1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቱርክ የሶሪያ ወታደራዊ ዘመቻ

ሰኞ፣ ጥቅምት 3 2012

ቱርክ ባለፈው ሳምንት አጋማሽ በሰሜን ምስራቅ ሶሪያ ወታደራዊ ዘመቻ ከፍታለች። ሀገሪቱ በአካባቢው ጥቃት መሰንዘር የጀመረችው በሰሜን ምስራቅ ሶሪያ ለመመስረት ያቀደችውን “ደህንነቱ የተጠበቀ ቀጠናን” በስፍራው ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎች ለማስለቀቅ በሚል ነው። 

https://p.dw.com/p/3RH2k
Frankreich Proteste in Paris gegen der türkischen Militäroffensive in Nordsyrien
ምስል picture-alliance/AP Photo/F. Mori

የቱርክ የሶሪያ ወታደራዊ ዘመቻ አንድምታ

የዶይቼ ቬለ ዋና መስሪያ ቤት የሚገኝባት የጀርመኗ ቦን ከተማ ባለፈው ሐሙስ መስከረም 29 ሰላማዊ ሰልፈኞች በሚያሰሟቸው መፈክሮች  ደምቃ ነበር ያመሸችው። ከሰልፈኞቹ አንደበት ተደጋግሞ የሚሰማው “ኩርዲስታን” የሚለው ቃል እና የያዟቸው ባንዲራዎች የተቃዋሚዎቹን ማንነት ይጠቁማሉ። ገሚሶቹ ሰልፈኞች መሃሉ ላይ ሃያ አንድ ቢጫ የጸሀይ ጨረሮች ያሉበትን ቀይ፣ ነጭ እና  አረንጓዴ የኩርዶችን የነጻነት ባንዲራ ያውለበልባሉ። ሌሎቹ ደግሞ በሰሜን ምስራቅ ሶሪያ የሚንቀሳቀስን የኩርድ ፓርቲ ባንዲራ አንግበዋል። ሰልፈኞቹ በተደጋጋሚ ቱርክን እና የሀገሪቱን ፕሬዝዳንት ራጂብ ጣይብ ኤርዶኻንን በመራር ቃላት ያወግዛሉ። 

የቦን ከተማ ሰልፈኞች ኤርዶ ኤርዶኻንን “ፋሺስት አሸባሪ እና የህጻናት ገዳይ” በሚል ቅጥያዎች እንዲያወግዙ ያደረጋቸው ቱርክ ሰልፍ ከመውጣታቸው ከአንድ ቀን በፊት በሰሜን ምስራቅ ሶሪያ ላይ የከፈተችው ወታደራዊ ዘመቻ ነው። ቱርክ በአካባቢው ጥቃት መሰንዘር የጀመረችው በሰሜን ምስራቅ ሶሪያ ለመመስረት ያቀደችውን “ደህንነቱ የተጠበቀ ቀጠናን” በስፍራው ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎች ለማስለቀቅ በሚል ነው።ይህ ቀጠና ከሶሪያ ጋር የሚዋስናትን 480 ኪሎ ሜትር ድንበርን የሚያካልል እና እስከ 32 ኪሎ ሜትር ድረስ ተሻግሮ የሚቋቋም እንደሆነ ቱርክ አሳውቃለች። ቱርክ በዚህ ቀጠና ከተለያዩ የሶሪያ ክፍሎች ተሰድደው በሀገሯ ከሚገኙ 3.6 ሚሊዮን ሶሪያውያን ስደተኞች ውስጥ አንድ ሚሊዮን ያህሉን የማስፈር እቅድ አላት። ቱርክ ስደተኞቹን ለማስፈር የምትፈልግበትን ቦታ አሁን በዋናነት ተቆጣጥረው የሚገኙት ደግሞ የኩርድ ሚሊሺያዎች ናቸው።

Syrien Region Manbidsch Türkei M60 Panzer
ምስል AFP/A. Tammawi

በምህጻሩ YPG ተብሎ የሚጠራው ይህ የሚሊሺያዎች ቡድን በሶሪያ ለሚገኙ ሁለት ሚሊዮን ለሚጠጉ ኩርዳውያን መብት የሚታገል ድርጅት ነው። ቡድኑ የሶሪያ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ከተሰኙ የአረብ ሚሊሺያዎች ጋር የዛሬ አራት ዓመት ጥምረት ከፈጠረ ወዲህ ይበልጥ ጡንቻውን አፈርጥሟል። ስድሳ ሺህ ከሚገመቱት የሶሪያ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ተዋጊዎች ውስጥ አብዛኞቹ የዚህ ቡድን አባላት እንደሆኑ ይነገራል። በሶሪያ ከሚገኙ ኩርዶች ውስጥ ግማሽ ያህሉ የሚኖሩት በእነዚህ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ባለው የሰሜን ምስራቅ ሶሪያ አካባቢዎች ነው።

የኩርዶች መጠናከር ሁሌም የሚባትታት ቱርክ የYPGን እንቅስቃሴ በአይነ ቁራኛ ስትከታተል ቆይታለች። ባለፉት ሶስት ዓመታት  የሶሪያ ኩርዶችን ኢላማ ያደረጉ ወታደራዊ ዘመቻዎችን ከአንድም ሁለት ጊዜ አድርጋለች። ቱርክ ባለፈው ሳምንት የከፈተችው ወታደራዊ ዘመቻ ዓላማ ለሶሪያውን ስደተኞች የሚሆን “ደህንነቱ የተጠበቀ ቀጠና መፍጠር ነው” ብትልም ዋነኛ ኢላማዋ ግን የኩርድ አማጽያን እንደሆኑ በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች ሲገልጹ ሰንብተዋል። በቱርክ የማህበረሰብ ሳይንስ ዩኒቨርስቲ የሚያስተምሩት የፖለቲካ ተንታኙ ዶ/ር ሙከርም ሚፍታህም ይህንኑ ያጠናክራሉ። 

