1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቩልፍ የፍርድ ሂደት ፍፃሜ

ረቡዕ፣ ሰኔ 11 2006

የቀድሞውን የጀርመን ፕሬዝዳንት ክርስቲያን ቩልፍን በነፃ ባሰናበተው ብይን ላይ ይግባኝ ብሎ የነበረው ዐቃቤ ህግ ሐሳቡን ቀይሮ ይግባኙን በማንሳቱ የቩልፍ የፍርድ ሂደት አብቅቷል ።

https://p.dw.com/p/1CKjs
2014 Freispruch für Ex-Bundespräsident Christian Wulff
ምስል picture-alliance/dpa

የጀርመን ከፍተኛው የሥልጣን እርከን ላይ ደርሰው በተሰነዘሩባቸው ክሶች ምክንያት የሥልጣን ዘመናቸው ሳይፈጸም ለመሰናበት ቢገደዱም ለዚህ ካደረጓቸው ክሶች ነፃ መሆናቸው ተበይኖላቸዋል ። በጀርመን ታሪክ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ ፕሬዝዳንት ተከሶ ፍርድ ቤት ሲቀርብ እርሳቸው የመጀመሪያው ናቸው ። የቀድሞው የጀርመን ፕሬዝዳንት ክርስቲያን ቩልፍ ። ቩልፍ ከቀረቡባቸው ክሶች ነፃ ናቸው ሲል ሀኖቨር የተሰየመው ፍርድ ቤት ባለፈው የካቲት ነበር የወሰነው ። ከሳሽ አቃቤ ህግ ግን ይግባኝ ብሎ ነበር ። ሆኖም ባለፈው ሳምንት ሐሙስ የሆነቨር አቃብያነ ሕግ ይግባኙን ሲያነሱ የቩልፍ የክስ ሂደት ፍፃሜ አግኝቷል ።የ54 ዓመቱ ክርስቲያን ቩልፍ የጀርመን ርእሰ ብሔር ከመሆናቸው በፊት አንጌላ ሜርክል የሚመሩት የጀርመኑ የክርስቲያን ዲሞክራት ህብረት ፓርቲ አባልና የኒደርዛክሰን ተኋታይ ሳክሰኒፌደራዊ ክፍለ ግዛት ጠቅላይ ሚኒስትር ነበሩ ። ቩልፍ ያለመከሰስ መብታቸው ተነስቶ ከቀረቡባቸው ክሶች መካከል ዋነኛዎቹ የኒደርዛክሰን ፌደራዊ ክፍለ ሃገር ጠቅላይ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት ለመኖሪያ ቤት መግዢያ ከባንክ ከመበደር ይልቅ ከወዳጆቻቸው በአነስተኛ ወለድ ገንዘብ መውሰዳቸው እንዲሁም በአንድ ወቅት ያረፉበትን ሆቴል ሂሳብ ወዳጃቸው እንዲከፍሉ አደረጉ የሚሉት ይገኙበታል ።

ከሁሉም በላይ ቩልፍ ቢልድ ለተባለው እውቅ የጀርመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በርሳቸው ላይ ስለተሰነዘረ ወቀሳም ሆነ ክስ እንዳይፃፉ ተዉ የሚል ኃይለ ቃል የያዘ መልዕክት ነገሩን አባባሰ ። በስልክ የተዉት ኃይለ ቃል የያዘ መልዕክት ነገሩን አባባሰ ።ከዚያን ጊዜ አንስቶ በተከታታይ ስህተት ነው የተባለ ድርጊታቸው ሁሉ ከኃላ እየተመዘዘ መውጣት ጀመረ ። ከሥልጣን እንዲወርዱ የሚቀርበው ጥያቄም ተደጋግሞ መሰማቱ አላቆም ሲል ምርጫ ያጡት ቩልፍ ከሥልጣን ወረዱ ። ፍርድ ቤት ቀርበውም ጉዳዩን የተመለከተው የሃኖቨር ፍርድ ቤት በቀረቡባቸው ክሶች የፈፀሙት ወንንጀል መኖሩን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ባለማግኘቱ በነፃ አሰናበታቸው። የዛሬ 6 ዓመት ቩልፍ የኒደርዛክሰን ጠቅላይ ሚኒስትር ሳሉ ለፊልም ስራ የገንዘብ ድጋፍ የሚሰጡት ዴቪድ ግሮንቫልድ የተባሉት ባለጸጋ፣ በሙኒክ የጥቅምት የቢራ ፌሽታ በዓል ላይ በተገኙበት አጋጣሚ ያረፉበትን ሆቴል ሂሳብ በከፊል እንዲከፍሉ መፍቀዳቸው አቃቤያነ ህጉ ከየካቲቱ ብይን በኋላም ስህተት ነው በሚለው አቋማቸው በመፅናታቸው ይግባኝ እንደሚሉ አሳወቁ ባለፈው ሳምንት ግን ይግባኙን አነሱ።በወቅቱ ወዳጃቸው ለቩልፍ የሆቴል ወጪ የከፈሉት ወደ 754 ዩሮ ወይም 1021 ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ነው ። አቃቤያነ ህግ ባለፈው ሳምንት ይግባኙን ያነሱት በምን ምክንያት እንደሆነ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል ። ምክንያታቸው ባይገልፅም ቩልፍ ግን የማታ የማታ ረተው የጠፋውን ስማቸውን ለማደስና የቀድሞውንም ክብራቸውንም ለማስጠበቅ በቅተዋል ። የቩልፍ ጉዳይ የፍርዱ ሂደትና ፍጻሜው እዚህ ጀርመን ብዙ ሲያነጋግር ሰንብቷል ። ጀርመን ፍራንክፍርት ነዋሪ የሆኑት የህግ ባለሞያና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ ስለፍርዱ ሂደትና አቃቤ ህግ ይግባኙን ሊያነሳ የቻለበትን ምክንያት ያስረዳሉ ።

