1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የናይጄሪያ ጦርና የቦኮሃራም ስጋት

ሰኞ፣ ጥር 25 2007

በሰሜናዊ ናይጄሪያ የሚንቀሳቀሰው እስላማዊ ቡድን ቦኮ ሃራም የማይዱግሪ ከተማን ለመቆጣጠር ለሁለተኛ ጊዜ የከፈተው ጥቃት አልተሳካም። በዚህ ወር በሚካሄደው የናይጄሪያ ምርጫ ላይ ጥቃት ሊሰነዝር ይችላል የሚል ስጋት በማየሉ የቀጠናው ሃገራት ወታደራዊ እርምጃ ጀምረዋል።

https://p.dw.com/p/1EUck
Nigeria Maiduguri Militär Sicherheit Anti Boko Haram 2014
ምስል picture-alliance/epa

በናይጀርያ የሚንቀሳቀሰዉ ቦኮ ሀራም የእስልምና አክራሪ ቡድን የቦርኖ ግዛት ዋና ከተማ የሆነችውን ማይዱግሪ ከተማ ለመቆጣጠር ጥቃት መክፈቱ ተሰምቷል። ከጽንፈኛ ታጣቂ ቡድኑ በሳምንት ለሁለተኛ ጊዜ ጥቃት የተሰነዘረባትን ከተማ የናይጄሪያ ጦር እና የከተማዋ ነዋሪ በጋራ መከላከላቸውን የፈረንሳይ የዜና ወኪል ዘግቧል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ከ 2009 ዓ.ም. ጀምሮ በሃይማኖታዊ ህግጋት የሚተዳደር ግዛት ለመመስረት በሽምቅ ውጊያ የጀመረው ቦኮ ሃራም ባለፈው አመት በሰሜን ምስራቅ ናይጄሪያ በርካታ ከተሞችንና መንደሮችን በሃይል ወስዷል። በቦኮ ሃራም ጥቃት ባለፈው አመት ብቻ 2000 ናይጄሪያውያን ሲሞቱ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ለስደት ተዳርገዋል።

በዚህ ወር ለሚካሄደው የናይጄሪያ ምርጫ ለምረጡኝ ዘመቻ በቦኮ ሃራም ጥቃት ወደ ደረሰባቸው አካባቢዎች የተዘዋወሩት ፕሬዝዳንት ጉድ ላክ ጆናታን ለችግሩ ትኩረት አልሰጡም የሚል ትችት ይቀርብባቸዋል። የቦርኖ ግዛት አስተዳዳሪ ካሺም ሼቲማ የግዛቲቱ ነዋሪዎች ከሃገሪቱ ጦር ጋር በመተባበር በቦኮ ሃራም ላይ የጀመሩትን ጥቃት እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል። ቻድ እና ካሜሮንም በጽንፈኛው ቡድን ላይ የተጀመረውን ዘመቻ ተቀላቅለዋል።የጸጥታ ተንታኝ የሆኑት ካቢሩ አዳሙ በቦኮ ሃራም ላይ የተጀመረውን ወታደራዊ ዘመቻ ስኬታማ ለማድረግ የሌሎች ሃገሮች እገዛ አስፈላጊ መሆኑን ይናገራሉ።

«የናይጄሪያም ሆነ የሶስቱ ሃገሮች ጦር አለም አቀፍ እገዛ ያስፈልገዋል።ይህ የግድ የጦር መሳሪያ እርዳታ ብቻ ማለት አይደለም። በዋናነት የመረጃ አሰባሰብ፤አጠቃቀም እና እንዴት ስኬታማ ወታደራዊ ዘመቻዎች ማካሄድ ይቻላል በሚሉ ጉዳዮች ላይ እገዛ ሊደረግላቸው ያስፈልጋል። ስብሰባዎች በማካሄድ ቃል መግባት ብቻ ለውጥ አያመጣም።»

ካቢሩ አዳሙ አራቱ የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት በቦኮ ሃራም ላይ ለጀመሩት ዘመቻ ስኬታማነት የጋራ ግብ ማስቀመጥ መረጃ በአግባቡ መሰብሰብና መለዋወጥ እንዳለባቸው በአጽንኦት ይናገራሉ። ጠንካራ የጦር ሰራዊት የሚያዘው የናይጄሪያ መንግስት ቡድን የሚፈጽማቸውን ጥቃቶች አስቀድሞ መከላከል አለመቻሉ ለትችት አጋልጦታል። ካቢሩ አዳሙ በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ከፍ ያለ ዝና ያተረፈው የናይጄሪያ ጦር በሙስና የተጨማለቀ በመሆኑ ቦኮ ሃራምን መግታት አይችልም ሲሉ ይናገራሉ።

Nigeria Maiduguri Boko Haram
ምስል picture-alliance/dpa

«የናይጄሪያ ወታደሮች በሰላም ማስከበር ዘመቻዎች ስኬታማ ናቸው ተብሎ በአለም አቀፍ ደረጃ ስለሚሞገሱ ለራሳቸው የሚሰጡት ክብር ከፍ ያለ ነው። ይህው ጦር የሙስና ችግር አለበት። ብዙ ነገሮች ተበላሽተዋል። አሁንም እየተበላሹ ነው። አሁን እኛ የምንጠይቀው አለም አቀፍ ትኩረት ቢሰጥ እነዚህ ችግሮች ይጋለጡ ነበር። ነገር ግን ከፍተኛ የመንግስት የመንግስት ሹማምንትም ይሁኑ የጦሩ ባለስልጣናት እንዲህ አይነት ትኩረት አይፈልጉም።»

የናይጄሪያ መንግስት ቦኮ ሃራም እና መሪው አቡባካር ሼካውን አስመልክቶ ጥርት ያለ መረጃ የለውም እየተባለ ይተቻል። መንግስት በአንድ ወቅት ሞተ ያለው አቡበከር እድሜው በትክክል አይታወቅም።

የናይጄሪያ መንግስት ከቻድ እና ካሜሮን ጋር በመተባበር በቡድኑ ላይ የአየር ጥቃት መጀመሩን ኤ.ኤፍ.ፒ. የዜና ወኪል ዘግቧል። ከምርጫ ይልቅ ለሐይማኖታዊ ህግጋት ቅድሚያ የሚሰጠውቦኮ ሃራም በዚህ ወር በሚካሄደው ምርጫ ጥቃት ሊሰነዝር ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።

እሸቴ በቀለ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