1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተባ መ ዓመታዊ የሰብዓዊ ዕድገት ዘገባ

ሐሙስ፣ ሐምሌ 22 1996

የተባ መ የልማት መርሐግብር ስለ ሰብዓዊው አኗኗር ዕድገት ዘንድሮ ባቀረበው ዓመታዊ ዘገባ መሠረት፣ በብዙ የዓለም አካባቢዎች አሁን የሚታየው የኑሮ ደረጃው ሁኔታ እ ጎ አ በ፲፱፻፺--ማለት ከ፲፭ ዓመታት በፊት ከነበረው ይዘቱ ያነሰ ሆኖ ነው የሚታየው። በተለይ የነፍስወከፉን ገቢ፣ የጤንነትን የዕድሜን ይዘት እና የትምህርትን ደረጃ የስሌት መሠረት የሚያደርገው ዘገባ እንደሚለው፣ ባለፉት ፲፭ ዓመታት በዓለም ውስጥ ብዙ ሀገሮች በልማት ረገድ ጭራሹን ወደ ኋላ እ

https://p.dw.com/p/E0fR

�ሸረተቱ ነው የተገኙት።

ያው የተባ መ የልማት መርሐግብር ዘገባ እንደሚያመለክተው፣ ወደፊት በመራመድ ፈንታ ይብሱን ወደ ኋላ የሚያሸረትቱት፣ በተለይ ከሰሐራው በረሃ በስተደቡብ የሚገኙት የአፍሪቃ ሀገራት ናቸው። ለምሳሌ ቀሳፊው በሽታ ኤድስ በተስፋፋባቸው በስምንት ያፍሪቃ ሀገሮች ውስጥ አንድ ሰው እንደሚኖረው የሚጠበቀው ዕድሜ ወደ ፵ ዓመታትና ከዚህም ወዳነሰ ደረጃ ያዘቀዘቀ ሆኖ ነው የሚታየው። በዚህ አኳኋን፣ በድህነት፣ በበሽታ እና በመሐይምነት አንፃር ትግሉ እንዲጠናከር እጎአ በ፪ሺ ዓ.ም. የዓለም ርእሳነብሔርና መራሕያነመንግሥት በተባ መ ዘንድ የተለሟቸው የአሠርቱ ምእት ግቦች በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ውስጥ ሊተገበሩ የሚችሉበት ጥያቄ አሁን አጠራጣሪ ነው የሆነው። እንዲያውም፣ ዘገባው እንደሚገምተው፣ እጎአ እስከ ፪ሺ፲፭ ድረስ ለመላው ሕፃናት መሠረታዊው ትምህርት እንዲዳረስ የታሰበው ግብ ከብዙ ዘመናት በኋላ--እጎአ በ፪ሺ፩፻፳፱ ዓ.ም. ነው ሊደረስበት የሚችለው። በሕፃናት ላይ የሚደርሰውም የሞት አደጋ እስከ ፪ሺ፲፭ ድረስ በሁለት/ሦሥተኛ እንዲቀነስ የተተለመውም ግብ ከ፪ሺ፩፻፮ ዓ.ም. በፊት የሚደረስበት መስሎ አይታይም። ግን፣ የአሠርቱ ምእት ግቦች ሊደረስባቸው ከመቻላቸው በፊት፣ የኑሮ ውኅደት የሚጎላበት፣ ባሕሎች የሚጣጣሙበት ብዙወጥ፣ ግን ተዋሃጅ ኅብረተሰብእ የሚፈጠርበት ርምጃ መተግበር እንዳለበት ነው የሚመለከተው። በዚህ አኳኋን፣ ኣናሳ ብሔረሰቦች በሚጨቆኑበትና ወደ ጠርዙ በሚገፉበት አድራጎት አንፃር ትግሉ መጠናከር እንዳለበት ነው ዘገባው የሚያስገነዝበው።