Ehemaliger Bundespräsident Christian Wulff stellt Buch vor "Ganz oben ganz unten"
ምስል picture-alliance/dpa

ቩልፍ አቃቤ ህግ ይግባኙን ከማንሳቱ ጥቂት ቀናት አስቀድሞ ባስመረቁት የፖለቲካ ህይወታቸውን ውጣ ወረድ ባሳዩበት መፀሃፋቸው ወግ አጥባቂ አቋም የሚያራምዱ ጋዜጦች ድራሻቸውን ለማጥፋት ቆርጠው ተነስተውባቸው እንደነበር በተካሄደባቸው የመገናኛ ብዙሃን ዘመቻም ፕሬዝዳንትነታቸው እንዳይዘልቅ መደረጉን አቃቤ ህግም ጉዳዩን እንዲያጣራ እጎአ የካቲት 2012 ከሥልጣን እንዲወርዱ ግፊት ማድረጋቸውንም ዘርዝረዋል ።ቩልፍ ክስ የተመሰረተባቸው ከስልጣን በወረዱ በዓመቱ ነበር ። ምንም እንኳን የኋላ የኋላ ንፅህናቸውበፍርድ ቤት ቢረጋገጥም የከፈሉት ዋጋና የደረሰባቸው ጉዳት ቀላል አልነበረም ። በግፊት ሥልጣናቸውን በአጠቃላይም የፖለቲካ ህይወታቸውን ከማጣታቸው በተጨማሪ ሁለተኛው ትዳራቸውም ፈርሷል ። አንዳንዶች አይወድቁ ውድቀት ለመውደቃቸው ምክንያት የግል ህይወታቸውን ከመጠን በላይ ለመገናኛ ብዙሃን ግልፅ ማድረጋቸው በተለይም ከርሳቸው በእድሜ ከሚያንሱት ዓይን ከሚጣልባቸው ባለቤታቸው ጋር የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሁሉ ትኩረት ውስጥ መግባቱ በቀላሉ ሊታለፉ የሚችሉትን ጉዳዮች እንዲጎሉ ማድረጋቸው ነው ይላሉ ። መገናኛ ብዙሃን የቩልፍን ጉዳይ አጋኖ በማቅረብ ጉዳዩ ከመጠን በላይ እንዲተኮርበት ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸው ብዙዎች ይስማማሉ ።

Christian Wulff Prozess 14.11.2013
ምስል Reuters

ዶክተር ለማ ይፍራሸዋም መገናኛ ብዙሃን የተጫወቱትን ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም ነው የሚሉትከፕሬዝዳንትነት ተገደው የወረዱት ቩልፍ 20 ሺህ ዩሮ ከከከፈሉ ጉዳያቸውን እንደማያነሳው አቃቤ ህግ ቢገልፅም ይህን ሳይቀበሉ በመቅረትንፁህነታቸውን ለማረጋገጥ በህዳር ወር ፍርድ ቤት ቀረቡ ። ሥልጣናቸውን አለአግባብ በመጠቀም ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ የገንዘብ ቅጣት ወይም የሶስት ዓመት እሥራት ነበር የሚጠብቃቸው ። ከዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ በኋላ በፍርድ ቤት ነፃ የወጡት የቀድሞው የጀርመን ፕሬዝዳንት ክርስቲያን ቩልፍ በሃሰት ሲጠፋ ለከረመው ስማቸው ታዲያ ካሳቸው ምን ይሆናል ?ቩልፍ ከአሁን በኋላ ወደ ፖለቲካ ዓለም የመመለስ እድልስ ይኖራቸው ይሆን ? ከድምጽ ዘገባዉ ያድምጡ፤

Deutschland Ex-Bundespräsident Wulff und Ehefrau Bettina trennen sich
ምስል picture-alliance/dpa

ሂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