1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የናይጀሪያ ፕሬዚደንት እና ፀረ ሙሰና ዘመቻቸው

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 9 2007

የናይጀሪያ ፕሬዚደንት መሀማዱ ቡሃሪ በሃገራቸው ስር የሰደደውን ሙስና የሚታገል አንድ ቡድን አቋቋሙ። ይህ ውጤታማ እንደሚሆን ተስፋ የተጣለበት ርምጃቸው ሕዝባቸውን ብቻ ሳይሆን በሃገሪቱ ገንዘባቸውን ለማሰራት የሚፈልጉትን አስደስቷል።

https://p.dw.com/p/1GG1w
Nigeria Symbolbild Muhammadu Buhari Anti-Korruptions-Offensive
ምስል picture-alliance/AP Photo/C. Owen

የናይጀሪያ ፕሬዚደንት እና ፀረ ሙሰና ዘመቻቸው

ሥልጣን ከተረከቡ ሁለት ወር ተኩል የሆናቸው አዲሱ የናይጀሪያ ፕሬዚደንት መሃማዱ ቡሃሪ ሰባት አባላት ያሉት ፀረ ሙስና ቡድን ሠይመዋል። በብዛት ምሁራን የተጠቃለሉበት ይኸው ቡድን የፕሬዚደንት ቡሃሪ መንግሥት ሙስናን ለመታገል በሚያደርገው እና በሕጉ ሥርዓት ላይ አስፈላጊውን ተሀድሶ ለማንቀሳቀስ በጀመረው ጥረቱ ላይ የማማከር ተግባር እንደሚኖረው የፕሬዚደንቱ ቃል አቀባይ አስታውቆዋል። ፕሬዚደንት ቡሃሪ ከዚሁ ርምጃቸው ቀደም ሲል ባለፈው ሳምንትም አዲስ የብሔራዊ ነዳጅ ዘይት ተቋም ኃላፊ ሾመዋል።
ናይጀሪያ ውስጥ ካለፉት ስድት ዓመታት ወዲህ በመንግሥቱ አንፃር የሚዋጋው የአክራሪ ሙስሊሞች ቡድን ቦኮ ሀራም ሚሊሺያዎች ባለፈው ሀምሌ ወር በተደጋጋሚ ጥቃት ከጣሉ በኋላም ፕሬዚደንቱ በርካታ የጦር ኃይሉ ኃላፊዎችን በአዲስ በመተካት የአክራሪዎቹን ደም አፋሳሽ ጥቃት በሶስት ወራት ውስጥ እንዲያበቁ አዘዋል።
Nigeria Soldaten in Diffa
ምስል Reuters/J. Penney
የናይጀሪያ ሕዝብ የአክራሪዎቹን ጥቃት ለማብቃት ፕሬዚደንት ቡሃሪ ያንቀሳቀሱት ርምጃቸውን አድንቆዋል። ከነዚህ መካከል አንዱ ኤዜንዋ ንዋጉ ናቸው። ኤዜንዋ ንዋጉ ሙስናን ለመዋጋት እና ጥፋት የሰሩ ባለሥልጣናትም ሳይቀጡ ሊታለፉ አይገባም በሚል የተነሱ እና ራሱን « ሰይ ኖ ካምፔይን» ብሎ የሚጠራው ቡድን መሥራች ናቸው።
« አሁን በፕሬዚደንት ቡሃሪ ላይ ያለኝን ዓይነት እምነት ካሁን ቀደም በአንዱም የናይጀሪያ መሪ ላይ ኖሮኝ አያውቅም። እኒሁ ግለሰብ ካሁን ቀደም በታማኝነታቸውእና ሞራላዊ መመሪያዎችን የሚከተሉ ጠንካራ መሪ በመሆን ጥሩ ውጤት ያስመዘገቡ ናቸው። ይሁንና፣ አሁን ያስቀመጡትን ዓላማ ከግብ ለማድረስ የያዙት እቅዳቸውን የሚያካሂዱት እሳቸው ሙሉ ለሙሉ ባልተቆጣጠሩት አስተማማኝ ባልሆነ ጊዜ ውስጥ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። »
ቡሃሪ እአአ በ1980 ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ሃገሪቱን በወታደራዊ አምባገነን ሥርዓት በገዙበት ዘመን እንኳን በሙስና አንፃር ጠንካራ ትግል አካሂደዋል። ባለፈው ግንቦትም ፕሬዚደንት ሆነው በመመረጥ ፣ በሃገሪቱ ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በዴሞክራሲያዊ የሥልጣን ሽግግር የሃገሪቱን አመራር የያዙ ርዕሰ ብሔር ሆነዋል። አንዳንዶች ግን ካለፈው የቡሃሪ ታሪክ በመነሳት አዲሱ የናይጀሪያ ፕሬዚደንት በዴሞክራሲያዊው መንገድ ቢመረጡም ደሞክራሲያዊውን ሥርዓት ለማዳበር መስራታቸውን እንደሚጠራጠሩት ነው የሚናገሩት። ቡሃሪ አሁን ፀረ ሙስና ቡድን ማቋቋማቸውም በተቀናቃኞቻቸው ላይ የበቀል ርምጃ ለመውሰድ ነው በሚል ሀያስያን እና ባለፈው ምርጫ የተሸነፉት የቀድሞው ፕሬዚደንት ጉድላክ ጆናታን የመሩት በአህፅሮት «ፒ ዲ ፒ» በሚል መጠሪያ የሚታወቀው የሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አባላት ተችተዋቸዋል። በተለያዩ ሃገራት የሚታየውን ሙስና የሚያጋልጠው መንግሥታዊ ያልሆነው ዓለም አቀፍ ድርጅት «ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል» ባልደረባ አዋል ሙሳ ራፍሳንዣኒ ግን ይህን ትችት የተሳሳተ ነው ሲሉ አጣጥለውታል።በመዲናይቱ አቡጃ የሕግ ምክር ሰጪ ማዕከል ያላቸው እና የ«ሰይ ኖ ካምፔይን» ህብረት አባል የሆኑት ራፍሳንዣኒ እንደሚሉት፣ የራሳቸው የፕሬዚደንት ቡሃሪ ገዢው በአህፅሮት « ኤ ፒ ሲ » የሚባለው የጠቅላላ ተራማጆች ኮንግረስ ፓርቲ አባላት ሳይቀሩ በሙስና ተጠርጥረዋል።
« ይህ ዓይነቱ እኩይ አስተሳሰብ በአሁኑ ጊዜ የሚሰራ አይመስለኝም። ናይጀሪያውያን የራስን ፖለቲካዊ ጥቅም ለማራመድ እና ሙስናን የመታገሉ ጥረት የሰውን ትኩረት እንዳያገኝ ለማድረግ በሚሰነዘሩ የዚህ ዓይነቱ ጥሪዎች ተሰላችተዋል። እነዚህ ጥሪዎችን አንዳንዶቹ የ«ፒ ዲ ፒ» አባላት የሚደግፉት አይመስለኝም። ታማኝ የሆነ ማንም ናይጀሪያዊ አሁን በሃገሪቱ በሚታየው የሙስና ደረጃም ሆነ ተጠያቂዎቹ ካለቅጣት እየታለፉ ባሉበት ሁኔታ በፍፁም ደስተኛ አይደለም። »
Nigeria National Petroleum Corporation Öl-Industrie Korruption
ምስል Reuters/A. Sotunde
የፀረ ሙስናው ትግል ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትንም ቢሆን እንደማይተው ፕሬዚደንት ቡሃሪ በግልጽ አስታውቀዋል። በተለያዩት የናይጀሪያ ሚንስቴሮች እና የቀድሞ ሚንስትሮች ላይ ሙስናን የማጣራቱ ምርመራ እየተካሄደ ነው። ቡሃሪ በወቅቱ ብቃት ያላቸው አዳዲስ ሚንስትሮችን የማግኘቱ ቀላል ያልሆነ ተግባር እየጠበቃቸው ሲሆን፣ ባለፈው ሀምሌ በሰጡት መግለጫ የአዲሱ ካቢኔ ምሥረታ እስከቀጣዩ መስከረም ሊቆይ እንደሚችል አመልክተዋል። በዚህም የተነሳ የ74 ዓመቱ ቡሃሪ በናይጀሪያውያን ዘንድ «ባባ አዝጋሚ» የሚል ቅጽል ስም ወጥቶላቸዋል። ይህ ሲታሰብ ታድያ፣
የአዲሱ ፀረ ሙስና ኮሚቴ የስራ ጊዜን በተመለከተ የፕሬዚደንት ቡሃሪ ቃል አቀባይ እስካሁን ተጨባጭ መረጃ መስጠት አለመቻላቸው ብዙዎችን አላስገረመም። ምክንያቱም ፀረ ሙስናው ኮሚቴ የምርመራውን ውጤት ሊያቀርብላቸው የሚገቡት ሚንስትሮች ገና አልተሾሙሙም። በሰሜን ናይጀሪያ በሚገኘው የዛሪያ ዩኒቨርሲቲ ምጣኔ ሀብት ባለሙያ በሺር ኩርፉ እንደሚሉት፣ ዓለም አቀፉ ኤኮኖሚያዊ ማህበረሰብ ይህንኑ በመንግሥት ምሥረታው ሂደት ላይ የሚታየውን ክፍተት፣ ብሎም፣ በናይጀሪያ በቀጥታ ሊያነጋግረው የሚችል የገንዘብ ሚንስትር ያለመኖሩን ድርጊት አሳሳቢ ሆኖ አግኝቶታል። በናይጀሪያ ፖለቲካዊ ሥርዓት ላይ እምነት መልሶ እንዲያድር እና ከዓለም አቀፉ የኤኮኖሚ ማህበረሰብ ጋር ጤናማ ግንኙነት እንዲኖር ከተፈለገ ፕሬዚደንት ቡሃሪ በሙስና የተዘፈቁትን ሚንስቴሮች ተግባርን ሊቆጣጠር የሚችል ጠንካራ ካቢኔ እንደሚያስፈልጋቸው በሺር ኩርፊ በማስረዳት፣ ቡሃሪ እየተከተሉት ያለውን ዝግመት የታየበትን አሰራራቸውን ተችተዋል።
G7 Gipfel Schloss Elmau Merkel mit Muhammadu Buhari
ምስል Reuters/C. Hartmann
« ጉዳዩ በናይጀሪያ ኤኮኖሚ ላይ ከብዙ ጊዜ አንስቶ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳረፈ ስለሆነ የሚሰሩትን ጠብቆ ማየት ይኖርብናል። ካቢኔአቸውን እስካሁን አለመሰየማቸው አሳሳቢ ነው። በተለይ፣ ያለፉት አስር ዓመታትን የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ሆነው ከቆዩ በኋላ፣ በምርጫ አሸንፈው ሥልጣን ከተረከቡ ከሁለት ወራ በኋላም በካቢኔአቸው ውስጥ የሚጠቃለሉትን እና ወዲያውኑ ወደ ስራ ሊገቡ የሚችሉ ሰዎችን እስካሁን አለማሰባሰባቸውን ለመረዳት አዳጋች ነው። »
ይሁን እንጂ ፣ በቡሃሪ ላይ ትልቅ እምነት ያሳደሩት የናይጀሪያ ሕዝብ እና ዓለም አቀፍ አጋሮች የአዲሱን ፕሬዚደንት አካሄድ የተረዱት ይመስላል። ግዙፉ ሙስና እና ከርሳቸው በፊት ሃገሪቱን የመሩት ጉድላክ ጆናታን ማስቆም ያልቻሉት ደም አፋሳሹ የቦኮ ሀራም ጥቃት፣ ከዚህ በተጨማሪ፣ የነዳጅ ዘይት ዋጋ በዓለም ገበያ ላይ መውደቅ የግዙፏን የአህጉሩ ኤኮኖሚያዊ ኃያል መንግሥት ናይጀሪያ ምጣኔ ሀብት ችግር ላይ በመጣሉ፣ ከባድ ስራ የሚጠብቃቸው ፕሬዚደንቱ በመንግሥት ምሥረታው ላይ ጊዜ መውሰዳቸውን ብዙዎች ትክክለኛ አድርገው መመልከታቸውን በናይጀሪያ ያለው የጀርመን ኤኮኖሚ ቡድን ተጠሪ ቤርብል ፍራየር ገልጸዋል። ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ፕሬዚደንት ቡሃሪ ፀረ ሙስና ኮሚቴ ያቋቋሙበትን ርምጃ አበረታቺ አድርጎ መቀበሉን የጀርመን ኮሜርስ ባንክ ኃላፊ ኦላፍ ሽሚውዘር አስታውቀዋል።
« ርምጃቸው አዎንታዊ አመለካከት አግኝቶዋል። ከከፍተኛ የዓለም አቀፉ የኤኮኖሚ ማህበረሰብ ኃላፊዎች ጋር ባካሄድኩት ውይይት ለመረዳት እንደቻልኩት፣ የቡሃሪ ርምጃ ፍሬ አስገኝቶ ዓለም አቀፍ ደረጃ የጠበቁ ውሎች ተፈርመዋል፣ ካሁን ቀደም ይደረግ እንደነበረው ገንዘብ መክፈል ሳያስፈልግ ማለት ነው። »
ለናይጀሪያ እና ምዕራብ አፍሪቃ በአሁኑ ጊዜ የባለወረቶችን ትኩረት አግኝተዋል። ጀርመናውያኑ ቤርብል ፍራየር እና ኦላፍ ሽሚውዘር ፕሬዚደንት ቡሃሪ እስከአውሮጳውያኑ 2015 መጨረሻ ጠንካራ ካቢኔ ያቋቁማሉ ብለው ይጠብቃሉ። ኦላፍ ሽሚውዘር እንደሚሉት፣ ባለወረቶች በሃገርሪቱ ምቹ እና አስተማማኝ የኤኮኖሚ ሁኔታ እንዲኖር ይፈልጋሉ። ይህንንም ቡሃሪ ጊዜ ወስደው የሚያቋቁሙት መንግሥት እንደሚያሟላ ተስፋቸውን ገልጸዋል።
አርያም ተክሌ
ልደት አበበ