1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተመድ እና ዳርፉር

ሐሙስ፣ መስከረም 12 1998

በሱዳን የዳርፉር ግዛት የቀጠለው ውዝግብ እንዳይባባስ ማሥጋቱን የተመድ ዋና ፀሐፊ ልዩ ልዑክ ጃን ፕሮንክ ትናንት በፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ባሰሙት ንግግር አስጠነቀቁ።

https://p.dw.com/p/E0jU

በመሆኑም ዓለም አቀፉ ኅብረት ሰብ በተቀናቃኞቹ ወገኖች መካከል ግፊት እንዲያሳርፍ ፕሮንክ ጥሪ አቅርበዋል። «በዳርፉር የቀጠለው ውጊያ እና የኃይል ርምጃ የታከለበት ግጭት እየተስፋፋ እንደሄደና ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጭ ሊሆን ይችላል።» ሲሉ ነበር ጃን ፕሮንክ በፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱ ዝግ ስብሰባ ላይ በግልፅ ያስረዱት። ለዚህም ተጠያቂው፡ ይላሉ ፕሮንክ፡ ዓለም አቀፉ ኅብረተ ሰብ የዳርፉር ጊዚያዊ ሁኔታን በቸልተኝነት የተመለከተበትና በተቀናቃኞቹ ወገኖች ላይ ንዑሱን ግፊት ብቻ ያሳረፈበት ድርጊት ነው። በመሆኑም፡ የዓለሙ መንግሥታት ድርጅት ላዕላዩ አካል ግልጹን ውሳኔ እንዲያሳልፍ ፕሮንክ ትናንትም በድጋሚ በአፅንዖት አሳስበዋል። የፀጥታ ጥበቃው ምክር ቤት ለሱዳን መንግሥትና ለዳርፉር ዓማፅያን የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እንዲሰጥ የተመድ ልዩ ልዑክ ጠይቀዋል። ማስጠንቀቂያ፡ «ካሁን በኋላ ውጊያው የቀጠለበትን ሁኔታ አንቀበልም፤ እስከፊታችን ታህሳስ ሀያ ሁለት ድረስም የሰላም ስምምነት የማይደረስበትን ድርጊት አንቀበልም።» የሚሉትን ዓረፍተ ነገር ማጣቃለል እንዳለበት ነው ፕሮንክ ያመለከቱት። ይሁንና፡ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት አባል መንግሥታት ዳርፉርን በተመለከተ እስካሁን ድረስ አንድ ዓይነት አቋም መያዝ እንደተሳናቸውና የወሰዱትም የፖለቲካ ውሳኔ ደካማ መሆኑን ፕሮንክ አላጡትም። ምክር ቤቱ እስከዛሬ ድረስ ለማሳለፍ የሞከረውን የተኛውም ጠንካራ ርምጃ ቋሚ አባላቱ ቻይና ወይም ሩስያ አግደውታል። በዚህም የተነሣ አሥራ አምስቱ የምክር ቤቱ አባል መንግሥታት ክትትል በዝቶበት በሚልዮን የሚቆጠር ሕዝብ ከቤት ንብረቱ ለተፈናቀለበትና በአሥር ሺህ የሚቆጠሩ ሲቭሎች ለተገደሉበት ድርጊት ተጠያቂዎች ናቸው ሲሉ ፕሮንክ በግልፅ ወቀሳ ሰንዝረዋል። በጊዜ ማስጠንቀቂያ ቢያቀርቡምና የዳርፉር ፀጥታን ለማረጋገጥ ግዙፍ ጦር እንዲሠማራ ቢጠይቁም፡ እጅግ ዘግይቶ ንዑሱ ርምጃ ብቻ፡ ማለትም፡ ጥቂት ወታደሮች ብቻ እንዲሠማሩ መፈቀዱን ልዩው ልዑክ አስረድተዋል። እርግጥ፡ ከውይይት በኋላ የአፍሪቃ ኅብረት ጦር ጓድ መሠማራቱና የተመድ ርዳታም ከበፊቱ በተሻላ ሁኔታ ቢቀርብም፡ የዳርፉርን ውዝግብ ለማብረድ በቂ አለመሆኑን ፕሮንክ ከመግለፅ አልተቆጠቡም። ሱዳን በጠቅላላ በወቅቱ አዲስ ሥጋት ተደቅኖባታል። የጀርመን ጦር ጓድ ይሠማራበታል በሚባለው በደቡባዊ ሱዳን ለምሳሌ ከሰሜን ዩጋንዳ የሚንቀሳቀሱት የሎርድ ሬዚስተንስ አርሚ ዓማፀያን ጥቃት መሰንዘራቸውን ፕሮንክ አስታውቀዋል። በመዲናይቱ ካርቱምም በርካታ ዐረባውኣን በመንግድ ተገድለው ከተገኙ ወዲህ የተደራጁ ዐረባውያን ቡድኖች በሀገሪቱ ጥቁር አፍሪቃውያን ላይ የበቀል ርምጃ አካሂደዋል። ከ 1956
ዓም ወዲህ፡ ይህ ዓይነቱ ጥቃት በመዲናይቱ ሲካሄድ ይህ የመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው። ተመሳሳዩ ግጭት ከቀጠለም ሁኔታዎችን መቆጣጠሩ አዳጋች ከመሆኑም ሌላ፡ ሰላም ለማውረድ የሚያስችሉ ድርድሮች አዎንታዊ ውጤት የሚያስገኙበትን ዕድል ሊያሰናክል እንደሚችል ፕሮንክ ሥጋታቸውን ገልፀዋል።