1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የባርነት ስርዓት በሞሪታንያ

ቅዳሜ፣ ኅዳር 27 2007

በይፋ ለሦስት ጊዜያት እንደተገረሰሰ ቢነገርም፥ ዛሬም ቢሆን በሞሪታንያ የባርነት ስርዓት ጭቆና አልተወገደም። የዕድሜያቸውን እኩሌታ በባርነት ቀንበር ሲማቅቁ የነበሩ አንድ ሞሪታኒያዊ ትውስታቸውን ያካፍላሉ። በመካከለኛው አፍሪቃ ሪፐብሊክ የሰፈረው የፈረንሣይ ጦር ሠላም ማስፈን ተስኖታል እየተባለ ነው።

https://p.dw.com/p/1E0Bh
የፀረ-ባርነት ተሟጋቾች፤ ቢራም አባይድ ከመሀከል
የፀረ-ባርነት ተሟጋቾች፤ ቢራም አባይድ ከመሀከልምስል AFP/GettyImages

ሞሪታንያ በሰሜን ምዕራብ አፍሪቃ የምትገኝ ሀገር ናት። ቢላል 50 ዓመታቸው ነው። የዕድሜያቸውን አጋማሽ የፈጁት ግን በባርነት ቀንበር ተውጠው ነው። በባርነት ቀጥቅጠው ይገዟቸው የነበሩ የቀድሞ አሳዳሪያቸው ከብቶችን ላለማሠማራትም ሆነ በሌሎች ከባድ ሥራዎች ላለመበዝበዝ «እምቢኝ!» ማለት ነበረባቸው። ከአሳዳሪያቸው ሰባራ ሣንቲም አያገኙም፤ ይልቁንስ ሠርክ የተረፋቸው መገረፍ ነበር። የሦስት ልጆች አባት የሆኑት ቢላል ሁሉን እንዲህ መለስ ብለው ያስታውሳሉ።

«ከቤተሰቦቼ ጋር ለማሳለፍ በቂ ጊዜ አልነበረኝም። ኹለቱም እንደ እኔው ባሮች ነበሩ። አንድ ቀን ከቤተሰቦቼ ጋር ለማሳለፍ ተሰውሬ ብሄድ እናቴ በአስቸኳይ ወደ አሣዳሪዎቼ ቤት እንድመለስ አዘዘችኝ። ልጄ፦ የአንተ ሠላም እና ደስታ በአሣዳሪዎችህ እግር ስር ነው ያለው አለችኝ»

በሞሪታንያ የመብት ተሟጋቹ ቢራም አባይድ
በሞሪታንያ የመብት ተሟጋቹ ቢራም አባይድምስል picture-alliance/dpa

ቢላል በሞሪታንያ ሥር የሰደደው የባርያ አሣዳሪ ልማድ ሰለባነታቸው ጎልቶ የሚወጣው ራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን «ባሮች» እያሉ መግለጣቸው ነው። ውቢላል ሠላም እና ደስታቸውን በስተመጨረሻም ቢሆን አግኝተዋል፤ በነፃነት ውስጥ። ካለፉት አምስት ዓመታት አንስቶ የራሳቸው በሆነ ቤት ውስጥ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እየኖሩ ነው።

ባርነት በሞሪታንያ በእርግጥ በይፋ እንደተወገደ ይነገራል። በእውነታው ዓለም ግን ገና ሙሉ ለሙሉ አልተወገደም። ለዚያም ነው የሰብዓዊ መብቶች ተቆርቋሪው ቢራም አባይድ የባርነት ብዝበዛን በመቃወም ጥሪያቸውን የሚያስተላልፉት። ቢላል ለመብታቸው ተሟግተው ከባርነት ቀንበር እንዲላቀቁ ረድተዋቸዋል።

«20 በመቶው የሞሪታኒያ ሕዝብ በባርነት መገዛት የሚገባቸው ከሚባሉት ቤተሰቦች ነው የሚመደቡት። እነዚህ ጥቁር ሞሪታኒያውያን ገና ከመወለዳቸው አንስቶ የቆዳ ቀለማቸው ፈካ ያለውና የዓረብ በርበር ዝርያ ያላቸው ሞሪታኒያውያን ንብረት እንደሆኑ ነው የሚቆጠረው።»

