1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቢቢሲ የአፍሪቃ ቀንድ የስርጭት እቅድ

Merga Yonas Bulaሐሙስ፣ መስከረም 27 2008

የብሪታኒያ የዜና አውታር የሆነው(ቢቢሲ) በፈረንጆቹ የመስከረም ወር የመጀመሪያ ሳምንት ማለትም በ2007 ዓም ማብቂያ ላይ ይፋ እንዳደረገዉ የዴሞክራሲ እጥረት አለባቸው ባላቸው ሃገራት አዲስ የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ስርጭቶችን ለመጀመር አቅዷል። ቢቢሲ አዳዲስ ስርጭቶችን ለማስተላለፍ ያቀደው ለሰሜን ኮሪያ፣ ሩሲያ፣ ኢትዮጵያና ኤርትራ ነዉ።

https://p.dw.com/p/1GlBv
Großbritannien BBC-Chef Tony Hall
ቶኒ ሆል፣ የቢቢሲ ዋና ሥራ አስኪያጅምስል Leon Neal/AFP/Getty Images

[No title]

እንዲያም ሆኖ በተለይ ለኢትዮጵያ እና ኤርትራ አሁን ስርጭት የታሰበበት ምክንያትም ሆነ በየትኛዉ ቋንቋ ያሰራጫል የሚለዉ ገና አልታወቀም።

የብሪታኒያ የዜና ማሰራጫ ኮርፖሬሽን የአለም አቀፍ አገልግሎት በመባል የሚታወቀዉ ቢቢሲ ጳጉሜ 2 ቀን2007 ዓ.ም. በኢትዮጵያ እና በኤትርራ አዲስ የራድዮ ስርጭት በመካከለኛና በአጭር ሞገድ ለመጀመር እንዳቀደ ማሳወቁ ይታወሳል። ቶኒ ሆል፣ የቢቢሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ እቅዱን ሲያብራሩ በመጭዎቹ አመታት ለመጀመር የታቀደዉ ይህ ስርጭት እንዲህ ያሉት አገራት ውስጥ በፍትኃዊ የዜና አዘጋገብ የዲሞክራሲ ጉድለት ለማሻሻል መሆኑን አስረድተዋል።

ይህ እቅድ በየ10 አመቱ የሚደረገዉ የቢቢሲ መተዳደሪያ ህግ ለውጥ አካል ሲሆን ስርጭቱ ከመጀመሩ በፊት በሚቀጥለው ዓመት በብሪታኒያ ፓርላማ ቀርቦ መፅደቅ እንዳለበት የድርጅቱ ኮምዩንኬሽን ስራ አስኪያጅ ፖል ራስሙሴን ለዶይቼ ቨሌ በኢ-ሜይል ገልጸዋል። ቢቢሲ ለምን አሁን ይህን ስርጭት ለመጀመር እንዳቀደ፤አስፈላጊነቱ፤እንዲሁም በየትኛው ቋንቋ ሊያሰራጭ እንዳቀደ በጥልቀት ለመናገር ከሚችሉበት ደረጃ ላይ አለመሆናቸውንም ፖል ራስሙሴን ገልጠዋል

ጋዜጠኛ አርጋው አሽኔ ቢቢሲ ወደ ምስራቅ አፍሪቃ ሥርጭት ለመጀመር ያቀደበት ምክንያት ሊሆን ይችላል ካሉት መካከል ዲሞክራሲ በሚታፈንባቸው አገራት የሚታየውን የመረጃ እጥረት መሸፈን አንዱ ነው።ከዚህ በተጨማሪ ባደጉት አገሮች የኢንተርኔት ቴክኖሎጂ መስፋፋቱ የአጭርና መካከለኛ ሞገድ ስርጭት እየተዳከመ በመምጣቱ ለቢቢሲ በኢትዮጵያና ኤርትራ አዲስ አድማጭ ለማፍራት ያቀደበት ፤ሊሆን ይችላል ይላሉ አቶ አርጋው።

ቢቢሲ በሬድዮ ዘርፍ ና መረጃ ሰጭነት ራሱን አዉራ አድርጎ ሥለሚቆጥር ልምዱን የበለጠ ለማስፋፋት ይጠቅመዋል የሚሉት አቶ አርጋዉ የምዕራቡን የፖለቲካ ርዮት አለም ለማስፋፋትና የባህል ተጽዕኖ ለመፍጠር ይጠቀምበታል ሲሉ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል። ኢትዮጵያም ሆነ ኤርትራ የሚድያ አፈና ያለባቸዉ አገር ስለሆኑ፣ ቢቢሲ በዚህ ዉስጥ በመሳተፍ አስተዋጾ ለማድረግ ያሰበ ይመስለኛል ሲሉ ደምድመዋል።

