1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአለም ሕግ፦ ፀረ ሽብር ዘመቻና የሰብአዊ መብት ረገጣ

ሰኞ፣ የካቲት 30 2001

የአለም ሕግ የሰዎችን ደሕንነት፥ እኩልነት፥ መብት ሠላምን ለማስከበር ከቆመ በድፍን አለም ከሚፈፀመዉ ግፍ በደል ሁሉ የዳርፉር የቀደመ-የበለጠበት ሰበብ ምክንያት ግራ-መሆኑ ነዉ-አጠያያቂዉ

https://p.dw.com/p/H8bz
ልዩ አጥኚ ሻይኒንምስል AP

እሳቸዉ ነቃ-ለቀቅ ቀበጥ ከሚል ሕዝብ-ባሕል የወጡ ሰፋ-ግን ደሕየት፣ ሞቅ ወበቅ በምትለዉ ሐገር ተወልደዉ ያደጉ ናቸዉ።ሊዊስ ሞሬና-ኦካምፖ።አርጀቲና።እኚሕኛዉ ባንፃሩ ጨመት፣ ጨበጥ፤ ረቀቅ ያለ ሕዝብ ባሕል ግኝት፤ የትንሽ ግን የከበርቴ፤ የበራድ-ቀዝቀዛ ሐገር ዉልድ ናቸዉ።ማርቲን ሻይኒን።ፊንላንድ።ይለያያሉ።በትምሕርት፤ በሙያ፤ በሚሰሩለት ድርጅት፣ በአላማ ግን አንድ ናቸዉ። ልዩም-አድም።ባለፈዉ ሐምሌ ላንድ-ድርጅት ለተለያየ ክፍል፣ ላንድ አላማ-ለተለያየ ሥልት ባንድ ቀን በተለያየ ሐገር ያደረጉትን ሲያደርጉ የነበራቸዉ ልዩነት ዛሬ በስምተኛ ወሩ የአለምን የልዩነት ርቀት፣ የሕግ፤ የፍትሕ፣ አተረጓጎሟን ተቃርኖ አፈጋዉ።የምግባራቸዉ የቅርብ ዉጤት፣ መነሻ፤ ማን-ምንነታቸዉ ማጣቃሻ፣የአለም እዉነት መድራሻችን ነዉ ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።

---------------------

የመንገደኞች አዉሮፕላኖችን የጠለፉ የአል-ቃኢዳ አባላት ኒዮርክና ዋሽንግተንን ካሸበሩበት ዕለት ወዲሕ አለም «ሽብር-ወይም አሸባሪ» ከሚሉት ቃላት እኩል የጠራቸዉ፤ ወይም የሚሰማቸዉ ሥም-ቃላት መኖራቸዉ አጠራጣሪ ነዉ።

ቃሉን በየቋንቋዉ ለየሕዝቡ መዓልት ወሌት የሚያዥጎደጉዱት፣ በቃሉ የሰሟቸዉን የሚያወግዙ፣ የሚወጉ፤ የሚገድሉ፣ የሚቀጡት የአለም መሪ-ፖለቲከኞች፣ ዳኛ-ሕግ አስከባሪዎች፣ ዲፕሎማት-አስተንታኞቹ፤ የመብት ተቆቋሪ-ጋዜጠኞች ለሽብር-እንዴትነት አግባቢ ብያኔ አለማግኘታቸዉ ነዉ ዚቁ።

የቀድመዉ የአለም ማሕበር ሊግ ኦፍ ኔሽንስ በ1937 (ዘመኑ በሙሉ እንደ አዉሮጳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) አሸባሪነትን ለመበየን ያደረገዉ ሙከራ ከከሸፈ ጀምሮ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በተለያየ ጊዜ ያረቀቃቸዉ ብያኔዎች አለማፅደቃቸዉ የሕግ ፕሮፌሰርና የመብት ተሟጋች ማርቲን ሻይኒን እንደሚሉት መንግሥታት ወይም ተቋማት የሚጠሉትን ሁሉ በአሸባሪነት እየወነጀሉ እንዲመቱ ጥሩ ሰበብ፤ ከሕግ ለማምለጥም ደሕና ማደናገሪያ ሆኗቸዋል።

