1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቦስኮ ንታጋንዳ እጅ መስጠት

ቅዳሜ፣ መጋቢት 14 2005

የዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ ዓማፅያን ቡድን መሪ ቦስኮ ንታንጋንዳ በቡድናቸው ውስጥ በተፈጠረው የሥልጣን ሽኩቻ ምክንያት ባለፈው ሰኞ ርዋንዳ በሚገኘው የዩኤስ አሜሪካ ኤምባሲ ተገን ጠየቁ። ዩኤስ አሜሪካ በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት የሚፈለጉትን ዓማፅያን ቡድን መሪ ለፍርድ ቤቱ ለማስረከብ ዝግጅት ጀምሮዋል።

https://p.dw.com/p/182us
ምስል Reuters

የምሥራቅ ኮንጎ ዓማፅያን ቡድን መሪ ቦስኮ ንታንጋንዳ  በኮንጎ የኢቱሪ ግዛት ውስጥ በስብዕና አንፃር ወንጀል ፈፅመዋል በሚል ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት ከሰባት ዓመታት በፊት የእሥር ትዕዛዝ ካስተላለፈበት ጊዜ አንስቶ ግለሰቡ ሳይያዙ በሰሜናዊ ኪቩ ግዛት በነፃ ሲንቀሳቀሱ ቆይተው ነበር። በሰሜናዊ ኪቩ እንደሚገኘው የሲቪክ ማህበረሰብ አስተባባሪና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ሙስጠፋ ምዊቲ አባባል፡ ቦስኮ ንታጋንዳ ግዙፍ ጥፋት ነው የፈፀሙት።
« በሕዝቡ ላይ ያደረሱት ጥፋት ግዙፍ ነው። ገድለዋል፡ ዘርፈዋል፡ ክብረ ንፅሕና እንዲደፈር አዘዋል። ሰዎች መጥተው በአንፃራቸው ቃላቸውን ከሰጡ ከፍርድ ያመልጣሉ ብየ አላስብም። » የኢቱሪ ወንጀል ብዙ ዓመታት ሆኖታል።
ለዚህም ነው ባለፈው ሰኞ ቦስኮ ንታጋንዳ በርዋንዳ ሳይታሰብ እጃቸውን መስጠታቸውን የዩኤስ አሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ቪክቶሪያ ኑላንድ ያስታወቁበት ድርጊት ብዙዎችን ያስገረመው።
« በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ የተላለፈባቸው እና ኤም-23 የሚባለው ያማፅያን ቡድን መሪ አንዱ የሆኑት ቦስኮ ንታጋንዳ ዛሬ ጥዋት ኪጋሊ ወደሚገኘው የዩኤስ ኤምባሲ መምጣታቸውን አረጋግጣለሁ። ዴን ኻግ ለሚገኘው ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት እንዲያስረክባቸውም ኤምባሲውን ጠይቀዋል። »
የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እስከዛሬ ተግባራዊ ላእሆነበት ድርጊት በተለያዩት የኮንጎ ቡድናት ያለው የኃይል ሚዛን ተጠያቂ ነው።  እርግጥ፡ ኮንጎ ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት ምሥረታን ያረጋገጠው የሮም ውል ተፈራራሚ እንደመሆንዋ መጠን ከፍርድ ቤቱ ጋ በመተባበር ንታጋንዳን ማስረከብ ይጠበቅባት ነበር። ግን የኮንጎ መንግሥት ንታጋንዳን ያን ያህል ጠንካራ ላልሆነው እና  እአአ መጋቢት 2009  ዓም ከኮንጎ መንግሥት ጋ ለተፈራረሙት የሰላም ውል ዘላቂ ህልውና ጠቃሚ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ ብሎ በማሰቡ ይህን አላደረገም። እንደሚታወቀው፡ በዚሁ አካባቢ ይንቀሳቀስ የነበረው በምሕፃሩ ሲ ኤን ዲ ፒ የተባለው ብሔራዊው የህዝብ ተከላካይ ኮንግረስ የሚሊሺያ ቡድን መሪ የነበሩት ትውልደ ርዋንዳ የሆኑት ቦስኮ ንታጋንዳ በምሥራቅ ኮንጎ የሚገኙትን የዉሁዳኑን የርዋንዳ ተወላጆችን ጥቅም ነው የሚያስጠብቁት።  