1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተዘረፉ የአፍሪቃ ቅርሶችን ለመመለስ ያለዉ ፍለጎት እስከምን?

ዓርብ፣ ጥር 3 2011

ቅርስ የሚዘረፍበት ዋናዉ ምክንያት አንገት ለማስደፋት ነዉ። የአንድን ሃገር ቅርስ ታሪክ ሲዘረፍ፤ የራሱ የሆነዉ አሻራ ሲወሰድ የኔነዉ የሚለዉ ነገር እንዲያጣ ይደረጋል። በዚህ ምክንያት ነዉ በቅኝ ግዛት ዘመን የተዘረፉ የአፍሪቃ ቅርሶች መመለስ አለባቸዉ። ይህ አይነቱ ዘረፋ ራሱን የቻለ የሥነ ልቦና ጦርነት ነዉ።

https://p.dw.com/p/3BItO
Das Victoria und Albert Museum, in dem äthiopische Raubschätze ausgestellt wurden, feiert den äthiopischen Tag
ምስል DW/H.Demissie

«ቅርስ ዘረፋ ራሱን የቻለ የሥነ-ልቦና ጦርነት ነዉ»

ቅርስ የአንድን ሃገር ታሪክን ባህልን ጠንቅቆ ወይም አቅፎ ከዘመን ዘመን የሚያሸጋግር ሰነድ ነዉ። ይህ ሰነድ ቅርሱ በተገኘበት ሃገር የሚኖር ማኅበረሰብ፤ ዋጋ የከፈለበት የታሪክ የባህሉ አሻራም ነዉ ይላሉ በለንደን የኢትዮጵያ ቅርፅ ማበልጸግያ ማኅበር ሊቀመንበር አቶ አለባቸዉ ደሳለኝ።  አቶ ደሳለኝ ቅርስን መዝረፍ ራሱን የቻለ የሥነ-ልቦና ጦርነት ነዉም ይሉታል።

«ቅርስ የሚዘረፍበት ዋናዉ ምክንያቱ አንገት ለማስደፋት ነዉ። የአንድን ሃገር ቅርሱ ታሪኩ ሲዘረፍ፤ የራሱ የሆነዉ አሻራ ሲወሰድበት የኔነዉ የሚለዉ ነገር እንዲያጣ ነዉ የሚያደርጉት። በዚህ ምክንያት ነዉ ቅርስን በተለይም አዉሮጳ ያደርጉት ከነበረዉ አስከፊዉ የቅኝ ግዛት ዘመን ዘርፈዋቸዉ የተመለሱት ቅርሶች በሙሉ የማኅበረሰቡን ታሪክ ቅርስ እና የማንነት መገለጫን ለልጅ ልጆች እንዳያሳዩ እንዳያሳዉቋቸዉ ባዶ እንዲሆን የሚያደርጉበት ራሱን የቻለ የሥነ ልቦና ጦርነት ነዉ።»   

BG Afrikanische Raubkunst | Ausstellung «Narren, Künstler, Heilige - Lob der Torheit» | Kraftfigur aus dem Kongo
ምስል picture-alliance/dpa/O. Berg

ምዕራባዉያኑ ሃገራት የሚያራምዱት ፖሊስም ሆነ ፖለቲካ የተዘረፉ የአፍሪቃ ጥንታዊ ቅርሶችን ወደ የሃገራቱ ለመመለስ የሚያስችል ይሆን?      

በቅኝ ግዛት ዘመን ምዕራባዉያን ሃገራት የዘረፍዋቸዉን ጥንታዊ ቅርሶች እንዲመልሱ የተለያዩ አፍሪቃ ሃገራት መወትወት ከጀመሩ ዓመታቶች ተቆጥረዋል። እንደ ፈረንሳይ ጀርመን የመሳሰሉት የቀድሞ ቅኝ ገዢ ሃገሮች በቅኝ ግዛት ዘመን ከአፍሪቃ ሃገራት የወሰድዋቸዉ ጥንታዊ እና ታሪካዊ ቅርሶችን ለመመለስ የሚካሄደዉ ዉይይት እና ክርክር በየሃገራቱ የባህል እና የፖለቲካ ተጠሪዎች ጋር ደርሶ ጉዳዩ መፍትሄ ለማግኘት መንገድን የያዘ ይመስላል። ባለፈዉ የጎርጎረሳዉያን ዓመት መገባደጃ ላይ ሁለት የቅርስ ጉዳይ ተመራማሪ ፈረንሳዉያን በፈረንሳይ የሚገኙ እና በሽዎች የሚቆጠሩ የአፍሪቃዉያን ጥንታዊ ቅርሶች ወደ አፍሪቃ ሃገራት ቤተ- መዘክር እንዲመለሱ የሚመክር ባለ 108 ገፅ ጥናታዊ ጽሑፍ ይፋ ካደረጉ በኋላ፤ የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኤማኑኤል ማክሮ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት በተለይ ከቤኒን የተዘረፉ ጥንታዊ ቅርሶች እንዲመለሱ ቁርጠኝነታቸዉን አሳይተዋል።