ሰበብ ማደናገሪያዉን ኢራቅን ለመዉረሪያነት ያዋሉት የፕሬዝዳት ቡሽና የጠቅላይ ሚንስትር ቶኒ ብሌር መስተዳድሮች ያዘመቱት ጦር ባግዳድን በተቆጣጠረ በሳልስቱ አርጀንቲናዊዉ እዉቅ የሕግ ባለሙያ ሊዊስ ሞሬና ኦካምፖ የተባበሩት መንግሥታት የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤት ጠቅላይ አቃቢ ሕግ ሆነዉ ተሾሙ።

ኦካምፖ የሾማቸዉ ድርጅት ሕግ የተጣሰበትን፤ የአለም ሕዝብ ተቃዉሞ ያየለበትን፤ መንግሥታት የተቃቃሩበትን ወረራ አለማ፣ ምክንያትን የማጣራቱን ጡቃንጡቅ ትተዉ ቢከሱ፣ ቢወንጅሉ፣ ቢያስቀጧቸዉ የሚጎዳ ጥርስ-ጥፍር የሌላቸዉ፣ ወይም የጎጂዎቹ ድጋፍ የተፈጋቸዉን የዩጋንዳ፤ የጎንጎ፤ የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ተጠርጣሪዎችን ሲያድኑ ከመሾማቸዉ ሁለት ወር ቀደሞ ዳርፉር የተጫረዉ ግጭት የአለም መገናኛ ዘዴዎች ርዕሥ ሆነ።

ፕሮፌሰር ሻይኒን ባንፃሩ ለኢራቅ ወረራ አሳማኝ ምክንያትን ከመፈለግ ጋር ሰላማዊ ሰዎችን የገደለ፤ እገላለሁ እያለ ያሸማቀቀ፣ መንግሥት፤ ቡድን፤ ድርጅት ይሁን ግለሰብ አሸባሪ ነዉ።የሚል እምነት አቋማቸዉን ለማስረዳት በየዩኒቨርስቲ-ጉባኤዉ ይዞሩ ነበር።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የመብት፤ የፍትሕ ተሟጋቾችን ዉትወታ፤ የሚሊዮኖች ጩኸትን ለማድመጥ ደንብ ሕጉን እንደየሚቻቸዉ የሚያጥፉ፣ የሚዘረጉለት፣ ሕልዉናዉን የሚያቀጭጩ-የሚያፋፉለት ሐይላት አሸባሪ የሚሉትን ሁሉ ከአፍቃኒስታን፣ ከፓኪስታን ከኢራቅ፣ ከሁዋንታናሞ አልፈዉ ከድፍን አለም ለቅመዉ፣ በየሚሹበት ሥፍራ አጉረዉ የሚሹትን ሁሉ እስኪያደርጉ መጠበቅ ነበረበት።

ጥበቃዉ በሁለት ሺሕ አምስት አጋማሽ አብቅቶ «በፀረ-ሽብር ዘመቻ ሽፋን የሚፈፀም የመብት ጥሰት እንዲጠና አለም አቀፉ ድርጅት ሲወስን-እኛ ሰዉ ልዩ አጥኚ ሆኑ።ማርቲን ሻይኒን።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጦር ወንጀል፤ ግድያ፤ የፖሊስን ሕገ-ወጥ እርምጃ፥ በሕፃናት፣ በሴቶች በአናሳ ጎሳዎች ወዘተ-የተፈፀሙና የሚፈፀሙ የመብት ረገጣዎችን የሚያጣሩ ሃያ-ሰወስት ልዩ አጥኚዎች አሉት።

የብዙዎቹ በርግጥ ቀላል አይደለም።ይኸኛዉ ግን ሻይኒን እንዳሉት አላማዉ ሰናይ ተልዕኮዉ ግን ከባድ-ዉስብስብም ነዉ።

ድምፅ

«የየሐገራቱ ልዩ ገፅታዎች አሉ።የያንዳዱን ሐገር ሁኔታ በተናጥል የመመርመር ሒደት ያስፈልጋል ማለት ነዉ።የርዕሠ-ጉዳዮቹ ልዩ ገፅታዎችም አሉ።ጉዳዮቹን በጥልቅ የመፈተሹ ሁኔታ አለ ማለት ነዉ።እነዚሕ ሁለቱም ዉስብስብ ጉዳዮች በኔ ሐላፊነት ዉስጥ ይከተታሉ። ዝር ዝር ምግባሩ የተለያዩ ሐገራትን የመጎብኘት ተልዕኮን ያካትታል።ጉብኝቱ የየሚጎበኘዉ ሐገር የሚወሰደዉን የፀረ-ሽብር ዘመቻ እርምጃ መጠንን እና እርምጃዉ ሠብአዊ መብትን ከመጠበቅ ጋር መጣጣሙን ለማገንዘብ ይረዳል።»

ሻይኒን አለም የሚፈራቸዉ የፈፀሙትን ግፍ ለማጣራት ለመጋፈጥ በወሰኑ በወሩ ኦካምፖ የአለም አስፈሪዎች ያወገዙ፣ የጠሉ፣ የወንጀሏት ሱዳንን እንዲከሱ በሰጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ያስወሰኑት ትዕዛዝ ደረሳቸዉ።መስከረም- ሁለት ሺሕ አምስት።

Luis Moreno Ocampo
ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ኦካምፖምስል dpa - Fotoreport

ሻይኒን የመጀመሪያ ዘገባቸዉን በሁለት ሺሕ ሰባት ይፋ ሲያደርጉ ከሁለት ሺሕ አንድ ጀምሮ በዩናይትድ ስቴትስ መሪ አስተባባሪነት በሚካሔደዉ ፀረ-ሽብር ጦርነት ሰበብ ከዩናይትድ ስቴትስ እስከ አዉስትራሊያ፤ ከአዉሮጳ-እስከ ካናዳ፤ ከሞሮኮ እስከ ኢትዮጵያ፤ ከፓኪስታን እስከ ቱርክ የሚገኙ የአለም መንግሥታት ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ረገጣ ማድረሳቸዉን አጋልጡ።

በየሐገሩ የሚታሰሩ፤ ከየሐገሩ የሚጋዙ፣ ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት ባለመቅረባቸዉ የተፈፀመባቸዉን ግፍ በደል ለማወቅ አለመቻሉን፥ ይሕ አይነቱ ግፍ ሕግ ከመጣስ ባለፍ ሽብርን ከማስቆም ይልቅ የሚያበረታታ መሆኑም አስጠነቀቁ።

ድምፅ

«በሸባሪነት የሚጠረጠሩ ሰዎች ለፍርድ የመቅረብ መብታቸዉ ከተነፈገ አሸባሪ እንዲሆኑ ይገፋፋቸዉ ይሆናል።እነሱ ባይችሉ እንኳን ዘመድ-ወዳጆቻቸዉ ወይም ባልደረቦቻቸዉ አሸባሪ እንዲሆኑ ምክንያት ይሆናቸዋል።»

ኦካምፖ በቀደም እንዳሉት የሐገር መሪነትም ሆነ፤ የፍርድ ቤታቸዉን ሕልዉና አለማወቅ ሕግ ፊት ላለመቅረብ ዋስትና አይሆንም።ምግባራቸዉ እንደ ማዕረግ፤ ሹመታቸዉ፣ እንደብሒል ቃላቸዉ ቢሆን ኖሩ ከዩጋንዳ-ኮንጎ እኩል አፍቃኒስታን፣ ከማዕከላዊ አፍሪቃ እኩል ኢራቅ፣ ከዳርፉር እኩል አቡ-ግራይብ ዋንታናሞ ለተዋለዉ ግፍ ተጠያቂዎችን ለሕግ ለማቅረብ የባልደረባቸዉ ጥናት ዉጤት ጥሩ መረጃ በሆናቸዉ ነበር።

ሻይኒን የመጀመሪያ ዘገባቸዉን ካቀረቡበት ጊዜ ጀምሮ ፕሬዝዳት ቡሽን የሚተካዉ የአሜሪካ መሪ ማንም ይሁን ማን በአሸባሪነት በሚጠረጠሩ ሰዎች ላይ ለተፈፀመዉ ግፍ፤ ለሕግ መጣስ፤ ለፍትሕ መረገጥ አይነተኛ ዋቢ፤ ጉሉሕ ማስረጃ የሆነዉን የዋንታኖሞ ማጎሪያን እንደሚዘጋ እርግጠኛ-በተስፋዉ ደስተኛም ነበሩ።

ድምፅ

«አዲሱ መስተዳድር የፕሬዝዳንቱ ማንነትና ስሙ ማንም ይሁን ማን የዋንታናሞን የእስራት ማዕከል ባስቸኳይ የሚዘጋበትን እቅድ ያዉጃል የሚል ጠንካራ እምነት ነበረኝ።»

