1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

የኒውክለር ኃይል ማመንጫ ለኢትዮጵያ?

ረቡዕ፣ መጋቢት 12 2010

የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ አፍሪቃ በመጡ ወቅት  ሀገራቸው የኒውክለር ኃይልን ለሰላማዊ አገልግሎት ለመጠቀም ከሚፈልጉ ሀገራት ጋር በትብብር እንደምትሰራ መናገራቸው ይታወሳል፡፡ በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታም ሀገሪቱ የኒውክለር ተቋም ለመገንባት ከሩሲያ ጋር ስምምነት ላይ መድረሷን አስታውቀዋል፡፡

https://p.dw.com/p/2ujNA
Frankreich Kernkraftwerk Bugey
ምስል imago

የኒውክለር ኃይል ማመንጫ ለኢትዮጵያ?

የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ኢትዮጵያን ጨምሮ አምስት የአፍሪቃ ሀገራትን ከሁለት ሳምንት በፊት መጎብኘታቸው ይታወሳል፡፡ ሀገራቸውን ለ14 ዓመታት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ያገለገሉት ላቭሮቭ ወደ አፍሪካ ብቅ ያሉት የሩሲያን የንግድ እና የመከላከያ ጥቅሞች የማስጠበቅ አጀንዳ አንግበው ነበር፡፡ ሩሲያ በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያላትን ያካበተ ልምድ እና እውቀትን በመጠቀም ሀገሪቱ ቀደም ሲል የነበራትን ኃይልነት እና ተሰሚነት ለመመለስ የምትደርገውን ጥረትም ሲያሳኩ ተስተውለዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከኢትዮጵያ እስከ ናሚቢያ፣ ከሱዳን እስከ ጋና፣ ከታንዛንያ እስከ ደቡብ አፍሪካ ሀገራቸው እንደ መባ በተደጋጋሚ እያቀረበች ያለችው የኒውክለር ቴክኖሎጂ ነው፡፡ 

ላቭሮቭ ከኢትዮጵያ አቻቸው ከዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ጋር በሰጡት የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይም ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር ልትካሄድ ስለተስማማችበት የኒውክለር ፕሮጀክት ጉዳይ ጥያቄ ተነስቶላቸው ተከታዩን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ “በሩሲያ ዲዛይን በተደረገ እና ቀድሞም ባለ የምርምር ማብሊያ ላይ የተመረኮዘ የኒውክለር ቴክኖሎጂ ማዕከል ለመመስረት በኢትዮጵያ ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡ ስራውን በጥሩ ፍጥነት እየተካሄደ ነው፡፡ እስካሁን ይህ ነው የሚባል መጓተት የለም፡፡ በመንግስታት መካከል የሚያስፈልጉ ስምምነቶች ከተፈረሙ እና ከጸደቁ በኋላ እንደውም ይበልጥ ይፋጠናል” ብለው ነበር፡፡ኢትዮጵያ የአቶሚክ ኃይልን ለሰላማዊ ጥቅም ለመዋል ከሩሲያ ጋር የመግባቢያ ስምምነት የተፈራረመችው ላቭሮቭ ወደ አዲስ አበባ ከመምጣታቸው ዘጠኝ ወር በፊት ነው፡፡ ይህን የመግባቢያ ስምምነት ባለፈው ሰኔ ወር የፈጸሙት መንግስታዊው የሩሲያ የአቶሚክ ኃይል ኮርፖሬሽን (ROSATOM) እና የኢትዮጵያ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ኃላፊዎች ናቸው፡፡

Äthiopien Besuch russischer Außenminister Sergei Lawrow mit Workneh Gebeyehu
ምስል Reuters/T. Negeri