በለንደን የኢትዮጵያ ቅርፅ ማበልጸግያ ማኅበር ሊቀመንበር አቶ አለባቸዉ ደሳለኝ ፕሬዚዳንት ኤማኑኤል ማክሮ የተዘረፉ ቅርሶችን ለመመለስ ቀና አስተሳስብ ይዘዉ በመነሳታቸዉ አደንቃለሁ ብለዋል። አፍሪቃዉያኑ ሃገራት የተዘረፉ ቅርሶቻችንን መልሱ ብለዉ ከወተወቱ ሳይወዱ በግድ ይመልሳሉም ሲሉ አቶ አለባቸዉ አክለዋል።     

Raubkunst? Die Bronzen aus Benin Ausstellung Hamburg
ምስል Museum für Kunst und Gewerbe Hamburg

«የሃገር መሪዎች የሃገር ማኅበረሰብ ለራሳቸዉ ዋጋ ሰጥተዉ ቅርሳችን ታሪካችን መለያችን ብለዉ ከተነሱ ተቆርቋሪ እንዳለዉ ካወቁ ሳይወዱ በግድ ይመልሳሉ። ቅርስ ተቆርቋሪ ከሌለዉ ግን ደንታ የላቸዉም ። ሙዚየማቸዉን የሚያሸበርቁበት ቱሪዝምን የሚሰበስቡበት አንዱ የገቢ ምንቻቸዉ ነዉ። ስለዚህ ስለዚያች ሃገር የሚያስቡት ምንም ነገር የለም። ዋጋ የምንሰጠዉ ልንከፍል የምንችለዉ እና ነን። በተለያዩ መንግሥታትም ረገድ ያየን እንደሆነ ሩጫዉ ፖለቲካዉ ላይ ነዉ። ታሪክ ላይ ማንም የለም። በታሪክ የሚገኝዉን ጠቀሚታ ገና ዓይናችንን አይገለጥንም። ለምን እንደሆን በዚህ ጉዳይ ላይ በጣም ያሳዝነኛል። ለምሳሌy እኔ 20 ዓመት ሙሉ ከኢትዮጵያ ተዘርፈዉ ወደ ብሪታንያ የገቡ ብዙ የኢትዮጵያን ቅርሶች እና ታሪክ ሰብስብያለሁ። አንድ ሰዉ እንኳ ስለቅርስ ስለታሪክ ያነጋገረኝ ሰዉ የለም። »   

በጀርመን የሚገኝ የአፍሪቃ ሃገራትን ቅርሶች መመለስ የሚለዉ ጥያቄ እስካሁን እንብዛም ትኩረት ያገኘ አይመስልም። በሰሜናዊ ጀርመን ሃምቡርግ ከተማ የሚገኙት የባህል ጉዳይ ምክር ቤት አባል ካርስቴን ብሮስዳ እንደገለፁት እስከ መጭዉ መጋቢት ወር ድረስ በጀርመን ግዛቶች እና አካባቢዎች የተዘረፉ ቅርሶች በተመለከተ የጋራ ጥናት እና መግለጫ ይፋ ለማድረግ እንደሚፈልጉ ተገልፆአል።  ጀርመን በያዝነዉ የጎርጎረሳዉያን 2019 በፕሩሻን ቅኝ አገዛዝ ዘመን የተፈራረመችዉን ዉል አንድ መቶ ዓመት ማለት አንድ ክፍለ ዘመን በመሙላቱ የዉሉን ተቀባይነት ታጣለች። በዚህም በመጭዉ መስከረም በርሊን ላይ ጀርመን ቅኝ ግዛት በነበረች በት ዘመን በአፍሪቃ የተገኙ ቅርሶችን ጨምሮ የሚታይበት አንድ ቋሚ ዓዉደርዕይ ለጎብኝዎች በይፋ ይከፈታል።

