1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የብሪታንያ ምርጫ

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 26 2002

በብሪታንያ የትላልቆቹ ፓርቲዎች መሪዎች መራጩን ህዝብ ለመሳብ ብቻ ሳይሆን፡ አንዱ ሌላውን ለማግባባት ወይም ለመውቀስ በመሞከር ላይ ናቸው።

https://p.dw.com/p/NE74
ምስል AP

በተለይ በህዝብ አስተያየት መመዘኛ መዘርዝር ውስጥ በሶስተኛነት የሚገኙት የሌበር መሪና ጠቅላይ ሚንስትር ጎርደን ብራውን የለዘብተኛ ዴሞክራቶቹ የምርጫ ተሀድሶ እንዲደረግ ያቀረበውን ሀሳብ በመደገፍ፡ ከምርጫ በኋላ ከስምምነት መድረስ እንደሚችሉ ለመግለጽ እየሞከሩ ነው።

« አዲስ ዓይነት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፡ አዲስ ዓይነት የህግ መወሰኛ ምክር ቤት ማየት እንፈልጋለን። በዚሁ ጥያቄ ላይ ህዝበ ውሳኔ ለማካሄድ ዝግጁ ነን። ወግ አጥባቂዎቹ እንደማይደግፉት አውቃለሁ። ለዘብተኞቹ ይደግፉታል ብየ ተስፋ አደርጋለሁ። እና በዚሁ ጉዳይ ላይ የምንጋራው ነገር አለ። »

እስካሁን በሚሰራበት የምርጫ ስርዓት አንድ ፓርቲ ዕጩዎቹ ከሌሎቹ ፓርቲዎች ይበልጥ ብዙ የምርጫ ቀጣናዎችን ካሸነፉ አሸናፊ ይባላል። ይህ ግን በመላ አገሪቱ የብዙ መራጮችን ድምጽ አግኝቷል ማለት አይደለም።

Parlament in London, Großbritannien
ምስል AP

አንድ ሌላ ትልቅ ፓርቲ በሁሉም ባይሆን በብዙዎቹ ትላልቅ የምርጫ ቀጣናዎች የብዙ መራጭ ድምጽ ሊያገኝ ይችላል። በዚህም የተነሳ ብዙ ቀጣናዎችን ካሸነፈው ፓርቲ ያነሰ መንበር ይይዛል። በብዙ ቀጣናዎች የሁለተኛነቱን ቦታ በመያዝ አዝማማሚያ ካይ የሚገኘዉ የለዘብተኛው ዴሞክራቶች ፓርቲ አሸናፊ ባለመሆኑ ያገኘው የመራጭ ድምጽ ሁሉ ለሌበር ወይም ለወግ አጥባቂው ይሰጥበታል።

በምርጫው ሂደት ላይ ኒክ ክሌግ እንደሚጥሩት ተሀድሶ ከተደረገ ግን ፓርቲዎች የሚያገኙት ድምጽ ነው በምክር ቤት የሚይዙትን መንበር ቁጥር የሚወስነው።

ይህም በሌበር እና በለዘብተኛ ዴሞክራቶች ፓርቲ መካከል አንድ የመሀል ግራ ጥምር መንግስት የሚቋቋምበትን መንገድ ሊከፍት ይችላል።

የለዘብተኛው ዴሞክራት ፓርቲ መሪ ኒክ ክሌግ ግን ጎርደን ብራውን ለዘብተኞቹን ዴሞክራቶች ለማግባባት ያደረጉትን ሙከራ በፍጹም ቦታ አልሰጡት።

« እንደማስበው፡ በወቅቱ ራሳቸውን የለውጥ ሐዋርያት አድርገው ማቅረብ የያዙት የሌበር ፓርቲ እና መሪው ጎርደን ተስፋ የቆረጡ ይመስለኛል። »

የክሌግ አነጋገር ከወግ አጥባቂዎቹ ጋር ለመስራት የቀረበ ሀሳብ መስሎ ታይቷል፤ ሆኖም ከሌላ ፓርቲ ጋር መጣመር የሚለው ሀሳብ ከጥያቄ ውጭ ነው ለሚሉት ለዴቪድ ካሜሮን በፍጹም ተቀባይነት የለውም።

የአንድም ፓርቲ የብዙኃን መራጮች ድምጽ የሌለበት ምክር ቤት የመነታረኪያ፤ የመከራከሪያ፡ ቦታ ነው የሚሆነው።

የወግ አጥባቂው ፓርቲ ቃል አቀባይ ኬን ክላርክ እንደሚሉትም፡ ይህ ዓይነቱ ፓርቲዎች ተጣምረው የሚሰሩበት ሁኔታ በሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት ላይ በቀላሉ የማይገመት መዘዝ ያስከትላል። ይህ ከሆነ ብሪታንያ ልክ እአአ በ 1976ዓም የተደረገላትን ዓይነት የፊናንስ ርዳታ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ መርህ ድርጅት ማግኘት ያስፈልጋታል። ይሁንና አንዱም የብዙኃኑን የመራጭ ድምጽ በማያገኝበት ሁኔታ ይበልጥ ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉት ለዘብተኞቹ ዴሞክራቶች የሀገሪቱ ሸርፍ ፓውንድን እና የሀገሪቱን ኤኮኖሚ ውድቀት ያስከትላል የሚለውን ሀሳብ አጣጥለውታል። አንዳንድ የምጣኔ ሀብት ጠበብት ይህንኑ አባባል ይደግፉታል። ፓርቲዎች በምክር ቤቶች ውስጥ የብዙኃኑን የመራጭ ድምጽ ያላገኙባቸው በርካታ ምሳሌዎችም አሉ።

በወቅቱ የህዝብ አስተያየት መለኪያ መዘርዝሮች እንደሚጥቁሙት፡ ብዙኃኑ የብሪታንያ መራጮች የሚፈልጉትም ጥምር መንግስት ነው። ፓርቲዎቹ በጋራ ተባብረው ብሪታንያን ከምትገኝበት አዳጋች ኤኮኖሚያዊ ሁኔታ እንዲያላቅቁ፡ ማለትም የበጀት ሚዛን ጉድለትዋን እንዲያስተካክሉ ይሻሉ።

አርያም ተክሌ

ሸዋዬ ለገሠ