1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተረሱት የሆሎኮስት ሰለቦች

ሐሙስ፣ ጥር 19 2003

ደምቆ የሚታየዉ-የክረምቱን ጉም ደመና ያገረጣዉን-ሰማያዊ ሰማይ ከአድማስ እስከ አድማስ የተደገፉ የሚመስሉ ጉብታዎች፥-በረዶ የሸፈነዉ ሳር : የተረሳ መሬት፥ እና ወንከርከር ብለዉ የቆሙ እርጥብ-ጥርብ ድንጋዮችን። ግን በርግጥ ቀብር ነዉ የአይሁዶች ቀብር።

https://p.dw.com/p/Qvyr
የተረሳዉ መካነ-ቀብር ዩክሬንምስል Mikhail Tyaglyy

ከ 70 ዓመት በፊት እንደ ጎርጎሮሳዉ አቆጣጠር ሰኔ 22 1941 የናትሴ ጀርመን ጦር የሶቬት ሕብረት ግዛትን ያጠቃ ጀመር።ዘመቻ ባርባሮሳ የተሰኘዉ የዚያ ጥቃት ዉጤት የሐይል አገዛዝ፥ አረመኔያዊ ግድያ እና ለአይሁዳዉያን መጨፍጨፍ ነበር።በዛሬዎቹ ሩሲያ፥ ዩክሬን፥ ቤሎ ሩስና ፖላንድ ግዛቶች እስካሁን ድረስ በግልፅ ያልታወቁ በርካታ የአይሁዶች የጅምላ ቀብሮች አሉ።በናትሴ ጀርመኖች የተጨፈፉ አይሁዶች ወይም ሆሎኮስት ሚታሰብበት ሰሞን አሁን እነዚያን የተረሱና የተዘነጉ የአይሁዳዉያን መካነ-ቀብሮችን ለመፈለግና ለመጠበቅ የሚደረገዉ አለም አቀፍ ጥረት ተጨባጭ ዉጤት እያስገኘ ነዉ።የዶቸ ቬለዋ ኮርኔሊያ ራቢትስ የዘገበችዉን ነጋሽ መሐመድ ሰበብ አድርጎ አጠናቅሮታል።

በሁለተኛዉ የአለም ጦርነት ወቅት የጀርመን ናትሴዎች የጨፈጨፏቸዉ አይሁዶች በየአመቱ የዛሬን ዕለት ይዘከራሉ።ከሩሲያ እስከ ፖላንድ በሚደርሰዉ ግዛት በጅምላ የተቀበሩትን ግን እስካሁን የሚያዉቅ-የሚስታዉሳቸዉም አልነበረም።ኮርኔሊያ ራቢትስ-«የተዳፈነዉ እዉነት» ትለዋለች።መካነ-ቀብሩን ደግሞ «የዘግናኝ አረመኒያዉ ምግባር ምሳሌ።

ፎቶ ግራፉ የመካነ ቀባር መሆኑን ለመረዳት አዳጋች ነዉ።ደምቆ የሚታየዉ-የክረምቱን ጉም ደመና ያገረጣዉን-ሰማያዊ ሰማይ ከአድማስ እስከ አድማስ የተደገፉ የሚመስሉ ጉብታዎች፥-በረዶ የሸፈነዉ ሳር : የተረሳ መሬት፥ እና ወንከርከር ብለዉ የቆሙ እርጥብ-ጥርብ ድንጋዮችን።ግን በርግጥ ቀብር ነዉ የአይሁዶች ቀብር።

«ጀርመኖቹ እነዚሕን ድንጋዮች ከ1941 ጀምሮ ወስደዋቸዉ መንገድ ሠርተዉባቸዉ ነበር።በ1944እና 45 ግን ቀዩ ጦር ድንጋዮቹን ሰብስቦ ዳግም እዚሕ አስቀመጣቸዉ።ከዚያ በሕዋላ ማንም ያስታወሳቸዉ ሥላልነበረ እንደነበሩ አሉ።»

ይላሉ ክርስቶፍ ፊሊንገር።በበርሊን የአሜሪካ የአይሁድ ማሕበረሰብ አባል ናቸዉ።ዩክሬይን ዉስጥ የሚገኘዉን ያን ሥፍራ ባለፈዉ አመት ፎቶ ግራፍ ያነሱትም እሳቸዉ ናቸዉ።አሜሪካዊ ራቢ አንድሬዉ ቤከር ደግሞ ሆሎኮስት የተጀመረዉ አዉሽቪትስ ሳይሆን-በዚያ በ1941 በጋ እዚያ ነበር-ይላሉ።