ይህ ቤተ መዘክር  ለሕዝብ እይታ ይፋ ሊሆን ጊዜዉ እየተቃረበ ባለበት በአሁኑ ወቅት የጀርመን የባህል ሚኒስትር ሞኒካ ግሩተርስ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶችን ለመመለስ ትርጉም ያለዉ ለዉጥ እንደሚካሄድ አመላክተዋል። የጀርመን ባህል ሚኒስትር በያዝነዉ የጎርጎረሳዉያን 2019 መጀመርያ እንደተናገሩት ፤ « የቅርሶቹ ባለቤቶች ቅርሶቹን መልሱልን ብለዉ እስኪጠይቁን መጠበቁ ትክክለኛ ርምጃ ካለመሆኑም በላይ በቅኝ አገዛዝ ዘመናችን የነበረዉን ሁኔታ በግልፅ አለማየትና አለማስታረቅ ነዉ። » ብለዋል። አዉሮጳዉያኑ ሃገራት ከአፍሪቃዉያኑ የዘረፉትን በሺዎች የሚቆጠር ጥንታዊ ቅርስ ነገ እንመልስ ቢሉ አፍሪቃዉያኑ ሃገራት ምንድን ነዉ ማድረግ ያለባቸዉ? ምንስ መዘጋጀት ይኖርባቸዋል?

«ይህ መሰረታዊ ጥያቄ ነዉ። በመጀመርያ ደረጃ ኅብረተሰቡን ስለቅርስ ምንነት መረጃ መስጠት ማስተማር ያስፈልጋል። ኅብረተሰቡ ቅርሱን እንዳይሸጥ ማኅተሙን እንዳይሸጥ የራሱን ማንነት በገንዘብም ሆነ በተለያዩ ጥቅማጥቅሞች አሳልፎ እንዳይሰጥ ማስተማር ያስፈልጋል።   ከዚህ በተጨማሪ ቅርሶቹ በእንክብካቤ መቀመጥ የሚችሉበት ቦታዎችን አስቀድሞ ማዘጋጀት ያስፈልጋል። ቅርሶች ዘመናትን ያሳለፉ በመሆናቸዉ ብዙ እንክብካቤን ይሻሉ። ማንነታቸዉን የሚጠብቅ ያስፈልጋል። ያንን ካላዘጋጁ በስተቀር ከዚህ አጨብጭበዉ በaneድ ሰማንት ይዘዉ ወደ ሃገራቸዉ ቢገቡም ተመልሰዉ በሽያጭ ይወጣሉ አልያም እዝያዉ ወድቀዉና ባክነዉ ይቀራሉ። ስለዚህ መንግሥታቶች በመጀመርያ ስለሕዝባቸዉ ስለ ሃገራቸዉ ሲያስቡ፤ የትምህርት ፖሊስያቸዉን ሲያዘጋጁ ለታሪክ ቦታ ሊሰጡ ይገባል። ቅርስ ጠባቂ ወታደሮች ያስፈልጉታል። እንደ አንድ መከላከያ ስራዊት ለመጠበቅ ፍላጎት ያላቸዉ ብቻ ሳይሆን እዉቀቱ ያላቸዉ በቅርስ ጥበቃ ላይ የሰለጠኑ ከዝያ በተጨማሪ ስለ ሃገራቸዉ የሚቆረቆሩ ፤ የሃገራቸዉ ነገር የሚያንገበግባቸዉ ፤ ታሪክ ሲበላሽ ቅርስ ሲዘረፍ የሚታመሙ ሰዎች ሊጠብቁት ይገባል።  ይህ ከተጠበቀ እንዲህ አይነት መሰረት ካለ በብሔር ብሔረሰብ እየተባለ በቋንቋና በዘር የሚጋጭባት ምክንያት የለም። ማንናዉም የሰዉ ዘር ልጅ የመጣዉ ከዚህ ቦታ ነዉ ብሎ መነሻዉ ታሪክ ስለሚያስነብብ ያንን ታሪክ ማገላበጥ ብቻ ነዉ። »      

Raubkunst? Die Bronzen aus Benin Ausstellung Hamburg
ምስል Museum für Kunst und Gewerbe Hamburg

