1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተመድ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች ከስራ መታገድ

ረቡዕ፣ ሐምሌ 18 1999

የተመድ በአይቨሪ ኮስት በተሰማራው ሰላም አስከባሪ ሰራዊቱ ውስጥ የተሳተፉና የህጻናትን ክብረ ንጽህና ደፍረዋል የተባሉ ወደ ሰባት መቶ የሚጠጉ የሞሮኮ ወታደሮቹን ከስራ አገደ።

https://p.dw.com/p/E0ai
የአይቨሪ ኮስት ሰላም አስከባሪዎች
የአይቨሪ ኮስት ሰላም አስከባሪዎችምስል AP

በአፍሪቃ የዓለሙ መንግስታት ድርጅት ሰላም ማስከበር ተግባር በተስፋፋባቸው ባለፉት ዓመታት የወሲብ ወንጀል ቁጥርም ከፍ እያለ መምጣቱን የሚገልጹ በርካታ ዘገባዎች ወጥተዋል። በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሬፑብሊክ የተሰማሩ የሞሮኮ ወታደሮችም ተመሳሳይ ወንጀል እንደፈጸሙ ከተሰማ በኋላ፡ የሞሮኮ መንግስት ስድስቱን ከሁለት ዓመት በፊት በቁጥጥር አውሎዋል። የተመድ ይህን ዓይነቱን ወንጀል በቸልታ እንደማያልፈው አስታውቋል።

መጀመሪያ ላይ የአይቨሪ ኮስት ሰላም አስከባሪ አባላት የሆኑት የሞሮኮ ወታደሮች የህጻናትን ክብረ ንጽህና ደፈሩ የሚል ጭምጭምታ ነበር፤ ግን ጭምጭምታው በቀጠለበት ጊዜ የሰላም አስከባሪው ጓድ መሪዎች ወታደሮቹን ላልተወሰነ ጊዜ ከስራ ማገድ ተገደዱ። ወንጀሉ ባለፉት ሶስት ዓመታት ውስጥ እንደተፈጸመ ነው የተገለጸው። ይህ ዓይነቱ ወንጀል እንዳይፈጸም የሚረዳ ዘመቻ መጀመር አስፈላጊ መሆኑን የተመድ ቃል አቀባይ ሀማዱን ቱሬ አስረድተዋል።

« የገለጻው ዘመቻችን ለወታደሮቻችን፡ እንዲሁም፡ ለሀገሩ ህዝብም ነው የሚሰጠው። ወታደሮቹና ህዝቡ ማንኛውንም የክብረ ንጽህና መድፈር፡ የወሲብ ብዝበዛ፡ የበላይ ባለስልጣናት በስልጣናቸው አላግባብ የሚጠቀሙበትን ወይም ማንኛውንም ያልተስሰካከለ አሰራርን በሚመለከቱበት ጊዜ በይፋ ማስታወቅ እንዳለባቸው ዘመቻው ያስተምራል። »

በዓለሙ መንግስታት ጓድ ውስጥ ተስፋፋ የተባለው የክብረ ንጽህና መድፈሩ ወንጀል በተለይ የሞሮኮ ወታደሮችን የሚነካ ነው። በሰሜናዊ አይቨሪ ኮስት በምትገኘው የቡዋኬ ከተማሰባት መቶ ሰላሳ የሞሮኮ ወታደሮች የተሰማሩ ሲሆን፡ ከነርሱ መካከል አንዳንዶቹ ለአቅመ ሄዋን ካልደረሱ በርካታ ህጻናት ጋር የወሲብ ግንኙነት አድርገዋል የሚል ወቀሳ ተሰንዝሮባቸዋል፡እንደ ሀማዱን ቱሬ አባባል።

« ይህ የተሰነዘረው ወቀሳ እውነት መሆን አለመሆኑንን እናጣራለን። በአሁኑ ጊዜ አንድ ቡድን ወደቡዋኬ ልከናል፤ ቡድኑ እስካሁን ያሰባሰበው ውጤት በኮት ዲቯር ያለውን የተመድ የሰላም አስከባሪ ሰራዊትን ስራ ለጊዜው ያቋረጥንበትን ውሳኔ እንድንደርስ አድርጎናል። »
የተመድ በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሬፑብሊክ፡ በኮሶቮ፡ በላይቤሪያ እና በሄይቲ እአአ በ ሁለት ሺህ ዓመተ ምህረት፡ አሁን ደግሞ በአይቨሪ ኮስት ባሰማራቸው ሰላም አስከባሪ ወታደሮች ፈጸሙዋቸው በተባሉ የክብረ ንጽህና መድፈር ወይም ህጻናትን ለዝሙት ወይም ለወሲቡ ተግባር መጠቀም ሰበብ ብርቱ ወቀሳ ሲፈራረቅበት ይሰማል። የተመድ በአሁኑ ጊዜ የዓለም ሰላምን ለማስጠበቅ 100.000 አሰማርቶዋል። ከ 1994 ወዲህ በተሰማሩባቸው ቦታዎች ከሶስት መቶ የሚበልጡ የክብረ ንጽህና መድፈር ወንጀል መፈጸሙ ሲመዘገብ፡ ወደ ሰማንያ የሚጠጉ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች ጥፋተኛነታቸው ተረጋግጦ ፍርድ ተሰጥቶዋቸዋል። አሁን በአይቨሪ ኮስት በሞሮኮ ወታደሮች ላይ የተሰነዘረው ወቀሳ ብርቱ መዘዝ እንደሚኖረው የተመድ ቃል አቀባይ ቱሬ አመልክተዋል።
« ጥፋተኛነታቸው የተረጋገጠባቸው ወታደሮች ወደ ትውልድ ሀገራቸው ይላካሉ። የየሀገሮቻቸው መንግስትም ከፈጸሙት ወንጀል ጋር የሚመጣጠን ቅጣት መስጠት ይኖርባቸዋል። የእስራት ቅጣት ወይም ከጦር ኃይሉ የሚባረሩበት ቅጣት ሊሆን ይችላል፤ ይህ ግን እንደየሀገሩ አሰራር ይወሰናል። »
ጥፋተኛ ሆነው የሚገኙ ወታደሮች ከባድ ቅጣት ነው የሚጠብቃቸው፤ ምክንያቱም፡ የተሰነዘረው ወቀሳ በገጽታው ላይ ትልቅ ጉዳት የደረሰበትን የተመድ ሰላም ማስጠበቅ ዓላማን ይጻረራር።
በኮንጎ ደኤሞክራቲክ ሬፑብሊክ የተሰማሩት የተመድ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች በህገ ወጡ መንገድ ወርቅ ከዚችው ሀገር እያወጡ በህገ ወጡ የጦር መሳሪያ ንግድ እንደተሳተፉ ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ሂውማን ራይትስ ዎች ከአንድ ዓመት ተኩል ገደማ በፊት መረጃ ካወጣ በኋላ ምርመራ ተካሂዶ የምርመራው ውጤት ከጥቂት ጊዜ በፊት ይፋ ሆኖዋል፤ ይሁንና፡ አንድ የፓኪስታን ሰላም አስከባሪ ወታደር በህገ ወጡ የወርቅ ማውጣቱን እንጂ፡ አብሮ ስለቀረበው ህገ ወጡ የጦር መሳሪያ ንግድ አንድም ዝርዝር ዘገባ ያላቀረበበትን ውጤት ሂውማን ራይትስ ዎች አጠያይቆዋል።