የሱዳን መካከለኛ ባለሥልጣናትን፤ የጃንጃዊድ መሪን ለመክሰስ ሲባትሉ የሻይኒን የመጀሪያ ዘገባ ያለፉት ኦካምፖ ባንፃሩ ለወራት እየበጠሱ-የቀጠሉ፣ እየለጠጡ-የጨምቁትን መረጃ አባሪ ያደረጉበትን የክስ ማመልከቻ ለፍርድ ቤቱ ሲያስገቡ ድል-እንደሚያደርጉ ያደረጉ ያክል እርግጠኛ ደስተኛም ነበሩ።

ሻይኒን ባንጻሩ ለአመት የሰበሰቡ፣ የመረመሩትን መረጃ ሥለሚዘግቡበት ሥልት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤና ከሰብአዊ ምክር ቤት መሪዎች ጋር ለመነጋገር ምክክር ከተባለዉ ስብሰባ ሲቀመጡ ቀዝ-ቀዝ ተከዝ እንዳሉ ነበር።እንደ ሁለቱ ባለሙያዎች ስሜት ልዩነት ሁሉ የነበሩበትም ሥፍራ የተለያ ነበር።ዘ-ሔግና ዤኔቭ። ቀኑ ግን አንድ ነዉ።ሐምሌ አስራ-አራት ሁለት ሺሕ ስምንት።

የኦካምፖ ማመልከቻ በስምተኛ ወሩ በቀደም ሮብ በርግጥም ለርግጥ ድል በቃ።

ድምፅ

«ኡመር አልበሽር የሱዳን ባለሙሉ ሥልጣንና ወሳኝ ፕሬዝዳት እና የሱዳን ጦር ሐይሎች ጠቅላይ አዛዥ እንደመሆናቸዉ መጠን፥-የፀረ-ሽምቅ ዉጊያዉን ዘመቻ እቅድና ተፈፃሚነቱን በበላይነት በማቀነባበር ተጠርጣሪ ናቸዉ።»

ኦካምፖ በዘር ማጥፋት፣ በጦር ወንጀል፣ በሰዎች ላይ በተፈፀመ ወንጀል-እያሉ በአስር የወንጀል ጭብጥ የከሰሷቸዉ ሱዳን ፕሬዝዳት ኦመር አልበሽር እንዲታሰሩ መበየኑ ለሱዳን ሰላም፥ ለአለም ሕግ ልዕልና መጥቀም አለመጥቀሙ አለምን ሲያከራክር የፕሮፌሰር ሻይኒን ሁለተኛ ዘገባ ተጠናቅሮ አበቃ።ነገ-ይፋ የሚሆነዉ ዘገባ እንደሚያመለክተዉ የዋንታናሞ እስር ቤት እንዲዘጋ መወሰኑ በፀረ-ሽብር ዘመቻ ሰበብ የሚፈፀመዉን የመብት ረገጣ እንዲቆም ለሚታገሉ ሐይላት በርግጥ ድል ነዉ።ከዚሕ ባለፍ ግን ሲ አይ ኤን የመሳሰሉ የሥለላ ተቋማት፥ የጦር ሐይላት በተጠርታሪዎች ላይ የሚያደርሱት ግፍ በደል የአለምን ሕግ፥ የፍትሕን ልዕልናም እየናደዉ ነዉ።

አልበሽር ጥፋተኛ አይደሉም ብሎ የሚከራከር ካለ በርግጥም አንድም እራሳቸዉ ሁለትም ደጋፊዎቻቸዉ፥ ሰወስትም ብጤዎቻቸዉ ናቸዉ።የአለም ሕግ የሰዎችን ደሕንነት፥ እኩልነት፥ መብት ሠላምን ለማስከበር ከቆመ በድፍን አለም ከሚፈፀመዉ ግፍ በደል ሁሉ የዳርፉር የቀደመ-የበለጠበት ሰበብ ምክንያት ግራ-መሆኑ ነዉ-አጠያያቂዉ።ነጋሽ መሐመድ ቸር ያሰማን።

ZPR (Töne),UNO Bericht Über Menschenrechte den Kampf gegen Terrorismus,Wikipedia

Negash Mohammed

►◄