የመብት ተሟጋቹ ቢራም የተቃውሞ ሰልፎችን ያስተባብራሉ፤ ቀድሞ በባርነት ይማቅቁ የነበሩ ሰዎች አዲስ መጠለያ እንዲያገኙ የተቻላቸውን ጥረት ያደርጋሉ። ለዚህ ተግባራቸውም ከተመድ እና ከጀርመኑ ቫይማር ከተማ ሽልማቶችን አግኝተዋል። ቢራም ራሳቸው በባርነት መገዛት የሚገባቸው ከሚባሉት ቤተሰቦች ነው የሚመደቡት። በሞሪታኒያ የሚኖሩ የዓረብ በርበር ዝርያ ያላቸው፣ በቆዳ ቀለማቸው ትንሽ ፈካ ያሉ ነዋሪዎች፤ ጠቆር እና ጠየም ያሉ የሀገሪቱ ዜጎችን ከእኛ ታንሳላችሁ በሚል የዘረኝነት ስሜት በእዚህ በ21ኛው ክፍለዘመን የባሪያ ፍንገላ ያኪያሂዳሉ።

የባርነት ሥርዓት በሞሪታኒያ
የባርነት ሥርዓት በሞሪታኒያምስል Robert Asher

የሞሪታኒያ ማኅበረሰብ በዘር ሐረግ አንዱን ከአንዱ የማበላለጥ ልማድ አለው። አንዳንዶቹ «ጌቶች» ከሚባሉ ቤተሰቦች የሚወለዱ ሲሆን፤ ሌሎች ደግሞ በዘር ግንዳቸው ብቻ «ባሪያ» ተደርገው ይቆጠራሉ። ልክ አሁን ነፃነታቸውን እንደተቀዳጁት ቢላል። በእርግጥ ቢላል አሁን ነፃ ቢሆኑም መብቶች ግን የሏቸውም።

«የቀድሞ አሣዳሪዬን በተመለከተ ለፖሊስ አመልክቼ ነበር። ፖሊስ አሳዳሪዬን ወደ ጣቢያ እንዲቀርብ አድርጎ ምናልባት ወደፊት ዳግም የማመልከት ዐሳብ ቢኖረኝ እንዲቀጠቅጠኝ መክሮ ሰደደው። ለእኔ ግን ፖሊሱ እንደ ቢራም ያሉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ጋር የመቅረብ ፍላጎት ካለኝ ለእዛ መዘጋጀት እንደሚገባኝ ነው የነገረኝ»

እንደ ቢላል ያሉ ሰዎች መብታቸውን እንዲጎናጸፉ መርዳት ያሻል። ይኽ የሞሪታኒያም ሆነ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ግብ ነው።

«እንደ እኛ ዐሳብ ከሆነ የቀድሞ በባርነት ተበዝባዦች እና የባርነት ሠለባዎች ባርነት በሚከለክለው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ መሠረት ወደ ፍርድ ቤት መቅረብ የሚችሉበትን ሁናቴ ማመቻቸት መቻል ይኖርብናል። በተጨማሪም በፍትኃ-ብሔር ሕጉ መሠረት ለምሳሌ የጉዳት ካሳ የሚያገኙበት እና ሌሎች ጉዳዮችን አንስተው የሚከሱበት መንገድ ሊመቻች ይገባል።»

ምንም እንኳን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የተቻላቸውን ያኽል ጥረት ቢያደርጉም፤ የሞሪታኒያ ማኅበረሰብ በቤተሰብ እና በዘር ቆጠራ አንዱን ከአንዱ ከማበላለጥ አልተቆጠበም። ይፋ በሆነ መልኩ ባርነት እና የባርነት ተግባር በሞሪታኒያ መወገዱ ከአንዴም ሦስቴ ታውጇል። መንግሥት ባርነትን በመዋጋቱ ሂደት እመርታ ማሳየቱን ይገልጣል። ይሁንና እንደ ቢላል ያሉ ሰዎች ግን ዛሬም ድረስ መብታቸውን አሳልፈው ሲሰጡ ይሰተዋላል።

«ኪሎ ሜትር አምስት» የሚባለው ሠፈር ከፊል ገጽታ
«ኪሎ ሜትር አምስት» የሚባለው ሠፈር ከፊል ገጽታምስል F.Daufour/AFP/GettyImages