ላቭሮቭ በምላሻቸው ጠቆም ያደረጉት የኒውክለር ማብሊያ በሁለት እንደሚከፈል ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ የመጀመሪያው ለምርምር የሚውል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ለኃይል ማመንጫነት የሚያገልግል እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ በኢትዮጵያ ሩሲያ ሰራሽም ሆነ ከሌላ ሀገር የመጣ የምርምር ማብሊያ ይኖር እንደው በኢትዮጵያ ጨረራ መከላከል ባለስልጣን የማሳወቅና ፍቃድ አሰጣጥ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑትን አቶ ስሩር ከድርን ጠይቄያቸው ነበር፡፡ የምርምር ማብሊያ (research reactor) የሚባለው ለምን እንደሚያስፈልግ በማስረዳት ይጀምራሉ፡፡

“የምርምር ማብሊያ  ሲባል ዩኒቨርስቲዎች አካባቢ የተለያዩ ምርምሮች ለማካሄድ፣ በዩኒቨርስቲው አካባቢ ኒውክለር ፊዚክስ ለማስተማር ከፈለግህ ያስፈልግሃል፡፡ እንደዚሁ አነስተኛ መጠን ያላቸው ለኒውክለር ህክምና የሚያገለግሉ ዝቅተኛ የሆነ ጨረር ሊያመነጩ የሚችሉ ሬድዩ ኒውክላይዶች እስከዛሬ ድረስ ከውጭ ሀገር እየገቡ ነው ጥቅም ላይ የሚውሉት፡፡ እነዚህን በሀገር አቅም ማምረት የሚቻልበት ነገር እንዲፈጠር ይሄ የምርምር ማብሊያ ያስፈልጋል፡፡ የጥራት ጉዳይ አለ፡፡ የተለያዩ መሳሪያዎችን ጥራት ለመቆጣጠር፣ አለመበላሸታቸውን፣ ችግራቸውን ለማወቅ የምርምር ማብሊያ ያስፈልጋል፡፡ እንደዚሁም ደግሞ ለድረባ (calibration) አገልግሎት የሚውሉ የተለያዩ ምርምሮችን እና የተለያዩ ቁስ አካሎችን ባህሪ ለማወቅ የሚያስችል ነው፡፡ እስካሁን ድረስ ባለው ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ የምርምር ማብሊያ የለም፤ እስካሁንም በኢትዮጵያ ውስጥ ስራ ላይ አልዋለም” ይላሉ ዳይሬክተሩ።

በኢትዮጵያ ቁጥራቸው በየጊዜው እየጨመሩ ያሉት ዩኒቨርስቲዎች የሀገሪቱን ችግር ሊቀርፉ የሚችሉ ምርምሮችን በተናጠል እና በጋራ ማካሄድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የምርምር ማብሊያ ለእንደዚህ አይነት ምርምሮች ጠቃሚ እንደሆነ አቶ ስሩር ይናገራሉ፡፡ በምርምር ማብሊያ ጀምሮ ኃይል ለማመንጨት ጥቅም ላይ ወደሚውለው ማብሊያ በቀላሉ መሸጋገር እንደሚቻልም ያስረዳሉ፡፡ አነስተኛ የኒውክለር ኃይል ማብሊያ ለመገንባት እየተንቀሳቀሰች ያለችው ሱዳን ይህን የባለሙያውን አካሄድ የተከተለች ይመስላል፡፡ ከማብሊያው ለጥቆ የኒውክለር የኃይል ማመንጫ ተቋሙን ለመገንባት የያዘችው የጊዜ ገደብ ስምንት ዓመት ነው፡፡  

Tschechien Kernkraftwerk Temelin
ምስል Getty Images

የካናዳ ኒውክለር ማህበር ባወጣው መረጃ መሰረት በጎርጎሮሳዊው 2017 በዓለም ላይ ያሉ የኒውክለር የኃይል ማብሊያዎች ቁጥር 446 የደረሰ ሲሆን 60 ተመሳሳይ ተቋማት ደግሞ በግንባታ ላይ ነበሩ፡፡ በዚያው ዓመት በዓለም አቀፍ ደረጃ 168 ተጨማሪ ማብሊያዎች ለመገንባት በእቅድ ሲያዙ የ345 ተቋማት ግንባታ ደግሞ በሀሳብ ደረጃ ቀርቧል፡፡ አሁን አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ የኒውክለር ማብሊያዎች ከዓለም አቀፉ የኤሌክትሪክ ኃይል 11.5 በመቶውን እንደሚሸፍኑ የማህበሩ መረጃ ያመለክታል፡፡ 

