሞክራሲያቸዉ በሚበጅ መልኩ ለዉጡን መምራቱ ቅድሚያ ቢሰጠዉ የተሻለ ነገር የተረጋጋ ነገር ሊፈጥር ይችላል።»

Sudan Proteste in Khartum
ምስል Reuters/M.N. Abdallah

እንደ ፖለቲካ ተንታኙ አቶ አበበ አይነቴ በሱዳን የሚታየዉን ተቃዉሞና አለመረጋጋት የሚያቆመዉ የአልበሽር እስርና ክስ ሳይሆን ለተቃዉሞ የወጡ ዜጎችን ጥያቄዎች በአግባቡ መመለስ ነዉ።ለዚህም ይመስላል «የነፃነትና የለዉጥ ሀይል ምክር ቤት» የተባለዉ የተቃዋሚ ጥምረት የተጠየቀዉ የነፃነትና  ወታደራዊ ሀይሉ በሲቪል አስተዳደር ይተካ ጥያቄ እስካልተመለሰ ድረስ ተቃዉሞዉ ይቀጥላል ሲል በዛሬዉ ዕለት የገለፀዉ።  

 

ፀሐይ ጫኔ

ኂሩት መለሰ