1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቦኮሃራም ጥያቄና የታገቱት ልጃገረዶች

ማክሰኞ፣ ግንቦት 5 2006

የናይጀሪያው የሙስሊም ፅንፈኛ ቡድን ቦኮ ሃራም ከትምህርት ቤት ያገታቸውን ልጃገረዶች ለመልቀቅ ያስቀመጠውን ቅድመ ሁኔታ የናይጀሪያ መንግሥት እንደማይቀበል አስታወቀ ። ቡድኑ ልጃገረዶቹን ለመልቀቅ የታሰሩበት ሚሊሽያዎች እንዲለቀቁ ያቀረበውን ጥያቄ የናይጀሪያ መንግሥት ውድቅ አድርጎታል ።

https://p.dw.com/p/1Byvx
Boko Haram Video 12.5.2014
ምስል picture alliance/abaca

ቦኮሃራም ትናንት ባሰራጨውና እስረኞቹ እንዲለቀቁ በጠየቀበት ቪድዮ ላይ የታገቱት ልጆገረዶች ታይተዋል ።የናይጀሪያን ደህንነት ስጋት ውስጥ የከተተው የቦኮሃራም እርምጃ የናይጀሪያን ጦር ኃይል ጥርጣሪ ውስጥ ጥሏል ። ቦኮ ሃራም በፈረንሳይ ዜና አገልግሎት በኩል ትናንት ባሰራጨው የ17 ደቂቃ ቪድዮ ወደ 100 የሚሆኑ ግራጫ ኒቃብ የለበሱ ልጃገረዶች የቁርአን ሐረጎች ሲያነቡ ታይተዋል በAFP ዘገባ መሠረት የናይጀሪያው ሙስሊም ፅንፈኛ ቡድን ቦኮሃራም መሪ አቡባካር ሼኩ በቪድዮው ላይ የታዩት ሚያዚያ 6 ፣2006 ዓም ከሰሜን ምሥራቅ ናይጀሪያ የቦርኖ ግዛት ስር ካለው ቺቦክ ከተማ ውስጥ ከሚገኝ ትምህርት ቤት ከታገቱት 233 ልጃገረድ ተማሪዎች መካከል የተወሰኑት መሆናቸውን ተናግሯል ። በወቅቱ ከታገቱት 276 ተማሪዎች መካከል አንዳንዶቹ ለማምለጥ ችለዋል ። ከተማሪዎቹ አብዛኛዎቹ ክርስቲያኖች መሆናቸው ተገልፆ ነበር ። ሼሁ በቪድዮው እንዳለው ልጃገረዶቹን አስልመዋቸዋል ። የሚለቋቸውም የታሰሩትን የቡድኑን አባላት መንግሥት ከፈታ ብቻ ነው ። ይኽው የቡድኑ መሪ ቀደም ሲል ልጃገረዶቹን ለባርነት እንደሚሸጣቸው ዝቶ ነበር ። ቦኮሃራም በመላ ናይጀሪያ በፈፀማቸው ልይ ልዩ ጥቃቶች የብዙ ሰዎች ህይወት ጠፍቷል፤ ንብረትም ወድሟል ። እስካሁን ድረስ ግን የናይጀሪያ ጦር ኃይል የቦኮ ሃራምን የጥቃት እርምጃ ማስቆም አልቻለም ። በዚህ የተነሳም ከጦር ኃይሉ የተወሰነው አካል ከአሸባሪው ከቦኮሃራምን ሳያተባበር አልቀርም የሚሉ ጥርጣሪዎች ይሰማሉ ። ከናይጀሪያው የአቡጃ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ጋርባ ኡመር ካሪ በዚህ ጥርጣሪ ላይ ለዶቼቬለ በሰጡት አስተያየት እርግጠኛ ሆኖ መናገር እንደማይቻል ነው የገለፁት ።

#BringBackOurGirls erster Tweet von Ibrahim M. Abdullahi
ምስል picture alliance/abaca

« አነዚህ አሉባልታዎች ናቸው ብዮ ነው የማምነው ። አሉባልታዎች እንዲሆኑም ነው የምፀልየው ። ምክንያቱም እውነት ከሆነ በጣም ከባድ ችግር አለ ። በናይጀሪያ ጦር ኃይል ውስጥ ሙስና ቸልተኝነት እንዲሁም ጦሩን ማስታጠቅ ያለመቻል ችግር እንዳለ አውቃለሁ ። ምንም እንኳን አንዳንድ ጥርጣሪዎች ቢኖሩም በበኩሌ በናይጀሪያ ጦር ኃይል ውስጥ ለቦኮሃራም የሚቆሙ ኃይሎች ስለመኖራቸው እርግጠኛ አይደለሁም ። ለኔ በተጨባጭ ይህ መደረጉን የሚያሳምን ነገር የለም ። »

ተንታኙ ካሪ ይህን ቢሉም በናይጀሪያ አሁን በተከሰተው የፀጥታ ችግር መንስኤ ከጦር ኃይሉ መካከል ተጠቃሚዎች መኖራቸውን ግን አልካዱም ።

«በርግጠኝነት ከዚህ የሚጠቀሙት ለናይጀሪያ ጥሩ የማይመኙት ናቸው ። አንደኛዎቹ ናይጀሪያ እንድትበታተን የሚፈልጉት ኃይሎች ናቸው ። እንደኔ ሌሎቹ ተጠቃሚዎች ደግሞ በናይጀሪያ ጦር ኃይል ውስጥ የሚገኙትና ከናይጀሪያ ወታደራዊ በጀት የሚቋደሱት ጀነራሎች በናይጀሪያ ጦር ኃይል ውስጥ ያሉ የበላይ አካላት ናቸው ።»

ካሪ እንዳሉት ባለፉት 3 ዓመታት ከናይጀሪያ በጀት ቢያንስ አንድ ሶስተኛው ለመከላከያ ነው የሚመደበው ። ይህም አንድ ትሪሊዮን ናይራ ወይም 5 ቢሊዮን ዩሮ ማለት ነው ።ይሁንና ወታደሮች በአግባቡ አልተያዝንም ሲሉ እያማረሩ ነው ይላሉ ካሪ ።

Boko Haram Video 12.5.2014
ምስል picture alliance/AP Photo

«በተለይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተደነገገባቸው ግዛቶች የተሰማሩ ተራ ወታደሮች ምሬታቸውን ይገልፃሉ ። ችላ እንደሚባሉ መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸው እንኳን እንደማይሟሉ አቤቱታ እያቀረቡ ነው »

ከዚህ ሌላ መንግሥት ችግሩን ለመፍታት ፈጥኖ ባለመንቀሳቀስ እየተወቀሰም ነው ። ናይጀያ ውስጥ ቦኮሃራም የጠለፋቸውን ልጃገረዶች ለመፈለግ ባለፉት ጥቂት ቀናት ዓለም ዓቀፍ ጥረት ተጀምሯል ። ብሪታኒያ ዩናይትድ ስቴትስና ፈረንሳይ በፍለጋው የናይጀሪያን ጦር የሚያግዙ ባለሞያዎች የሚገኙባቸው ቡድኖችና መሣሪዎች ልከዋል ። እስራኤልም በፍለጋው እየተሳተፈች ነው። መnንግሥት የታገቱት ልጃገረዶች አሁንም ናይጀሪያ ውስጥ ናቸው ይላል ። ተማሪዎቹ ምናልባት ወደ ቻድና ካሜሩን ሳይወሰዱ አልቀረም የሚለው ስጋት ግን አሁንም እንዳለ ነው ።

ሂሩት መለሰ

ነጋሽ መሀመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