1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

የባለድርሻዎች ስንብት

ረቡዕ፣ ኅዳር 14 2009

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጥቅምት 22 ቀን 2009 ዓ.ም. በፃፈው መመሪያ የኢትዮጵያ ዜግነት የሌላቸው ግለሰቦች በባንኮች እና የመድን ሽፋን ሰጪ ኩባንያዎች ውስጥ ያላቸውን የባለቤትነት ድርሻ እንዲመልሱ ትዕዛዝ አስተላልፏል።

https://p.dw.com/p/2T8TB
Äthiopien Enat Bank
ምስል DW/Y. G. Egziabher

Wirtschaft፤ Government to Impound Dividend of Ethiopian Origins 23.11.2016 - MP3-Stereo

የኢትዮጵያ ባንኮች እና የመድን ሽፋን አቅራቢ ኩባንያዎች የውጭ አገር ዜግነት ያላቸውን ባለ አክሲዮኖች በጋዜጣ ማስታወቂያዎች እየጠሩ ነው። አቢሲኒያ ፤ አንበሳ ኢንተርናሽናል ፤ ብርሃን ኢንተርናሽናል፤ ዘመን እና ዳሸን ባንኮች በዚህ ሳምንት ለአንባብያን በደረሱት የአዲስ ፎርቹን እና ሪፖርተር ጋዜጦች የሌላ አገር ዜግነት ላላቸው ባለድርሻዎቻቸው ጥሪ ካቀረቡት መካከል ይገኙበታል። ከመድን ሽፋን አቅራቢዎች መካከል ንብ እና ዓባይ ኢንሹራንስም ተመሳሳይ ርምጃ ወስደዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጥቅምት 22 ቀን 2009 ዓ.ም. በፃፈው መመሪያ የኢትዮጵያ ዜግነት የሌላቸው ግለሰቦች በባንኮች እና የመድን ሽፋን ሰጪ ኩባንያዎች ውስጥ ያላቸውን የባለቤትነት ድርሻ እንዲመልሱ ትዕዛዝ አስተላልፏል። መመሪያው ባለድርሻዎቹ ያላቸው የአክሲዮን ተመን እና ትርፍ እስከ እስከ መጪው ሰኔ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ እንዲከፈላቸው አዟል። ለመሆኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያወጣው መመሪያ የሚመለከተው ማንን ነው? አቶ አብዱልመናን መሐመድ ሐምዛ የኢትዮጵያ ባንኮችን በቅርበት የሚከታተሉ ባለሙያ ናቸው። በዩናይትድ ኪንግደም ፖርትቤሎ በተሰኘ ኩባንያ የአካውንቲግ ኃላፊ ሆነው በመሥራት ላይ የሚገኙት አቶ አብዱልመናን ሞሐመድ የሌላ አገር ዜግነት ያላቸው ባለአክሲዮኖች በዘርፉ ያላቸው ድርሻ ከአንድ በመቶ አይበልጥም ሲሉ ይናገራሉ።

የባንክ ሥራ አዋጅ ቁጥር 592/2000  የሌላ አገር ዜጎች በኢትዮጵያ ባንክ መመሥረት እንደማይችሉ ይደነግጋል። «የውጭ ሀገር ዜጎች ወይም በከፊልም ሆነ በሙሉ በውጭ ሀገር ዜጎች ባለቤትነት ሥር ያሉ ድርጅቶች ወይም የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ ውስጥ ባንኮች ወይም የባንክ ቅርንጫፎች ሊያቋቁሙ አይችሉም፤ በኢትዮጵያ ውስጥ በተቋቋሙ ባንኮች አክሲዮን መያዝ አይችሉም» የሚለው አዋጅ ገቢራዊ ከሆነ አመታት ተቆጥረዋል። አቶ አብዱልመናን አሁን የኢትዮጵያ መንግስት ይፋ ያደረገው መመሪያ ህጉን ለማስፈጸም ያቀደ ነው ሲሉ ይናገራሉ።

Addis Ababa (Äthiopien)
ምስል picture alliance/landov

የዜጎችን አመታዊ ገቢ መካከለኛ ደረጃ ካሉ የዓለም አገራት ጎራ ለማድረስ ያቀደው የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፉት አመታት ሰፊ የመሰረተ-ልማት ግንባታዎች ላይ አተኩራል። የመንግሥት ግዙፍ እቅዶች አማራጭ የፋይናንስ ምንጭ ቢያስፈልጋቸውም የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት የውጭ አገር ባንኮች በአገሪቱ እንዲሰማሩ ፈቃደኛ አይደሉም።

የኢትዮጵያ የንግድ ሚዛን ከፍተኛ ጉድለት ይታይበታል። በአብዛኛው ጥሬ የግብርና ምርቶችን ወደ ውጭ የምትልከው ኢትዮጵያ በዓመት ወደ 3 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገቢ ታገኛለች። በአንፃሩ ከውጭ ለምታስገባቸው ምርቶች እስከ 10 ቢሊዮን ዶላር ታወጣለች። የአገሪቱ የወጪ እና ገቢ ንግድ ሚዛን መዛባትን ለማስተካከል አማራጭ የፋይናንስ ተቋማት በኢትዮጵያ ገበያ ቢሰማሩ ያዋጣል የሚሉ ባለሙያዎች አልጠፉም። የዓለም ባንክ እና የዓለም የገንዘብ ድርጅትን የመሳሰሉ የኢትዮጵያ አበዳሪዎችም መንግስት ዘርፉን ለውጭ ባለወረቶች ክፍት እንዲያደርግ ይወተውታሉ። አቶ አብዱልመናን የኢትዮጵያ የባንክ አገልግሎት «ጥርቅም» ተደርጎ ተዘግቷል ሲሉ ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከሶስት ዓመት በፊት ይፋ ያደረገው የዲያስፖራ ፖሊሲ ከ2 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በሰሜን አሜሪካ፤ አውሮጳ፤መካከለኛው ምሥራቅ፤ አውስትራሊያ እና አፍሪቃ እንደሚኖሩ ያትታል። በውጭ አገራት የሚኖሩ ዜጎች ለወዳጅ ዘመዶቻቸው የሚልኩት ገንዘብ ከኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ምንጮች ዋንኛው ነው። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒሥቴር እንዳስታወቀው በጎርጎሮሳዊው 2015 ዓ.ም. በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ አገር ቤት የላኩት የገንዘብ መጠን ከጎርጎሮሳዊው 2014 ዓ.ም. ጋር ሲነፃጸር በ1.5 ቢሊዮን ዶላር ጭማሪ አሳይቷል። ወደ ኢትዮጵያ የሚላከው ገንዘብ በጎርጎሮሳዊው 2014 ዓ.ም 2 ቢሊዮን የነበረ ሲሆን በጎርጎሮሳዊው 2015 ዓ.ም. ወደ 3.7 ቢሊዮን ዶላር ማደጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒሥቴር አስታውቋል። አቶ አብዱልመናን መሐመድ የኢትዮጵያ መንግስት በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እንደ ባንክ እና የመድን አቅራቢ ኩባንያዎች ውስጥ እንዲሳተፉ ቢፈቅድ ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ማግኛ መንገድ ይሆናል የሚል እምነት አላቸው።

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