በዚሁ ውል መሠረት፡ የሲ ኤን ዲ ፒ ዓማፅያን በመደበኛው የኮንጎ ጦር ውስጥ ተዋህደው፡ ንታጋንዳም በጦሩ ውስጥ የጀነራልነት ማዕረግ ሊይዙ ችለዋል። እንደሚታወሰው፡ ንታጋንዳ የሚሊሺያውን ቡድን መሪነት ሥልጣን የያዙት የቀድሞው የቡድኑ መሪ ሎውሮ ንኩንዳ እአአ በ 2009  ዓም መጀመሪያ ላይ በርዋንዳ የመታሰር ዕጣ ከገጠመቸው በኋላ ነበር። በዚሁ ጊዜ ብዙዎቹ ዓማፅያን፡ ታማኝነታቸውን ለታሰሩት ንኩንዳ በማሳየት፡ ንታጋንዳን ለንኩንዳ መታሰር ተጠያቂ አድርገዋል። በዚሁ ሰበብ የሲ ኤን ዲ ፒ ዓማፅያን በኮንጎ ጦር ከተዋኃዱም በኋላ በቀጠለው ውዝግብ የቀድሞ ዓማፅያን ከኮንጎ ጦር በመክዳት የ ኤም-23 አቋቋሙ። በዚሁ ጊዜ ከዓማፅያኑ ድጋፍ እንደሌላቸው የተረዱትና የኮንጎ መንግሥት ፕሬዚደንት ጆሴፍ ካቢላ በ 2012 ዓለም አቀፍ ግፊት ሲበረታባቸው ጀነራል ንታጋንዳ ለዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ለማስረከብ የቃጡበት ድርጊት የኮንጎ የሰላም ውል የማያስተማምን መሆኑ ታየ፡ በዚሁ ጊዜ ንታጋንዳ ከጦሩ ከድተው በመውጣት ሸሹ። ምክንያቱም፡ ይላሉ፡ በብሬመን ከተማ የሚገኙት ጀርመናዊው የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር አሌክስ ቫይት፡ ንታጋንዳ ሌሎች ያማፅያን መሪዎች ቀደም ባሉ ጊዚያት የገጠማቸውን መጥፎ ዕጣ በሚገባ ያውቃሉ።
« ሌሎች የደረሰባቸውን አይተዋል። ከኮንጎ መንግሥት ጋ የሰላም ውል ከተፈራረሙ በኋላ በኮንጎ ጦር ውስጥ ተዋህደው የነበሩት የቀድሞ ሚሊሺያ መሪ ንጉጁሎ ችዊ  ተይዘው ለፍርድ ቤቱ የተሰጡበትን ድርጊት ያዩት ንታጋንዳ ተመሳሳይ ዕጣ እስኪደርስብኝ አልጠብቅም። ያን ያህል ደደብ አይደለሁም »
ነበር ያሉት።
ንታጋንዳ አሁን እጃቸው  አሁን ለምን እንደሰጡ በግልጽ ባይታወቅም፡ ዕጣ ፈንታቸው የሚወሰነው በዴን ኻግ እንደሚሆን ይገመታል። ምክንያቱም፡ ዩኤስ አሜሪካ የሮሙ ውል ተፈራራሚ ባትሆንም፡ ከዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ጋ ለመተባበር ዝግጁነትዋን አሳይታለች። የሪፍት ቫሊ ተቋም የፖለቲካ ተንታኝ ጄሴን ስቴርንስ እንደሚሉትም፡ ርዋንዳም ሌላ አማራጭ አይኖራትም፡ ምክንያቱም፡
« የዩኤስ አሜሪካ እና የርዋንዳ መንግሥታት ፡ ኤምባሲው የሚገኘው ኪጋሊ በመሆኑ፡ ቦስኮ ንታጋንዳን ባፋጣኝ ለዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት ባፋጣኝ ማስረከብ ይቻል ዘንድ እንዲተባበሩ እንጠብቃለን። ንታጋንዳን ለኮንጎ የማያስረክቡ ከሆነ። ምክንያቱም በኒሁ ጦረኛ ላይ ክስ ተመሥርቶዋልና። »
በሰሜናዊ ኪቩ የሚገኘው የሲቪክ ማህበረሰብ አስተባባሪና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ሙስጠፋ ምዊቲም ተመሳሳይ አመለካከት ነው ያለው።
« ርዋንዳ የሮሙን ውል ባትፈርምም፡ ከጥቂት ጊዜ በፊት በአዲስ አበባ በፈረመችው ውል መሠረት፡ ማንም ያካባቢ ሀገር ከጎረቤት ሀገር የሚሄዱ ወንጀለኞችን ከለላ መስጠት የለባትም። »
በሰሜናዊ ኪቩ የሚገኘው የሲቪክ ማህበረሰብ አስተባባሪና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ሙስጠፋ ምዊቲ  እና የኢቱሪ ነዋሪዎች ቦስኮ ንታጋንዳ ለጥፋታቸው በዴን ኻግ የሚገባቸውን ብይን እንደሚያገኙ ተስፋ አድርገዋል።

Kongo Armee sucht nach Milizenchef Bosco Ntaganda
ምስል Reuters
Karte Grenzgebiet Demokratische Republik Kongo Ruanda
ምስል DW
Kongo Armee sucht nach Milizenchef Bosco Ntaganda
ምስል dapd

አርያም ተክሌ

መሥፍን መኮንን

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