1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የናይጄሪያ ታጣቂዎች ጥቃት

ማክሰኞ፣ የካቲት 11 2006

በናይጄሪያ የክርስትና እና የእስልምና ዕምነት ተከታዮች ዘንድ ብዙም ሰላም አይስተዋልም። ከሳምንቱ መጨረሻ ጀምሮ ዳግም በሰሜን ምስራቃዊ ናይጄሪያ ከ100 የሚበልጡ ሰዎች ተገድለዋል። ለዚህም የሚጠረጠረው የናይጄሪያው አክራሪ ቡድን ቦኩ ሀራም ነው።

https://p.dw.com/p/1BAda
Nigeria Boko Harem Angriff in Damaturu
ምስል picture-alliance/AP

በሰሜን ምስራቃዊ ናይጄሪያ ቦርኖ ከተማ በርካታ የክርስትና ዕምነት ተከታዮች ይኖራሉ። የአይን እማኞች ለፈረንሳይ ዜና ወኪል እንደገለፁት ካሜሮን ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው ከተማ ባለፉት ቀናት ታጣቂዎች የመንደሩን ነዋሪዎች ሲያባርሩ እና ሰዎች ላይ ሲተኩሱ ተስተውሏል። በናይጄሪያ የፀጥታ ጉዳይ ባለሙያ የሆኑት ሁሴይኒ ማንጉኑ እንደሚሉት ያለው ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ነው ።

Nigeria Soldaten
ምስል Quentin Leboucher/AFP/Getty Images

« እስካሁን ያለው ሁኔታ እጅግ አስደንጋጭ ነው። ሰዎች እየሞቱ ይገኛሉ። ቤታቸው ቀን በቀን እየተቃጠለ ነው። ሰዎች ግራ ተጋብተው ነው የሚገኙት። በተለይም በሰሜን እና ደቡብ ቡርኖ ያለው የሰዎች ደህንነት እጅግ አስደንጋጭ ነው። »ለሚደርሱት ጥቃቶች በሙሉ የሚጠረጠረው አክራሪው ቡድን ቦኩ ሀራም ነው። የናይጄሪያ ጦር በበኩሉ የሰሞኑ ጥቃት መድረሱን አረጋግጧል። ይሁንና የናይጄሪያ መንግሥት በቂ ደህንነት ለህዝቡ እየሰጠ አይደለም ነው የሚሉት የፀጥታው ጉዳይ ባለሙያ ማንጉኑ

«ፖሊስ የናይጄሪያ ጦርም ይሁን የሲቪል መከላከያው ምንም አይነት ርምጃ እየወሰዱ አይደለም። ያለ ምንም አማራጭ ተትተናል። ምን አልባት መንግሥት የሚደርሰው ቀውስ አያሳስበውም አልያም የሚሆነውን ነገር ይደግፋል። ለምን ቢባል ብዙ ገንዘብ ለዚህ ጥቃት ተመድቧል። ይሁንና በስራ ላይ ሲውል አይታይም። የቦሮኖ ወታደሮች ሳይቀሩ ጣልቃ ለመግባት በቂ የሰው ኃይል የለንም ይላሉ በጣም የሚያሳዝን ሁኔታ ነው ያለው። እንደሚመስለኝ የአለም ዓቀፍ ርዳታን እንሻለን።»

Nigeria Soldaten
ምስል Quentin Leboucher/AFP/Getty Images

የጎርጎሮሲያኑ 2014 ከጀመረ አንስቶ ብቻ 14 መንደሮች ላይ ጥቃት እንደተጣለ የገለጹት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት ሂውማን ራይትስ ዎች የናይጄሪያ ተመራማሪ ማውዚ ሼጉን ቦኮ ሀራም መንደሮቹን እየመነጠረ ነው ይላሉ። ቦኮ ሀራም ጥቃት የሚያደርስባቸው አካባቢዎች በብዛት የክርስትና እምነት ተከታዮች በሚኖሩበት መንደሮች ነው፤ ይሁንና ጥቃቱ ከእምነት ጋር ብቻ የተያያዘ ነው ለማለት ይከብዳል ይላሉ ተመራማሪ፤ «ከመጀመሪያው አንስቶ ቦኮ ሀራም እስልምናን ሊያስፋፋ ወይም የሻሪያን ህግ ለማስከበር እንደሚፈልግ ግልፅ አድርጓል። ነገር ግን በቅርቡ የደረሱትን ጥቃቶች ስመለከት ያስተዋልኩት ነገር ቢኖር የደቡቡ ቦርኖ ሐይማኖትን የተመለከትን እንደሆን ክርስትያኖች የሚኖሩበት ነው ይሁንና የዛኑ ያህል ይህ ስፍራ ለቦኮ ሀራም ለመሸሸግ እጅግ አመቺ ስፍራ ነው። ስለዚህ ክርስትያኖችን ለማጥቃት የታለመ ነው ወይም በዚህ አካባቢ ያሉትን መንደሮች ለመመንጠር ስለሚያመነቻቸው ነው ለማለት ያስቸግራል።»

ባለፉት 1 ወር ተኩል ውስጥ ብቻ ከ330 በላይ የሚሆን ሰው ህይወት መጥፋቱ ተገልጿል። የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት የናይጄሪያ ተመራማሪ እንደሚሉት የማህበረሰቡን ሰላም በማስከበሩ ረገድ የናይጄሪያ መንግሥት ቦኮ ሀራምን ለንግግር መጋበዝ ይኖርበታል።

ልደት አበበ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