1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የናይጀሪያ ጦር በቦኮ ሃራም ላይ የሰነዘረው ጥቃት

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 28 2007

የናይጀሪያ ጦር ሠራዊት በቦርኖ ግዛት፤ በቦኮ ሃራም ታግተዉ የነበሩ 101 ህፃናትን ማስለቀቁን ገለፀ። የሃገሪቱ የጦር እንደገለፀዉ ከማይዲጉሪ በስተሰሜን በምትገኘዉ አዉላሪ ከተማ አካባቢ የናይጀርያ ጦር ሠራዊት በከፈተዉ ጥቃት 67 ሴቶች 10 ወንዶች እንዲሁም 101 ህጻናትን በጠቅላላ 178 ሰዎች ከቦኮሃራም እጅ ነፃ ወጥተዋል።

https://p.dw.com/p/1G9U4
Nigeria Befreite Geiseln Boko Haram
ምስል picture-alliance/AP Photo/J. Ola

[No title]

የናይጀሪያ ጦር ሠራዊት በቦኮሃራም እጅ ታግተዉ የነበሩ ሰዎችን ያስለቀቀዉ ባለፈዉ እሁድ እንደሆነ ነዉ የተነገረዉ። ጦር ሰራዊቱ ትናንት ይፋ እንዳደረገዉ ከቦኮ ሃራም ነፃ የወጡት 178 ታጋቾች በጥሩ ጤና ላይ ይገኛሉ። የ 101 ዱ ታጋች ህፃናት ወላጆችም ልጆቻቸዉን ዳግም በእቅፋቸዉ ያስገባሉ። የጦር ሰራዊቱ ታጋቾቹን ከጽንፈኛዉ ቡድን ሲያስለቅ አንድ የቦኮሃራም ከፍተኛ አዛዥ በቁጥጥር ሥር መዋሉም ተመልክቶአል። ታጋቾችን ለማስለቀቅ በተደረገዉ ዉግያ በተለይ አባማ በተሰኘችዉ ከተማ ዙርያ በርካታ የቦኮ ሃራም የጦር መሳርያ ማካማቻ ቦታዎች ወድመዋል። የናይጄርያ የአየር ኃይል እንዳስታወቀዉ የሚሊዮኖች መኖርያ ከሆነችዉ ማዲጉሪ ከተማ 70 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘዉ «ቢታ» አካባቢ ጥቃቱን አስፋፍቶ በርካታ የቦኮ ሃራም ሃራም አባላት ገድሎአል። ቦኮሃራም በበኩሉ በናይጀሪያ ጦር ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረስኩ ነዉ ሲል በቪዲዮ የተደገፈ መረጃዉን ያሰራጨዉ። የናይጀሪያ ጦር የሕዝብ ግንኙነት ቢሮ ጊዜያዊ ዳይሬክተር ኮሎኔል ሳኒ ኩኩ ሼካ ዑስማን ግን ይህ ከፕሮፓጋንዳ ሌላ ፋይዳ የሌለዉ ወሪ ነዉ ያሉት።

«ቪዲዮዉ የአሸባሪ ፕሮፓጋንዳ ከመሆን የዘለለ ፋይዳ የለዉም። ቪዲዮዉን በጥንቃቄ የመመርመር አቅም ያለዉ በፊልሙ የተካተተዉ ሁሉ በቅርቡ የተከናወነ እንዳልሆነ መረዳት ይችላል። ለጥቃት አድራሾቹ ግልፅ ጥቅም ያለዉ ይመስል ይሆናል ነገር ግን የናይጀሪያ ጦር እና ተባባሪዎቹ የቦኮሃራም አሸባሪ ቡድን ጀሌዎች በናይጀሪያም ሆነ በተገኙበት በየትኛዉን ሀገር እንደሚያጠፋቸዉ ላረጋግጥ እወዳለሁ።»
ቦኮ ሃራም ቀደም ሲል ቦርኖ አዉራጃ በምትገኝዉ ማላራይ አነስተኛ መንደር ላይ ጥቃት ጥሎ ቢያንስ 13 ወጣቶች መገደላቸዉንና 30 የሚሆኑ ሰዎች መጎዳታቸዉ ተመልክቶአል። ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል አዣንስ ፍራንስ ፕሪስ የአይን እማኞች እንደገለጹት የቦኮሃራም አቀንቃኞች መኖርያ ቤቶችንና መደብሮችን በእሳት አጋይተዋል። ጽንፈኞቹ የብቀላ እርምጃ ላይ ናቸዉ፤ ሲሉ ከቦኮሃራም ጥቃት ያመለጡ አንዲት ገበሬ መናገራቸዉ ተዘግቦአል። እንደ ወጣትዋ ገበሪ፤ ጥቃት አድራሾቹ የት እንደተደበቅን ለናይጀርያ ጦር ኃይል ተናግራችኋል ሲሉ እንደሚከሱም ነዉ የገለፁት። የናይጀሪያ ጦር የሕዝብ ግንኙነት ቢሮ ጊዜያዊ ዳይሬክተር ኮሎኔል ሳኒ ኩኩ ሼካ ዑስማን እንደገለጹት የሃገሪቱ ጦር ሠራዊት ጽንፈኛዉን ቦኮሃራም ቡድን ከመሸገበት እየገባ እያደነ ነዉ።

« የናይጀርያ ጦር ሰራዊት ቦኮ ሃራም በየተሸሸገበት እያደነ ነዉ። ጦሩ አሸባሪ ቡድኑን እንደሚረታ ላረጋግጥ እወዳለሁ። እንደገና ለማስታወስ የምፈልገዉ ጉዳይ ሽብርተኛዉን ቡድን ለማደን የተዘጋጀዉ አካባቢዊ ጥምር ኃይል በናይጀርያም ሆነ በቻድ አካባቢዎች ብሎም በምዕራብ አፍሪቃ የትኛዉም አካባቢ የሚደበቅበት ቦታ አያገኝም።»
የናይጄርያ አዋሳኝ ሃገሮች በአካባቢያቸዉ የሚንቀሳቀሰዉን ጽንፈኛ ቡድን ቦኮ ሃራምን ለማደን ጥምረት መጀመራቸዉ ይታወቃል። ጽንፈኛዉ ቦኮ ሃራም በሰሜናዊ ናይጄርያ እስላማዊ መንግሥት እመሰርታለሁ በሚል ከስድስት ዓመት ጀምሮ ከፍተኛ ጥቃት እና አደጋ በተከታታይ በማድረስ ላይ መሆኑ ይታወቃል። እንደ ተመድ ገለጻ ቡድኑ እስካሁን በጣላቸዉ ጥቃቶች ከ 15 ሽህ በላይ ሰዎች ተገድለዋል። በያዝነዉ የጎርጎሮዮሳዊ ዓመት መጀመርያ ላይ ቦኮ ሃራም እራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ ለሚጠራዉ አሸባሪ ቡድን ወገናዊነቱን መግለጹ ይታወቃል።

Nigeria Armee rettet Mädchen Symbolbild
ምስል picture-alliance/dpa/H. Ikechukwu
Nigeria Flüchtlinge wegen der Offensive gegen Boko Haram
ምስል Reuters/A. Sotunde


አዜብ ታደሰ


ነጋሽ መሃመድ