1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተለያዩ ወገኖችን ያስተባበረ ፀረ መንግሥት ተቃውሞ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 3 2008

ሃሳብን የመግለፅ ነፃነትን፣ የፖለቲካ እስረኞች መፈታትን፣ የሥልጣን እና የሀብት ፍትሓዊ ክፍፍልን በመጠየቅ ባለፉት ቀናት አደባባይ በወጡ ሰላማዊ ተቃውሞ ሰልፈኞች ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ኃይል የታከለበት ርምጃ መውሰዱ ለብዙዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት ሆነ። ይህ የተለያየ አመላካከት ያላቸው ወገኖች በመንግሥት አንፃር እንዲተባበሩ አድርጓቸዋል።

https://p.dw.com/p/1JepK
Karte Äthiopien Amhara, Tigray, Oromia Deutsch

[No title]

በኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች በቀጠለው ፀረ መንግሥት ተቃውሞ ባለፈው ቅዳሜ በአዲስ አበባ ወደ አምስት መቶ የሚጠጉ ተቃዋሚዎች የፖሊስ ጥብቅ ቁጥጥርን ጥሰው በመሥቀል አደባባይ መውጣታቸው፣ በመንግሥቱ አንፃር ተቃውሞው ምን ያህል እያየለ መምጣቱን እና አዲስ ደረጃ ላይ መድረሱን እንዳሳየ የፖለቲካ ተንታኞች ተናግረዋል። የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ የጋራ ማስተር ፕላንን በመቃወም ባለፈው ህዳር ወር በኦሮሚያ ክልል ተቃውሞ ከተጀመረ ወዲህ ተቃዋሚዎች በመዲናይቱ በመሥቀል አደባባይ በብዛት ሲወጡ የሳምንቱ መጨረሻ የመጀመሪያ ነበር። እርግጥ፣ መንግሥት እቅዱን ቢሰረዝም፣ ብዙዎች፣ ጭቆና እንዲያበቃ፣ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ፣ ፍትሓዊ የስልጣን እና የሀብት ክፍፍል እንዲኖር፣ ሃሳብን በነፃ መግለፅ እንዲቻል፣ በፖለቲካ ውሳኔ ላይ ሁሉም ተሳታፊ እንዲሆን በመጠየቅ ተቃውሟቸውን አሁንም እንደቀጠሉ ይገኛል።
የፀጥታ ኃይላት በመሥቀል አደባባይ ባለፈው ቅዳሜ የተሰበሰበውን ሰልፈኛ በኃይል ርምጃ ከመበተናቸው ሌላ ከአስራ ሁለት የሚበልጡትን አስረዋል። የመብት ተሟጋቾች እንዳሉትም፣ በሳምንቱ መጨረሻ ብቻ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች በብዙ ከተሞች፣ መንግሥት «ሕገ ወጥ » ያላቸው ተቃውሞዎች ተካሂደው ብዙዎች ተገድለዋል። የዜና ወኪሎች በባህር ዳር ሰባት ሰዎች እንደተገደሉ ቢዘግቡም፣ የዓይን እማኞች የተገደሉትን ቁጥር ከ30 በላይ አድርሰውታል። በተለያዩት ተቃውሞዎች ምን ያህል ሰው መገደሉን በተመለከተ እስካሁን በይፋ የወጣ መረጃ የለም።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ባለፈው ዓርብ ተቃውሞ እንዳይደረግ ቢከለክሉም እና የፀጥታ ኃይላት እገዳውን በማያከብሩ ላይ አስፈላጊውን ርምጃ እንዲወስዱ ቢያዙም፣ በለንደን «ስኩል ኦፍ ኤኮኖሚክስ» የሰብዓዊ ጉዳዮች ተመራማሪ አቶ አዎል ቃሲም ይህ የሕዝቡን ሕገ መንግሥታዊ መብት የሚጥስ መሆኑን ነው ያስታወቁት።
« በሕገ መንግሥቱ መሰረት፣ ተቃዋሚ ሰልፈኞች አደባባይ እንደሚወጡ ማስታወቅ ብቻ ነው ያለባቸው። እና መንግሥት ተቃውሞ መውጣት እንደማይችሉ ቢከለክልም፣ አደባባይ ወጥተዋል። እና ይህ የቀድሞው የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ከሞቱ ወዲህ በሀገሪቱ ታሪክ የታየ ትርጉም ያለው ወሳኝ ለውጥ ነው። »
እንደ አቶ አዎል ቃሲም አስተሳሰብ፣ መንግሥት በተቃዋሚዎች ላይ የኃይል ርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ለደህንነታቸው ዋስትና መስጠት በተገባው ነበር። ይህን ግዴታውን በመወጣት ፈንታ ታድያ በተቃዋሚዎች ላይ የኃይል ርምጃ መጠቀሙ በፍፁም እንዳላስገረማቸው ነው አቶ አዎል የገለጹት።
«የኢትዮጵያ መንግሥት ሲጀመርም አንስቶ በኃይል ተግባር፣ በሙስና እና መሰል ዘዴዎች ላይ የሚተማመንጨቋን መንግሥት ነው። ይህን ያደረገው ደግሞ መላው የኢትዮጵያን ሕዝብ የማይወክል የውሁዳን መንግሥት በመሆኑ ነው። ስለዚህ ይህ ዓይነት ስርዓት ሕልውናውን ለማስጠበቅ ሲል የተለያዩ የቁጥጥር እና የጭቆና ዘዴዎችን መጠቀም ይኖርበታል። »
ምንም እንኳን ቢከለከሉም፣ በሳምንቱ መጨረሻ፣ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች በሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚ ሰልፈኞች አደባባይ መውጣታቸው ራሱ፣ ይላሉ አቶ አዎል ቃሲም ፣ በኢትዮጵያ ፣ የሕዝብ ጠንካራ ቁርጠኝነት የታየበት መሰረታዊ ለውጥ ገሀድ መሆኑን የጠቆመ እና በተለይ፣ የተለያየ የፖለቲካ ጥያቄ ያላቸው ወገኖች፣ ልዩነታቸውን ለጊዜው ወደ ጎን በማስቀመጥ፣ መንግሥት በሚከተለው የጭቆና ፖሊሲ እና በሰበቡ በተከተለው ማህበራዊ ኢፍትሃዊነት አንፃር እንዲተባበሩ ያደረገ ነው።

Äthiopien Protest
ምስል Reuters/T. Negeri

አርያም ተክሌ

ሂሩት መለሰ