Syrien | SDS Kämpfer
ምስል picture-alliance/dpa/Le Pictorium/MAXPPP/C. Huby

የYPG ተዋጊዎች የበላይነቱን የያዙበት የሶሪያ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች የአሜሪካ የጸረ ሽብር ውጊያ ዋነኛ አጋር ነበር። አሜሪካ በሶሪያ የሚንቀሳቀሰው እና ራሱን እስላማዊ መንግስት (ISIS) ብሎ የሚጠራውን ታጣቂ ቡድን ለመደምሰስ ከፍታው በነበረው ውጊያ ዋነኛውን ሚና ሲጫወቱ የቆዩት የኩርድ ሚሊሽያዎች ነበሩ። በየሀገራቱ የውስጥ ፖለቲካ ላይ ረጅም እጇን ታስገባለች የምትባለው አሜሪካ ሶሪያን ጨምሮ በአራት የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ተበትነው የሚኖሩትን ኩርዳውያኑን ለዚሁ ዓላማ ትጠቀምባቸው ነበር የሚሉ የፖለቲካ ተንታኞች አሉ። ዶ/ር ሙከርም ከዚህ ጋር የሚመሳሰል አስተያየት አላቸው።  

ቱርክ የአሜሪካ አጋር የነበሩት የኩርድ ሚሊሺያዎች ላይ ዘመቻ ለመክፈት የተነሳችው ከራሷ አሜሪካ ባገኘችው "የአይዞሽ ባይነት" ምልክት ነው የሚሉ የፖለቲካ ታዛቢዎች አሉ። በሶሪያ ሰፍረው የነበሩትን ወታደሮቿን እንደምታስወጣ ስታስታወቅ የቆየችው አሜሪካ በዚህ ሳምንት ቃሏን ወደ ተግባር መቀየሯን ለዚህ በማሳያነት ይጠቅሳሉ። አሜሪካ አካባቢውን ለቅቃ ለመውጣት የወሰነችበት ምክንያት ምን እንደሆነ የፖለቲካ ተንታኙ ያብራራሉ። 

አሜሪካ አካባቢውን ለቅቃ ስትወጣ እነርሱ ይሰሩ የነበሩትን ወታደራዊውንም ሆነ ሰላም የማስፈኑን ስራ ቱርኮች በኃላፊነት እንዲወጡ ከስምምነት ላይ ደርሰው ነው ይላሉ ዶ/ር ሙከርም። ዩናይትድ ስቴትስ ቦታውን ለቱርክ ስትተው በአሜሪካ ሲደገፉ የቆዩት የኩርድ ሚሊሺያዎች ክህደት እንደተፈጸመባቸው ተሰምቷቸዋል። ዶ/ር ሙከርም ይህ የአሜሪካ እርምጃ በሌሎች ዘንድም ነቀፋ አስከትሏል ይላሉ።  

ቱርክ በሰሜን ምስራቅ ሶሪያ እያካሄደች ያለችውን ወታደራዊ ዘመቻ ለመረዳት በቱርኮች እና ኩርዶች መካከል ያለውን ትስስር ከስር መሰረቱ መመልከት እንደሚያስፈልግ የፖለቲካ ተንታኙ ያስረዳሉ። ለአምስት ዓመታት በቱርክ የኖሩት ዶ/ር ሙከርም በአካል ያስተዋሉትን ልዩነት ይገልጹታል። ምንም እንኳ የቱርክ ወታደራዊ ዘመቻ ዋና ዓላማ የኩርድ ሚሊሺያዎችን ማጥቃት ነው ቢባልም ሀገሪቱ በይፋዊ ምክንያትነት ያስቀመጠችው የሶሪያ ስደተኞች ጉዳይም እንዲሁ ዝም ብሎ የሚታለፍ ጉዳይ እንዳልሆነ የፖለቲካ ተንታኙ ያብራራሉ። ከሶስት ሚሊዮን በላይ የሶሪያ ስደተኞችን ባስጠለለችው ቱርክ ስደተኞች የፈጠሩት ጫና ከመኖሪያ ቤት ኪራይ መወደድ አንስቶ እስከ ኢ-መደበኛ የኢኮኖሚውን ዘርፍ መቀራመት ድረስ በጉልህ እንደሚታይ ያስረዳሉ። 

Syrien l Militäroffensive der Türkei in der Grenzstadt in Akcakale
ምስል Reuters/M. Sezer

ቱርክ የሶሪያ ስደተኞችን ጉዳይ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብን "ለማስፈራራት" ስትጠቀምበት ቆይታለች። ሀገሪቱ በሶሪያ ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ስትከፍት ያጋጠማትን አይነት ተቃውሞ ለመከላከል ያስጠለለቻቸውን ስደተኞች በገፍ ወደ አውሮፓ እንዲሄዱ እንደምትፈቅድ በመዛት እጅ ለመጠመዘዝ ትሞክራለች። ይህን ያስተዋሉት ዶ/ር ሙከርም የስደተኞች ጉዳይ ዓለም አቀፉን ማህብረሰብ "አጣብቂኝ ላይ ጥሏል" ይላሉ። 

ሙሉ መሰናዶውን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ። 

ተስፋለም ወልደየስ 
አዜብ ታደሰ