1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተመ ድ አረጋጊ ቡድን፣ ሚኑስማ፣ በማሊ

ሰኞ፣ ሰኔ 24 2005

የተመድ ማሊን ለማረጋጋት ዛሬ ሰኞ እአአ ሀምሌ አንድ ቀን የሰላም ተልዕኮ ይጀምራል። ይኸው በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ ሚኑስማ በመባል የሚጠራው የተመድ አረጋጋጊ ቡድን 12,600 ወታደሮች ያሰልፋል።

https://p.dw.com/p/18zN3
ምስል Reuters

ይኸው በሰሜናዊ ማሊ የሚንቀሳቀሱት ዓማፅያን ጥቃት ያሰጋው የተመድ የማሊ አረጋጋጊ ቡድን ስንቅ እና ትጥቅ የማሟላት ትልቅ ችግር ተደቀኖበታል። ይህ መሆኑ እየታወቀም ግን፣ ዓለም አቀፉ ማህበረ ሰብ በተመድ የማሊ አረጋጋጊ ቡድን ትልቅ ትፅቢት አሳርፎዋል።

በማሊ ስራውን ዛሬ ሰኞ ሀምሌ አንድ ቀን የሚጀምረው የተመድ አረጋጋጊ ቡድን ተልዕኮው ቀላል እንደማይሆን የተልዕኮው መሪ ቤርት ከንደርስ ባማኮ ከሚገኘው ቢሮአቸው አስታውቀዋል፣ ተልዕኮው ማሟላት ያለበትን ተግባር ከንደርስ ሰሞኑን ኒው ዮርክ ከሚገኘው የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ጋ ባደረጉት ቀጥታ የቪድዮ ግንኙነት ዘርዝረዋል።

Albert Gerard Koenders ehemaliger niederländischer Entwicklungshilfeminister
ምስል Getty Images/AFP

« በሁለት ዋነኛ ዘርፎች እንድንረዳ፣ ማለትም፣ የሽግግሩን ስምምነት እና በቅርቡ ይካሄዳል የሚባለውን ምርጫ ተግባራዊ እንድናስደርግ ጥሪ ቀርቦልናል። እነኂህ ርዳታዎች ለቀጣዩ ወሳኝ ሂደት አስፈላጊ የሆኑ የመጀመሪያ ርምጃዎች ናቸው። የነዚህ ትግባራት መሳካት እምነት በመፍጠሩ እና ማሊ ለማረጋጋት በሚያስችለው ድጋፍ ላይ ጥገኛ ይሆናል። »

እንደሚታወሰው፣ የማሊ መንግሥት ከጥቂት ቀናት በፊት ነበር ከቱዋሬግ ዓማፃፅያን ጋ የሰላም ውል የተፈራረመው። የማሊ ዜጎች ሀምሌ መጨረሻ አዲስ ፕሬዚደንት ይመርጣሉ። በዚህም ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት፣ መጋቢት 2012 ዓም አንድ የጦር ኃይሉ ቡድን መፈንቅለ መንግሥት ካካሄደ እና ይህን ተከትሎም የቱዋሬግ ዓማፅያን እና አክራሪ ሙሥሊሞች ሰሜናዊ ማሊን ከተቆጣጠሩ በኋላ በሀገሪቱ የተፈጠረውን ምሥቅልቅል ሁኔታ በማብቃት አሁን በማሊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የመትከሉ ሂደት ይጀመራል። የማሊ የሽግግር መንግሥት በ2012 ዓም የመፀው ወራት ከተመድ ወታደራዊ ርዳታ ቢጠይቅም የተመድ እስከጥቂት ጊዜ በፊት ድረስ ሲያመነታ ነበር የቆየው።

የማሊ መንግሥት ሰሜናዊ ማሊን በፈረንሳይ ወታደሮችና በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ አፊስማ በመባል በሚታወቀው በአፍሪቃውያን የተመራውን የማሊ ድጋፍ ሰጪ ጓድ መልሶ መቆጣጠር ችለዋል። በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ አፊስማ በመባል የሚታወቀውን በአፍሪቃውያን የተመራውን የማሊ ድጋፍ ሰጪ ተልዕኮ ሰሜናዊ ማሊን ለማረጋጋት ይሰጠው የነበረውን ድጋፍ አሁን የተመድ አረጋጋጊ ቡድን፣ ሚኑስማ ይረከባል። ከምዕራብ አፍሪቃ የተውጣጡት እና በአፊስማ የተጠቃለሉት 6000 የምዕራብ አፍሪቃ ሀገራት ወታደሮች በቤርት ከንደርስ የሚመራውን ሚኑስማን በመቀላቀል ያን ያህል ያልተጠናከረውን የማሊን ሰላም ለማሰከበር ይጥራሉ። ሚኑስማ በተለይ የሰሜን ማሊን ሕዝብ አፈንግጠው ከወጡ ተገንጣይ ያማፅያን ቡድን ጥቃት፣ ካስፈለገም በኃይል ተግባር ተጠቅመው፣ ይከላከላል። ከዚህ በተጨማሪም በዚሁ አካባቢ የሚታየውን ረሀብ እና በሽታ የመታገል፣ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ስደተኞች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ እና የፖሊስ ጣቢያዎች እና ማዘጋጃ ቤቶች እንደገና ስራቸውን በሚገባ እንዲጀምሩ ርዳታ የማድረግ ስራ ይጠበቅባቸዋል። ይህ ቀላል እንደማይሆን የጀርመን መከላከያ ሚንስትር ቶማስ ደ ሜዝየር ገልጸዋል።

Mali UN Mission MINUSMA 01.07.2013
ምስል Reuters

« በአፍሪቃ ትዕግሥት ያስፈልጋል። ተልዕኮው አዳጋች ሊሆን ይችላል። ከሚጀመሩ ተልዕኮዎች ብዙ መጠበቅ እንደሌለበት ተምረናል። ሊኖር የሚችለውን ዕድል እና ሊከተል የሚችለውን ስጋት ማጤን አስፈላጊ ነው። »

የሚኑስማ ተልዕኮ የስንቅ እና ትጥቅ አቅርቦት መሟላትን በተመለከተ ከተመድ ተልዕኮዎች ሁሉ አዳጋቹ መሆኑን የሚኑስማ ኃላፊ ቤርት ከንደርስ በማስታወቅ ወታደሮች ለስራቸው እንደሚፈለገው ዝግጁ ለማድረግ ለተልኮው ተጨማሪገ ንዘብ እንዲመደበለት ጠይቀዋል። ይህ በተለይ በማሊ የተሰማሩት እና አስፈላጊው ትጥቅ የተጓደላቸውን ምዕራብ አፍሪቃውያኑን የአፊስማ ወታደሮችን ይመለከታል።

« ማሊን ለማረጋጋት ላሳዩት ቆራጥነት እና ላበረከቱት አስተዋፅዖ ላመሠግናቸው አወዳለሁ። በዚሁ ተግባር ላይ ሕውታቸውን ላጡት ጓዶቻቸው ቤተሰቦችም ሐዘኔን እንደገና እገልጻለሁ።

ፔተር ሂለ/አርያም ተክሌ

መሥፍን መኮንን