1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተባበሩት መንግስታት የሰላምና የመልሶ ግንባታ ኮሚሽን

ዓርብ፣ ሰኔ 16 1998

ኮሚሽኑ ዛሬ የመጀመሪያውን ጉባኤውን ያካሂዳል።

https://p.dw.com/p/E0iY

በተሀድሶ ዕንቅስቃሴው አዲሱን የሰብዓዊ መብት ምክርቤት ያቋቋመው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ወደፊት ከሚጠብቁት ተመሳሳይ ተግባራት ውስጥ የድርጅቱን የሰላምና የመልሶ ግንባታ ኮሚሽን መመስረትም ይገኝበታል። ለመንግስታቱ ድርጅት የሰላም ማስጠበቅ ተልዕኮ ድጋፋ ሰጭ የሆነው ይኽው ኮሚሽን የአካባቢያዊ ተቅዋማትን፣ የለጋሽ መንግስታትን ፣ለድርጅቱ ወታደር የሚሰጡ አገራትን እንዲሁም የዓለም ዓቀፍ የገንዘብ ድርጅቶችን ጥረቶችን ማስተባበር ነው ዋነኛው ተግባሩ ። ከዚህ ቀደም ጦርነት በተካሄደባቸው አገሮች ጦርነት እንዳበቃ ከሚከሰቱ ችግሮች ልምድ በመነሳት በተለይ በመልሶ ግንባታ ላይ የሚያተኩረው ይህ ኮሚሽን ዛሬ የመጀመሪያውን ስብሰባውን ያካሂዳል። ዛሬ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የመጀመሪያ ጉባኤውን የሚካሄደው ሰላሳ አንድ አባላት ያሉትበድርጅቱ የሰላምና የመልሶ ግንባታ ኮሚሽን አደራጃጀት ቅዋሚ ኮሚቴ ነው ። ጉባኤው የኮሚሽኑን ሊቀመንበር ይመርጣል ፤ ጊዜያዊ የመተዳደሪያ ደንብም ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል። ጉባኤውን በንግግር የሚከፍቱት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሀፊ ኮፊ አናን እንደሚሉት የኮሚሽኑ ዕውን መሆን ትልቅ ውጤት ነው።
ድምፅ.............................................................................
“ከጦርነት ወደ ሰላም በመሸጋገሪያው አስቸጋሪው ወቅት ላይ መንግስታትና ህዝቦችን ለመርዳት በምናደርጋቸው ጥረቶች እዚህ ደረጃ ላይ መድረሳችን አንድ ትልቅ ውጤት ነው”

የመንግስታቱ ድርጅት የሰላምና የመልሶ ግንባታ ኮሚሽን ምስረታ ከአጠቃላዩ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተሀድሶ ዕንቅስቃሴዎች አንፃር ሲታይ ብዙም ጎልቶ አይወጣ ይሆናል።ይሁንና የኮሚሽኑ መመስረት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ከማንም በላይ በጦርነት ውስጥ ያለፈ ሰው የሚረዳው ጉዳይ ነው። ጦርነት በህዋላ ሁኔታዎች ተረጋግተው እንደቀድሞው እስኪሆኑ ድረስ ፈተናው ቀላል አይደለም ። ይህ ደግሞ በምስራቅ አውሮፓ፣ በአፍሪቃ እንዲሁም በእስያ በተደጋጋሚ ጊዜያት የተከሰተ ነው ። የተባበሩት መንግስታት የሰላምና የመልሶ ግንባታ ኮሚሽንን መቅዋቅዋም አስፈላጊ የሆነውም ከነዚህ አገራት ልምድ በመነሳት ነው። በዚህ ጉዳይ ዙሪያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጀርመን አምባሳደር Gunter Pleuger አስተያየታቸውን ሲሰጡ
ድምፅ...................................................................................................................................
“ያለን ልምድ ወታደራዊው ግጭት እንዳበቃ ዓለም ዓቀፍ ሀይሎች ግጭቶች ከተከሰቱባቸው አካባቢዎች በወጡ በአምስት ወይም በአስር ዓመት ጊዜ ውስጥ ጦርነት ተመልሶ መቀስቀሱን ነው የሚያሳየው።”
በቅርቡ በምስራቅ ቲሞር የተቀሰቀሰው ግጭት በዚህ ረገድ እንደምሳሌ ይነሳል ። ሌሎች አካባቢዎችም ተመሳሳይ ችግር ውስጥ መውደቃቸው ይታወቃል።እናም አዲሱ ኮሚሽን ከግጭቶች በህዋላ ሁኔታዎች እስኪረጋጉ ድረስ ለረዥም ጊዜ የሚዘልቅ ተግባር ያከናውናል ። ለዚህ ተግባር ማካሄጃም ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውጭ የሆኑት እንደ ዓለም ባንክና የአውሮፓ ህብረት የመሳሰሉ ድርጅቶች የገንዘብ ድጋፍ ይጠበቃል ። ምክንያቱም አምባሳደር Pleuger እንዳሉት የመንግስታቱ ድርጅት ለኮሚሽኑ ተልዕኮ የሚያስፈልገውን ወጪ የመሸፈን አቅም አይኖረውምና ።
ድምፅ.........................................................................................................................................
“በአሁኑ ወቅት በአራት አህጉራት ውስጥ አስራ ስምንት የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች አሉን ። በዚህ የተነሳ ወጪው ከሶስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር ወደ አምስት ቢሊዮን ዶላር አሻቅቦዋል።”

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በዳርፉር ከተሰማራ ደግሞ የድርጅቱ ወጪ በሁለት ቢሊዮን ዶላር ከፍ ማለቱ አይቀርም።ይሁንና የጀርመኑ ዲፕሎማት አዲሱ ኮሚሽን የራሱን የገቢ ምንጮች ያገኛል የሚል ተስፋ ነው ያላቸው። በዚህ ምንክንያትም የመንግስታቱ ድርጅት የኢኮኖሚና የማህበራዊ ክፍሎች በኮሚሽኑ ውስጥ ይካተታሉ።የሰላሙን ሂደት ለመደገፍ የዓለም ባንክ በሩን ክፍት ማድረግ አለበት ። እስካሁን ካለፉት ዓመታት ከአሉታዊው ተሞክሮአቸው ትምህርት የወሰዱት የመንግስታቱ ድርጅት መሪዎችና የመጀመሪያውን ጉባኤያቸውን ዛሬ የሚያካሂዱት ሰላሳ አንዱ አባላት ስለወደፊቱ ተግባራቸው ብቻ ሳይሆን በኮሚሽኑ ማ ምን እንደሚሰራ በተጨባጭ ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል። ኮሚሽኑ በዛሬው ጉባኤው የብሩንዲና የሴራልዮንን ከጦርነት ወደ ሰላም ሽግግር በማገዝ ተግባር ላይ ይነጋገራል።