«የአዉሮጳ አይሁዳዉያንን ሆን ብሎ መግደል የተጀመረዉ የጀርመን ጦር ወደ ምሥራቅ ባደረገዉ ዘመቻ ፖላንድ፥ ዩክሬንና ቤሎ ሩስን ሲይዝ ነበር።ተንቀሳቃሾቹ የገዳዮች ቡድናት በመደበኛዉ ጦርና ባካባቢዉ በሚኖሩ ተባባሪዎቻቸዉ እየታገዙ በየደረሱበት አይሁዶቹን እየገደሉ በመቶ የሚቆጠሩትን በጅምላ ቀብረዋቸዋል።»

Holocaust Denkmal Berlin Flash-Galerie
የሆሎኮስት መታሰቢያ-በርሊንምስል DW/Nelioubin

አንድ የፈረንሳይ በጎ አድራጊ ድርጅት ባደረገዉ ጥናት ዩክሬን፥ፖላንድ፥ ቤሎሩስና ሩሲያ ዉስጥ አንድ ሺሕ ያሕል የጅምላ መቃብሮች ተገኝተዋል።የተገኙት የጅምላ መቃብሮች ዳግም እየተገነቡ በቅጡ እንዲያዙም እየተሞከረ ነዉ።የጀርመን ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ለሙታኑ መታሰቢያ ማሰሪያ 3መቶ ሺሕ ዩሮ ለገሷል።

የመርሐ ግብሩ የበላይ ሐላፊ ያን ፋልቡሽ እንደሚሉት የጅምላ ቀብሮቹ ይዞታ በግልፅ የታወቀዉ ባለፈዉ ታሕሳስ ነበር።አንዳዶቹ በየጉጥ ስርጓጉጡ ተደብቀዋል።ሌሎቹ ደግሞ ክፍት ናቸዉ።

«መቃብሮቹ ክፍት መሆናቸዉ ግድያዉም ሆነ አቀባበሩ በይድረስ ይድረስ መፈፀሙን አመልካች ነዉ።ከዚሕም ሌላ መቃብሩ ለብሶት የነበረዉ አፈር ከጦርነቱ በሕዋላ መጠረጉን ጠቋሚ ነዉ። መቃብሮቹ መከፈታቸዉም በግልፅ ይታያል።አንዳድ ሥፍራ ከጉርጓድ ዉጪ ሜዳ ላይ አፅሞች ተገኝተዋል።ይሕ የአካባቢዉ ነዋሪ ከሟቾቹ ጋር የተቀበሩ ጌጦችና ቁሳቁሶችን ፍለጋ መቃብሩን ከፍተዉ የተዉት ሳይሆን አይቀርም።»

Vergessene Massengräber des Holocaust
የተረሳዉ መካነ-ቀብርምስል Mikhail Tyaglyy

የአለም አቀፉ ጥረት አለማ ያኔ የተፈፀመዉን የግፍ-ታሪክ ለአሁኑ ትዉልድ ከማሳወቅ አልፎ ለመጪዉም ለማስረዳት መረጃዎችን መሰብሰብና በቅጡ ማደራጀት ነዉ።በዩክሬን የአይሁዳዉያን ኮሚቴ ሰብሳቢ ኤድዋርድ ዶሊንስኪይ እንደሚሉት የጅምላ ቀብሮቹ ታሪክ ለዚያ አካባቢ አይሁዳዊ አሁንም ወቅታዊ ርዕሥ ነዉ።

«የሆሎኮስቱ የጅምላ ግድያ ችግር ለኛ ወቅታዊ ጉዳይ ነዉ።ምክንያቱም ማሕበረሰቡ የተፈፀመዉን ታሪክ ችላ የማለት አዝማሚያ ይታይበታል።ወጣቶችና ሕፃናት የሚያዉቁት ነገር የለም።ለማወቅ ሥለማይፈልጉ አይደለም-የሚማሩት ሥለ ሌለ እንጂ።»

ታሪኩን የመመዝገብ-የማሳወቅ፥ የማቆየት-ማስተማሩ ጥረት በርግጥ ቀጥሏል።ለዘግናኙ ታሪክ የተሟላ ሥዕል ለመስጠት ከዋነኞቹ መረጃዎች አንዱ የአይን ምስክሮች እማኝነት ነዉ።ከዚያ ዘመኑ ትዉልድ እስካሁን በሕይወት ያሉት ጥቂቶች ናቸዉ።እነሱም ሰማንያና ዘጠናዎቹን አመታት እያገባደዱ ነዉ።እና የተዘነጋዉን መካነ-ቀብር የሚፈልጉ፥ የግፉን ታሪክ የሚያሰባስቡት ወገኖች ከጊዜ ጋር እሽቅድምድም ገጥመዋል።
ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሠ