1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

ከአንድ አመት በኋላ ወደ 27 ሚሊዮን ስልኮች ከአገልግሎት ይወጣሉ

ረቡዕ፣ መስከረም 10 2010

የኢትዮጵያ መንግሥት ከአንድ አመት በኋላ «ጥራታቸውን ያልጠበቁ» የሚላቸዉን የተንቀሳቃሽ ስልኮች ከአገልግሎት ውጪ ሊያደርግ መዘጋጀቱን አስታውቋል። እርምጃው በኢትዮጵያ ተንቀሳቃሽ ስልኮች ለሚገጣጥሙ ኩባንያዎች እና አስመጪዎች በጎ ዜና ቢሆንም በደንበኞች ላይ ጫና ሊያሳድር ይችላል የሚል ሥጋት ማሳደሩ አልቀረም። 

https://p.dw.com/p/2kOk1
Mobiltelefon Nokia 3310
ምስል picture alliance/dpa/Lehtikuva/M. Airio

27 ሚሊዮን ስልኮች ከአገልግሎት ውጪ ይሆናሉ

ወደ 58 ሚሊዮን ገደማ የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚዎች ያሏት ኢትዮጵያ በአንድ አመት ውስጥ 2.7 ሚሊዮን የቴሌኮም መሳሪያዎችን ከአገልግሎት ውጪ ልታደርግ ተዘጋጅታለች።በሐገሪቱ  ብቸኛው አገልግሎት ሰጪ ኢትዮ-ቴሌኮም ከአገልግሎት ውጪ የሚሆኑት ቀረጥ ያልተከፈለባቸው፤ ከደረጃ በታች የሆኑ እና የጤና ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉት ናቸው ብሏል። ኢትዮ-ቴሌኮም እና የመገናኛ እና ኢንፎርሜሽን ሚኒሥቴር በጥምረት  እርምጃውን ተግባራዊ የሚያደርጉት ተንቀሳቃሽ ስልኮችን ጨምሮ የቴሌኮም መገልገያ ቁሳቁሶች የተሰጣቸው መለያ ቁጥር በመመዝገብ ነው። 

ዓለም አቀፍ የሞባይል መለያ ምዝገባ በእርግጥ ለኢትዮጵያ አዲስ ይሁን እንጂ አገልግሎት አቅራቢዎች የደንበኞቻቸውን አጠቃቀም የሚከታተሉበት መንገድ ሆኖ ቆይቷል። ደንበኞች ተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው ቢጠፉ አሊያም ቢሰረቁ የመለያ ቁጥሮች ያሉበትን ለመለየት ያስችላሉ። የቀድሞው የኢትዮ-ቴሌኮም ባልደረባ አቶ ፋሲል ነጋሽ የተንቀሳቃሽ ስልክ መለያ ቁጥሮች አገልግሎት አቅራቢዎች የደንበኞቻቸውን አጠቃቀም የመቆጣጠር ሥልጣን እንደሚሰጣቸው ይናገራሉ። 

ምዝገባው በኢትዮጵያ የተንቀሳቃሽ ስልኮችን ለሚገጣጥሙት 14 ኩባንያዎች እና አስመጪዎች የምስራች ዜና ይመስላል። ገበያው ግን ዛሬም ከኮንትሮባንድ ንግድ ጋር እየተናነቀ ነው። ባለፈው አመት የኩባንያዎቹ ማኅበር ይፋ ባደረገው ዘገባ ወደ በኢትዮጵያ ገበያ ከሚሸጠው ተንቀሳቃሽ ስልክ 65 በመቶው ከጎረቤት አገራት በሕገ-ወጥ መንገድ የገባ ነው ሲል አትቶ ነበር። የኢትዮጵያ ገቢዎች እና ጉሙሩክ ባለሥልጣን በበኩሉ በ2009 ዓ.ም. የመጀመሪያ ስድስት ወራት 83 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ ሕገ-ወጥ ተንቀሳቃሽ ስልኮችን መያዙን ገልጧል። አቶ ብሩክ እንደሚሉት ገበያው አሁንም ከሕገ-ወጥ የተንቀሳቃሽ ስልክ ንግድ እምብዛም አላገገመም። 
ኢትዮ ቴሌኮም የተንቀሳቃሽ ስልኮች ምዝገባው "በሚታወቁ እና ህጋዊ በሆነ መንገድ ሥራቸውን በሚያከናውኑ አስመጪዎችና አምራቾች መካከል ጤናማ የሆነ ውድድር እንዲኖር ያስችላል" የሚል እምነት አድርበታል። አዲስ አበባ ላይ በተሰጠው ጋዜጣ መግለጫ አቶ ባልቻ ሬባ አሁን ተግባራዊ የሚደረገው እርምጃ ተመሳስለው የተሰሩትን ከትክክለኛ ስልኮች ለይቶ ለማገድ ያግዛል ሲሉ ተናግረዋል። 

እሸቴ በቀለ
ነጋሽ መሐመድ