1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቶኒ ብሌር የሊቢያ ጉብኝት

ዓርብ፣ መጋቢት 17 1996

የብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር ቶኒ ብሌር ትናንት በሊቢያ ከሀገሪቱ መሪ ሞአመር ኤል ጋዳፊ ጋር ተገናኝተዋል። ከቀድሞው የብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር ዊንስተን ቸርችል ወዲህ አንድ የብሪታንያ መሪ ሊብያን ሲጎበኝ ብሌር የመጀመሪያው ናቸው። ብሌር በዚሁ ብሪታንያውያኑ ታሪካዊ ባሉት ጉብኝታቸው በራስዋ ጥፋት ከዓለም የፖለቲካ መድረክ ተገልላ የቆየችው ሰሜን አፍሪቃዊቱ ሀገር ሊብያ እንደገና ወደ ዓለም አቀፉ ኅብረተ ሰብ እንደተመለሰች አረጋግጠዋል። ይኸው ሂደት

https://p.dw.com/p/E0l6

ም ምዕራባውያኑ ለረጅም ጊዜ ሳይሰለቹ ያካሄዱት ቀላል ያልነበረው ድርድር ውጤት ነው።

የቶኒ ብሌር የሊብያ ጉብኝት ታሪካዊ እንደሆኑ ብሪታንያውያኑ ይናገራሉ። ቸርችል በኤርዊን ሮመል የአፍሪቃ ጓድ አንፃር ድል የተቀዳጀውን የብሪታንያ ጦር እአአ በ 1943 ዓም በሊብያ ከጎበኙ ወዲህ አንድም የብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር ሊብያን ጎብኝቶ አያውቅም። የዩኤስ አሜሪካ ፕሬዚደንት ጆርጅ ዳብልዩ ቡሽ የሚመሩት መስተዳድር በኢራቅ አንፃር የወሰደው ቁርጥ ርምጃ የትሪፖሊን አመራር አስተሳሰብ እንዳስቀየረ፡ በሀገሩ የፊታችን ጥቅምት ለሚካሄደው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ዘመቻ እንዲያመቸው በማሰብ፡ ከመግለፅ ወደ ኋላ ባይልም ገሀዱ ሌላ ነው። እንደሚታወቀው፡ ሊብያ በቀድሞው የዩኤስ አሜሪካ ፕሬዚደንት ቢል ክሊንተን ሁለተኛ የሥልጣን ዘመን ነበር ዋሽንግተን በሀገርዋ ላይ ያሳረፈችውን ማዕቀብ ካነሣችላት የአቶም መርሐ ግብርዋንና የመርዘኛ ንጥረ ነገር፡ እንዲሁም ከጥቃቅን ነፍሳት የተሠሩ የጦር መሣሪያዎችን ለመደምሰስ ዝግጁነትዋን የገለፀችው። በዚሁም ጊዜ ክሊንተን ሊብያ በሎከርቢ ስኮትላንድ ላይ ሲበር የቮምብ ጥቃት ተጥሎበት በተከሰከሰው የፓናም አይሮፕላን የሞቱት ሰዎች ጉዳይ መልስ እንዲያገኝ ቅድመ ግዴታ ማሳረፋቸው ይታወሳል። ሊብያም ለጥቃቱ ኃላፊነቱን በመውሰድ፡ ሁለት ተጠርጣሪ ዜጎችዋን ለፍርድ እንዲቀርቡ ካደረገች በኋላ፡ አንዱ በነፃ ተለቆዋል፤ ለጥቃቱ ሰለባዎች ቤተ ዘመዶችም ሁለት ነጥብ ሰባት ሚልያርድ ዶላር፡ ማለትም፡ ለያንዳንዱ ሟች ቤተሰብ አሥር ሚልዮን ዶላው ካሣ ከፍላለች። አሁን ብሌር ጋዳፊን በጎበኙበት ድርጊት የሊቢያው መሪ እንደገና በዓለም ፖለቲካ ላይ ተሰሚነት አግኝተዋል። የስድሳ ሁለት ዓመቱ ጋዳፊ ጅምላ ጨራሹን የጦር መሣሪያ ለመደምሰስ እና ለአሸባሪዎቹ ቡድኖችም ድጋፍ መስጠታቸውን እንደሚያቋርጡ በይፋ ላስታወቁበት ድርጊት አሁን ፍሬውን መሰብሰብ ጀምረዋል።
ለንደንና በተለይ ዋሽንግተን ሊረሡት የማይገባ ጉዳይ ቢኖር፡ የሊብያ መንግሥት የአቶም መርሐ ግብርዋንና የመርዘኛ ንጥረ ነገር፡ እንዲሁም ከጥቃቅን ነፍሳት የተሠሩ የጦር መሣሪያዎችን ለመደምሰስ ዝግጁነቱን የገለፀው፡ ቡሽ በተከተሉት የመካከለኛው ምሥራቅ ፖለቲካ ወይም የጦር ዛቻን በመፍራት ሰበብ ሳይሆን፡ የተ መ ድ እና ዩኤስ አሜሪካ ያሳረፉባት መራራው የኤኮኖሚ ማዕቀብ ባደረሰባት ጉዳትና፡ ምዕራባውያቱ ሀገሮች ባካሄዱት ቀላል ያልነበረው ድርድር የተነሣ መሆኑን ነው። ይህም ብሪታንያና ዩኤስ አሜሪካ ቡሽ እኩይ ካሉዋት ሊብያ ጋር ያደረጉት ድርድር እኩይ በሚሉዋት ሌላዋ ሀገር ኢራቅ አንፃር የተከተሉት የጦር ርምጃ የሚመረጥ ሆኖ መገኘቱን አሳይቶዋል።