በጀርመን የፕሩሻን ባህል ቅርስ ጥበቃ ፕሬዚዳንት ሄርማን ፓርዚንገር በበኩላቸዉ በርሊን ላይ የሚከፈተዉ ሁምቦልት ፎሩም የተባለዉ እና የአፍሪቃ ጥንታዊ ቅርስ እንዲሁም በጥንት ጊዜ ከአፍሪቃ የመጣ የራስ ቅልን ያካተተዉ ዓዉደ ርዕይ « የፀጥታ ቦታ» ሲሉ ሰይመዉታል። ሄርማን ፓርዚንገር ዓዉደ ርዕዩ ጀርመን ቅኝ በገዛችበት ዘመን የተፈፀመዉን ወንጀል ሕዝብ እንዳያጤነዉ አልያም እንዳያስበዉ ያስቆማል ባይ ናቸዉ። ከዚህ በተጨማሪ የቅኝ አገዛዝን ሕግጋቶች በመቃወም ለተቃዉሞ በወጡ ሄሬሮና ናማ ጎሳዎች ላይ ከ 1904 እስከ 1908 ዓ.ም ድረስ የተካሄደዉ የጅምላ ጭፍጨፋም ተጠቃሽ ነዉ።  ጀርመን በሄሬሮና ናማ ጎሳዎች ላይ የተካሄደዉ ግድያ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ መሆኑን ያመነችዉ በጎርጎረሳዉያን 2015 ዓ.ም ነበር። እንድያም ሆኖ ጀርመን ቅን ግዛት በያዘችበት ዘመን ከአፍሪቃ ሃገራት የወሰደችዉን ቅርሶች ለመመለስ ምንም አይነት ስምምነት አላካሄደችም።  የአዉሮጳ ሃገራት ከአፍሪቃ ሃገራት የዘረፍዋቸዉን ጥንታዊ ቅርሶች ለየሃገራቱ ለመመለስ የሚያራምዱት የቅርስ ጥበቃ ፖሊስም ሆነ ፖለቲካ ይፈቅድ ይሆን?   ይህ እንደየሃገራቶቹ ስርዓቶች ሊወስነዉ ይችላል። የየሃገራቶቹ መንግሥታት ስርዓት እና ፓርላማ ሕግጋቶች ይወስነዋል።

BG Afrikanische Raubkunst | Statue des Königs Ghezo
ምስል Imago/United Archives International

አቶ አለባቸዉ ደሳለኝ ከተንቀሳቃሽ ቅርሶች በተጨማሪ ታሪካዊ ሆቴሎች ንጻዎች ይዞታቸዉ ተጠብቀዉ ለትዉልድ መተላለፍ እንዳለባቸዉ ሳይገልፁ አላለፉም። 

በፕሬዚዳንት ኤማኑኤል ማክሮ ጥያቄ የአፍሪቃዉያን ሃገራት ቅርሶች ለማስመለስ የቀረበዉን ጥናት ከመፃፋቸዉ በፊት በበርሊን የሚከፈተዉ ቋሚ ቤተ-መዘክር « ሁምቦልት ፎሩም » የምክር ቦርድ አባል የሆኑት ፈረንሳዊትዋ ቤኔዲክት ሳቮይ፤ በዓዉደ ርዕዩ ይቀርባል የተባለዉ በቅኝ ግዛት እጅ ሥር ከወደቁት ሃገራት የመጣዉ ጥንታዊ ቅርስ ምን ያህል ደም እንደፈሰሰበት ይመርመር፤ ይህ በምርመራ ካልተጣራ ሁምቦልት ፎሩም የተሰኘዉ ቋሚ ኤግዚቢሽን መከፈት የለበትም ሲሉ ተቃዉሞአቸዉን ስራቸዉን በገዛ ፈቃዳቸዉ በመልቀቅ አሳይተዋል። ፈረንሳይ በቅኝ ግዛት ዘመን የተዘረፉ ቅርሶችን ለመመለስ የሚያስችል ሰፊ የጥናት ጽሑፍ ይፋ ከሆነ በኋላ የጀርመን ሙዚየም ዋና ዳይሬክተሮች ለምሳሌ በድሬስደን ከተማ የሚገኘዉ የሥነ-ጥበብ ቤተ-መዘክር ዳይሬክተር ማሪዎችን አከር ማን እንደገለፁት ባህላዊ ተቋማት ከአፍሪቃ ተዘርፈዉ የመጡ ጥንታዊ ቅርሶችን ለባለቤቱ በአፋጣኝ ለመመለስ ሕጋዊ ጥያቄዎች ላይ መስራት ይገባቸዋል።     

ሙሉ ጥንቅሩን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን። 

አዜብ ታደሰ

አርያም ተክሌ