ጥናት ከተደረገባቸው ፩፻፸፯ ሀገሮች መካከል እጅግ ማለፊያ የኑሮ ጥራት ያላት ሆና የተገኘችው ሀገር ኖርዌ ናት። ከዚያም ስዊድን፣ አውስትራሊያ፣ ካናዳና ኔደርላንድ ናቸው በተለይ በምሥጉንነት የሚጠቀሱት። በዚሁ ዘገባው በሚያቀርበው የኑሮ ጥራት ዝርዝር ውስጥ ጀርመን ለጊዜው ፲፱ኛውን ቦታ ነው የያዘችው። አማካዩ የገቢ ደረጃ ተነጥሎ ሲታይ ደግሞ፣ በዓመትና በነፍስወከፍ 27100 ያሜሪካ ዶላር እኩያ ገቢ ያላት ጀርመን ፲፬ኛው የኑሮ ጥራት ቦታ ላይ የምትገኘው። ግን በጾታዎች እኩል መብት ጥያቄ ረገድ ትልቂቱ እንዱስትሪ-ሀገር ጀርመን ገና ብዙ መሻሻል እንደሚያስፈልጋት የዓለሙ ድርጅት ዘገባ ያስገነዝባል። በዚህም መሠረት፣ጀርመን ውስጥ የሴቶች ገቢ በወንዶቹ ደሞዝ አኳያ ሲታይ፣ ጀርመናውያኑ ከኡክራይና እና ከኮሎምቢያም ኋላ 83ኛውን ቦታ ነው የሚይዙት። ዓመታዊው ዘገባ እንደሚያሳየው፣ ዩኤስ-አሜሪካ በዚሁ በኑሮ ጥራት ረገድ እ ጎ አ በ፪ሺ፫ የነበራትን ቦታ በአንድ አጓድላ ወደ ስምንተኛው ወርዳለች። ከመረጃ ጉድለት የተነሳ፣ ኢራቅ፣ አፍጋኒስታን፣ ሰሜን ኮርያ እና ላይቤሪያ በኑሮው ጥራት ረገድ የተባ መ ፍተሻ አልተደረገባቸውም።

አስቀድመን የጠቀስናት ኖርዌ በዚያው በኑሮው ጥራት ረገድ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ ቀዳሚውን ቦታ እንደያዘች ነው የቆየችው። የዚያችው ሀገር ሕዝብ ረዥም ዕድሜ በ፸፱ ዓመታት ነው የሚታሰበው። የመጀመሪያዎቹን ፳ ቦታዎች የሚይዙት እንደተለመደው በእንዱስትሪ ልማት የበለፀጉት ሀገራት ናቸው፣ የምድብ ቦታዎቻቸውም ተቀራራቢ ሆነው ነው የሚታዩት። በዚህም መሠረት፣ ቤልዥግ ከሆላንድ ለጥቃ ስድስተኛውን ቦታ ስትይዝ፣ ከርሷ የሚለጥቁት በቅደም-ተከተል አይስላንድ፣ ዩኤስ-አሜሪካ፣ ጃፓን፣ አየርላንድ፣ ስዊስ፣ ብሪታንያ፣ ፊንላንድ፣ ነምሳ፣ ሉክሰምቡርክ፣ ፈረንሳይ፣ ዴንማርክ፣ ነው ዚላንድ፣ ጀርመንና እስጳኝ ናቸው። በዝርዝሩ ዘብጥ ላይ የምትገኘው፣ በዓመታት ጦርነት ስትታመስ የቆየችው ምዕራብ አፍሪቃዊቱ ሀገር ሴራ ሊዎን ናት። ኢትዮጵያ ደግሞ ጥናቱ ከተደረገባቸው ፩፻፸፯ቱ ሀገራት መካከል ሰባቱን ብቻ--ማለት ሞዛምቢክን፣ ጊኔቢሳውን፣ ቡሩንዲን፣ ማሊን፣ ቡርኪናፋሶን፣ ኒዤርንና ሴራሊዎንን--ቀድማ ፩፻፸ኛውን ቦታ ነው የያዘችው።

አስቀድሞ እንደተጠቀሰው፣ በአፍሪቃ የብዙዎቹን ሀገራት ሕዝብ ዕድሜ ወደ ፵ ዓመታትና ከዚህም በታች ያሽቆለቆለው ጠንቀኛው በሽታ ኤድስ በሰብዓዊው ዕድገት ረገድ ዋነኛው መሰናክል ሆኖ ነው የሚታየው። የተባ መ የልማት መርሐግብር አመራር እንደሚለው፣ ኤድስ ሰዎችን ገና በአፍላው እጅግ ምርታማ ዕድሜያቸው ስለሚፃረር መንግሥታትን በመላው የኑሮ ዘርፍ በኩል ነው የሚያሰነካክለው። ስለዚህ፣ ዘገባው እንደሚያስገነዝበው፣ ለሰብዓብዓዊው ዕድገት በሚደረገው ጥረት ረገድ በተለይ በኤድስ አንፃር ለሚካሄደው ዘመቻ ነው ከሁሉ የቀደመው ትኩረት መሰጠት ያለበት።