በመካከለኛው አፍሪቃ ሪፐብሊክ መዲና ባንጉዊ ውስጥ የሚገኘው «ኪሎ ሜትር አምስት» የሚባለው ሠፈር፤ «የሙስሊም ደሴት»፣ «በአውላላው ሠማይ እስር ቤት»፣ የጀሐዲስቶች መሸሸጊያ» የተሰኙ እና ሌሎችም በርካታ ስሞች አሉት። በአብላጫው ክርስቲያን ማኅበረሰብ በሚኖርባት ከተማ፥ ይኽ ሠፈር የሙስሊሞች መጠለያ ነው። ከኹለት ዓመታት ግድም በፊት ሴሌካ የተሰኘው የሙስሊም አማፂያን ጥምረት ሀገሪቱን ለመቆጣጠር እንቅስቃሴ ካደረገበት ጊዜ አንስቶ መካከለኛው አፍሪቃ ሪፐብሊክ ውስጥ በሃይማኖት የተነሳ ውዝግቡ ተባብሷል። ከእዚያን ጊዜ ጀርምሮ በተቀሰቀሰ የእርስ በእርስ ጦርነት 6000 ያኽል ሰዎች ተግድለዋል። ግማሽ ያኽሉ የሀገሪቱ ነዋሪ ቤት ንብረቱን ጣጥሎ ሕይወቱን ለማትረፍ ሸሽቷል።

የንግድ እንቅስቃሴዎች ጎልተው ይታዩበት የነበረው «ኪሎ ሜትር አምስት» የሚባለው ሠፈር በግጭቱ በአያሌው ተጎድቷል። ሠፈሩ እንደቀድሞው ለመረጋጋት ረዥም ጊዜ ይፈልጋል። «አንድ ላይ መኖራችን፥ በጋራ ለመበልጸግ ዕድላችን» ይላል ግባያ ዶምቢያ በሚባለው ትምህርት ቤት ቅፅር ግቢ ግንብ ላይ በግልፅ የሚታየው ጽሑፍ። ትምህርት ቤቱ የአካባቢው ነዋሪዎችን በማስተባበር የተለያዩ እምነት ተከታዮችን ለማቀራረብ ይጥራል። ከመርሐ-ግብሩ ውስጥ በክርስቲያኖች እና በሙስሊሞች መካከል የሚከናወን የእግር ኳስ ጨዋታ ይገኝበታል። በክንፍ በኩል የሚጫወተው ሙስሊም ነዋሪ አዶላዬ ያያ።

«የምናፍቀው ሠላም በመሆኑ እግር ኳስ እጫወታለሁ። እኛ የምንሻው ሠላም እንጂ ጠብ አይደለም። መሣሪያ እና ቦንቦች ብትታጠቁ እንኳ፤ ይኹን ግድ የለም። አምስት ኪሎሜትር ሠፈር ቤታችሁ ነው።»

በትምህርት ቤቱ ግንብ ላይ በግልጽ እንዲታይ ተደርጎ የተሰቀለው ሌላኛው ጽሑፍ ደግሞ፦ «እናመሰግናለን ሣንጋሪ፣ EUFOR እና MINUSCA» ይላል። ሣንጋሪ ፈረንሣይ ወደ ባንጉዊ የላከችው ወታደራዊ ተልዕኮ ስያሜ ነው። ሌሎቹም መካከለኛው አፍሪቃ ከተዘፈቀችበት ቀውስ እንድትወጣ ለመርዳት ወደ ሀገሪቱ የገቡ ዓለምአቀፍ ወታደራዊ ተልዕኮዎች ናቸው። የፈረንሣዩ ሣንጋሪ በ1600 ከፈረንሣይ የተላኩ ወታደሮች ተዕልኮውን በይፋ የጀመረው እጎአ 2013 መገባደጃ ላይ ነበር። በወቅቱ ሠብዓዊ ቀውስ ለመከላከል በሚል ፕሬዚዳንት ፍራንሷ ከፈረንሣይ የላኳቸው ወታደሮች ተልዕኮ በአጭር ጊዜ የሚወሰን እንደነበር ቃል መግባታቸው ይታወሳል። አሁን ወታደሮቹ መካከለኛው አፍሪቃ ሪፐብሊክ ከገቡ አንድ ዓመት ሆኗቸዋል ማለት ነው።

ሣንጋሪ የተባለው የፈረንሣይ ተልዕኮ በሙስሊሞች ዘንድ የክርስቲያኖቹ ፀረ-ባላካ ሚሊሺያ ደጋፊ ነው በሚል ይወቀሳል። አንዳንድ ግድግዳዎች ላይ የተጻፉ ጽሑፎች «እምቢ ለፈረንሣይ፤ እምቢ ለሣንጋሪ» የሚሉ መልእክቶችን የያዙ ናቸው። የኦካፒ የማማከር ሥራ ድርጅት ኃላፊ እና የመካከለኛው አፍሪቃ ሪፐብሊክ ጉዳዮች ተንታኝ ዳቪድ ስሚዝ የፈረንሣይ ወታደራዊ ተልዕኮ ባይኖር የሚከሰተው የከፋ እንደነበር ይገልጣሉ።