ኢትዮጵያ አሁን ከምታመነጨው 2421 ሜጋ ዋት ውስጥ አብዛኛውን የኃይል ፍላጎቷን የምታገኘው በውሃ ግድቦች ላይ ከተመሰረቱ የኃይል ማመንጫዎች እንደሆነ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ተቋም አሃዞች ያመለክታሉ፡፡ ሀገሪቱ በሁለተኛው የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ማጠናቀቂያ ተጨማሪ 17 ሺህ ሜጋ ዋት ለማመንጨት በእቅድ አስቀምጣለች፡፡ የእዚህ እቅዷ ዋነኛ ምስሶ በአባይ ወንዝ ላይ በመገንባት ላይ ያለው እና 6450 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም የሚኖረው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ትኩረቷን በውሃ ኃይል ማመንጫ ላይ አድርጋ ሳለ የኒውክለር ኃይል ማመንጫን መመኘቷ ስለምን ነው? ሲሉ የሚጠይቁ አሉ፡፡ አቶ ስሩር ምላሽ አላቸው፡፡ 

“የእኛ ያው በጣም ብዙ ሚሊዮን ህዝብ ያለው፣ ብዙ የቆዳ ሰፋት ያለው ሀገር ነው፡፡ ወደፊት ደግሞ ከህዝባችን ቁጥር፣ ከዚህ ከቴክኖሎጂው ዕድገት፣ ዕድገትንም ከማፋጠን አኳያ በተለይ ኃይል በጣም ወሳኝ ነገር ነው፡፡ በተለይ ዕድገትን ቀጣይ ከማድረግ አኳያ ምንም ዓይነት የኃይል ቀውስ ሊያጋጥም አይገባም ፡፡ ስለዚህ ወደፊት ይበልጥ ወደ ኢንዱስትሪያላዜሽን እየተሸጋገርን በምንሄድበት ሰዓት ብዙ ዓይነት የኃይል አማራጮች ሊኖሩን ይገባል፡፡ በተለይ ነገ ሊከሰት የሚችል ለምሳሌ የአየር መዛባት የመሳሰሉ ነገሮችን በዚያ ላይ ጥገኛ ያልሆነ፣ አስተማማኝ የሆነ፣ አረንጓዴ የሆነ አካባቢን ሊበክል የማይችል የኃይል አማራጭ መኖሩ ጥሩ ነው የሚል ነገር ነው ያለኝ” ይላሉ። አካባቢን ከማይበክሉ የኃይል አማራጮች አንዱ የሆነው የኒውክለር ኃይል ከምን እና እንዴት ነው የሚገኘው? በኦስትሪያ ቬይና በሚገኘው ዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ የኒውክለር ኃይል ተቆጣጣሪ ባለሙያ ዶ/ር ተሾመ ባዩ ማብራሪያ አላቸው፡፡ አንድ ሀገር የኒውክለር ኃይል ማመንጫ ለመመስረት የግዴታ የኒውክለር ማብሊያ መገንባት እንደማይጠበቅባትም ዶ/ር ተሾመ ይናገራሉ፡፡  

NO FLASH Fahne Logo IAEO IAEA
ምስል picture-alliance/dpa/dpaweb

በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ የአፕላይድ ኬምስትሪ መምህር የሆኑት ዶ/ር ታጁዲን ያህያ የኒውክለር ኃይል ማመንጫ በኢትዮጵያ መገንባቱ ለሀገሪቱ ይጠቅማል ብለው ያምናሉ፡፡ ሆኖም ወደ ግንባታው ከመኬዱ በፈት መደረግ ያለባቸው ቅደመ ሁኔታዎች አሉ ባይ ናቸው፡፡

ሙሉ መሰናዶውን የድምጽ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ። 

ተስፋለም ወልደየስ

ኂሩት መለሰ