በዚያው በተባ መ የሰብዓዊ ዕድገት ዘገባ መሠረት፣ በባሕላዊው ኑሮ ረገድ ብዙወጥ የሆኑት ኅብረተሰቦች ለዓለሙ ድርጅት የአሠርቱ ምእት ግቦች ክንውን ዓቢይ ቁልፍ ነው የሚሆኑት። ይኸውም፣ መሠረታዊ ሰብዓዊ መብት የሆነው ብዝሃ-ባሕል፣ ሙሉው ባሕላዊ ነፃነት፣ ዴሞክራሲ፣ የፖለቲካው መድበላዊነት ለተቀናባሪው የፖለቲካ ኑሮ እና ለደንዳናው የኤኮኖሚ ሂደት ዓይነተኛ መሠረት ሆኖ ነው የሚታየው። መላው ሕዝቦች የብሔረሰብ፣ የቋንቋ፣ እና የሃይማኖት መለያቸውን ለመጠበቅ ሙሉ መብት አላቸው፣ ለእነዚሁኑ ልዩነቶች ትውቂያን የሚሰጠው መንግሥታዊ መርሕ ብቻ ነው በብዙወጥ ኅብረተሰቦች ውስጥ አዛላቂውን ዕድገት ለማከናወን የሚያስችለው ይላል የተባ መ የልማት መርሐግብር ዘገባ። ዓለም የአሠርቱ ምእትን ግቦች ሊደርስባቸውና የኋላ-ኋላም ድህነትን ሊቀርፈው ይበቃ ዘንድ፣ ከሁሉ በፊት ብዝሃ-ባሕል ያለበትን ኅብረተሰብእ ተቀናባሪ ኑሮ መግንባት እጅግ አስፈላጊ መሆኑ ነው የሚመለከተው።

ድህነት የተጫናቸውና ወደ ኑሮው ጠርዝ የተገፉት ወገኖችና ኣናሳ ብሔረሰቦች በየወረዳው፣ በየኣካባቢውና በየብሔራዊው ደረጃ የፖለቲካውን ተግባር አብሮ የመወሰን መብት ካላገኙ በስተቀር፣ ለሥራ ቦታ፣ ለትምህርት፣ ለሕክምና እና ለሌሎችም መሠረታዊ አገልግሎቶች ዕድል አይኖራቸውም ይላል የተባ መ ዘገባ። እንዲያውም፣ የልይዩ ብሔረሰቦች፣ የሃይማኖትና የቋንቋ ቡድኖች ሙሉ እኩልነት ትውቂያ ነው በዚህ በ፳፩ኛው ምእተ-ዓመት በዓለምአቀፉ የፖለቲካ እርጋታና ሰብዓዊ ዕድገት ላይ እጅግ ከፍተኛ ተጽእኖ ካላቸው ጥያቄዎች አንዱ ሆኖ የሚታየው።

በ፪፻ ሀገሮች ውስጥ ከ፭ሺ የሚበልጡ ልይዩ የብሔረሰብእ ቡድኖች እንዳሉ ይታወቃል። ከየ፫ ሀገሮች በሁለቱ ውስጥ ቢያንስ አንድ ትልቅ የብሔረሰብእ ቡድን ከሕዝቡ ፲ በመቶውን ወይም ከዚህ የበለጠውን እንደሚወክል ጥናቱ ያመለክታል። የተባ መ ዘገባ እንደሚለው፣ ዛሬ ዘመናዊው ኅብረተሰብእ ሰዎች ራሳቸውን እንደፈለጋቸው እንዲያንቀሳቅሱ ይፈቅዳል። ለምሳሌ፥ በላቲን አሜሪካ የሚገኙ ኣናሳ ብሔረሰቦች በባልካን ወደሚገኙ ሺኣ መሰሎቻቸው፣ የኢራቅ ሱናዎችና ኩርዶች በሰሜን አፍሪቃ ወዳሉ የብሔረሰብእ ተጓዳኞቻቸው ይንቀሳቀሳሉ። በድንበር አልባው አጽናፋዊነት፣ በመገናኛ አውታር መስፋፋት፣ በተፋጠነ ፍልሰት እና በዴሞክራሲ ድብረት ምክንያት ዛሬ ሰዎች የብሔረሰብን፣ የሃይማኖትን፣ የዘርን፣ እና የባሕልን መስመሮች እየተከተሉ ከአንዱ የዓለም አካባቢ ወደሌላው በነፃ የሚንቀሳቀሱበት ዝንባሌ ነው የሚጎላው--የተባ መ የልማት መርሐግብር ዘገባ እንደሚለው። ነገሩን ለማጠቃለል እንግዲህ፥ ዘገባው አበክሮ እንደሚስገነዝበው፥ ይህንኑ የኅብረተሰብ ብዙወጥነት አስተባብሮ የሚያጠናክረው እና መድበለ-ባሕልን የሚያነቃቃው መርሕ በልማቱ መርሐግብር ውስጥ የሚጣጣን መሆን አለበት--ይህ ሲሆን ብቻ ነው፥ የልማት ሂደት፣ የፖለቲካ እርጋታና ጤናማ ዴሞክራታዊ አስተዳደር ሊረጋገጥ የሚችለው።