የፈረንሣይ ወታደሮች የ«የሣንጋሪ ተልዕኮ» በሞሪታንያ
የፈረንሣይ ወታደሮች የ«የሣንጋሪ ተልዕኮ» በሞሪታንያምስል Pacome Pabandji/AFP/Getty Images

« በሀገሪቱ በስተምዕራብ በኩል እንደ ቦዳ ከተማ ባሉ አንዳንድ ቦታዎች ላይ የሳንጋሪ ተልዕኮ ባይኖር ኖሮ የሙስሊሙ ማኅበረሰብ በአጠቃላይ እልቂት ተከስቶበት ነበር»

በእርግጥ ይላሉ ዳቪድ፤ በመካከለኛው አፍሪቃ ሪፐብሊክ የሚገኙ የዓለም አቀፉ ወታደሮች ብዙ ነገሮችን ማድረግ አይችሉም። ዴቪድ ወታደሮቹን በተመለከተ «ምናልባት የታጠቁ ቡድኖችን መገላገል ይችሉ ይሆናል፤ ያ ግን ዘላቂ ሰላም አያመጣም» ሲሉ ይተቻሉ።

የፈረንሣይ ወታደራዊ ተልዕኮ በቦታው ሥራ ከጀመረ አንድ ዓመት ተቆጥሮም እንኳ የተልዕኮው ይዘት አልተቀየረም ይላሉ ዴቪድ። ሀገሪቱን አረጋግቶ ሊያቆይ የሚችል በቂ ወታደራዊ ኃይል የለም። በርካቶቹ የቀድሞው ወታደሮች ጫካ ገብተው የተለያዩ አማፂያንን እንደተቀላቀሉ ይነገራል። ቀድሞ በዓማፂያን ንቅናቄ ውስጥ የነበሩ ዕጩዎች እጎአ በ2015 ዓም ሊካሄድ በታቀደው ሀገር አቀፍ ምርጫ ሊቀርቡ ይችሉ ይኾናል በሚል መስጋታቸውን ዴቪድ ይጠቁማሉ። በእዚህም አለ በእዚያ ግን ምርጫው መከናወን አለበት ባይ ናቸው።

«በመካከለኛው አፍሪቃ ሪፐብሊክ የቱንም ያህል ሊጭበረበር የሚችል ምርጫ ቢሆን እንኳ፤ ያው መጭበርበሩ አይቀርም፤ መካከለኛው አፍሪቃ ሪፐብሊክ አይታው የማታውቀውን፥ ሆኖም በየትኛውም ሉዓላዊ ሀገር የሚኖረውን፥ ተቋማትን ለመገንባት ወደ ቀጣዩ ደረጃ የሚያሻግረውን ምርጫ ማከናወን ያስፈልጋል»

በመጪው የካቲት ይኪያሄዳል ተብሎ ዕቅድ የተያዘለት ምርጫ ሊዘገይ እንደሚችልም ተነግሯል። የመካከለኛው አፍሪቃ ሪፐብሊክ ጊዜያዊ መንግሥት ፕሬዚዳንቲት ካተሪን ሳምባ ፓንዛ በምርጫው አሸናፊ ለሆነው ዕጩ ሥልጣኑን እንዲያስረክቡም ነው ዕቅድ የተያዘው። የመካከለኛው አፍሪቃ ሪፐብሊክ ተንታኝ ዴቪድ ሀገሪቱ ቀደም ሲል ወደ እርስ በእርስ መተላለቅ በመሯት ሰዎች ልትመራ ትችል ይሆናል የሚል ስጋትም አላቸው። እነዚያ ሰዎች ምናልባት በምርጫ ወደ ሥልጣን መንበሩ ከቀረቡ ማለት ነው።

በዚህም አለ በዚያ ግን በመካከለኛው አፍሪቃ ሪፐብሊክ ተመርጦ ሥልጣን የሚይዘው አካል በርካታ ችግሮች ከፊት ለፊቱ ይጠብቁታል። በአሁኑ ወቅት ባንጉዊ የሚገኘው መንግሥት የሀገሪቱ ሰሜናዊ ሰፋፊ ክፍሎችን መቆጣጠር አልቻለም። ራሱን ችሎ የሚቆም አስተዳደራዊ መዋቅርም እስካሁን አልተዘረጋም። ሰላም የሰፈነበት አስተማማን ኑሮ ለመካከለኛው አፍሪቃ ሪፐብሊክ ነዋሪዎች ዛሬም የማይታሰብ ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ተክሌ የኋላ