Zentralafrikanische Republik Medien Radio
ምስል SIA KAMBOU/AFP/Getty Images

ቢቢሲ በየትኛው ቋንቋ በኢትዮጵያ ስርጭቱን እንደሚጀምር ግልጽ ባይሆንም የቢቢሲ ዓለም አቀፍ አገልግሎት አንድ ከፍተኛ ኃላፊ ኮርፖሬሽኑ በየትኛው ቋንቋ ስርጭቱን ለመጀመር እንዳቀደ ሲጠየቁ የሰጡትን መልስ አፍሪካን ኮንፍዴንሽያል የተሰኘ መጽሔት «አስገራሚ» ብሎታል። ስማቸው ያልተጠቀሰው እኚሁ ኃላፊ «በአፍሪቃ ቀንድ እንደ አረቢኛ ቋንቋ ተመጣጣኝ የሆነ ሁሉም ሠዉ መረዳት የሚችለው ሌላ ቋንቋ የለም ወይ?» ሲሉ ጥያቄውን በጥያቄ መልሰዋል። ግን መጽሄቱ የለም ባይ ኔዉ። ምክንያቱም፣ በኤርትራ ብቻ 10 ቋንቋዎች ይነገራሉ፣ አልፎም በኢትዮጵያ ከ70 በላይ ቋንቋዎች እንዳሉ መፅሄቱ ገልጿዋል።

ኣንድርዉ ዋዬር፣ የመጽሄቱ አርታዒ የሆኑት እሄን ጉዳይ አስመልክቶ ስናገሩ፣ «የቢቢሲ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አካል ወደ ኢትዮጵያ ስርጭት ለመጀመር አስቧል። ግን ምን ያህል ቋንቋዎች እንዳሉ አላሰቡበትም። ለዚህም ነው እቅዱ ላይ ከውሳኔ ከተደረሰ ራሳቸውን ትልቅ ችግር ውስጥ ነው የሚጥሉት። ለምሳሌ አማርኛ ብሄራዊ የስራ ቋንቋ የሆነው ግን የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ ቀደም ብሎ በአማርኛ ማሰራጨት ጀምሯል። እንደዚያም ሆኖ ብዙሃኑ የሚናገሩት ቋንቋ አይደለም። የገዢው መደብ ቋንቋ የሆነው ትግሪኛ አለ። ኦሮሞኛና ሌላ ብዙ ቋንቋዎች አሉ። ለዛም ነው አንዳንድ ሰዎች የስርጭቱ ቋንቋ እንግሊዝኛ መሆን አለበት ሲሉ አሳባቸውን ያቀረቡት። ለዚህም መከራከሪያ ነጥብ ሊሆን የሚችለው በኢትዮጵያ አብዛኛው ሰው እንግሊዝኛ በትምህርት ቤት ይማራሉ። በዚህም ማሰራጨት አብዛኛውን ሰው ለመድረስ ይቻላል በሚል ነው።»

ቢቢሲ ላቀደው የአፍሪቃ ቀንድ ስርጭት እንግሊዘኛ አማራጭ ሊሆን የሚችለው የአገሪቱን የቋንቋ ብዛትና የፖለቲካ ችግሮች ታሳቢ በማድረግ ሊሆን እንደሚችል አንድሪው ተናግረዋል። በእንግሊዝኛ ማሰራጨት በራሱ ችግሮች ሊኖሩት ይችላሉ፣ ይህም፣ ኮርፖሬሽኑን እንደ አዲስ ቅኝ ገዢ ሊያስቆጥረው ይችላል ሲሉ አንድሪው ዋዬር መላምታቸውን ሰንዝረዋል።ያም ተባለ ይህ ቢቢሲ እስካሁን ወደ አፍሪቃ በተለይም ወደ ኢትዮጵያ ና ኤርትራ የራድዮ ሥርጭት የመጀመር እቅድ እንዳለው ከማሳወቅ ውጭ በየትኛው ቋንቋ እንደሚያሠራጭ እስካሁን ግልፅ አላደረገም።

ቢቢሲ ለጊዜዉ በየትኛዉ ቋንቋ ስርጭቶቹን ሊያስተላልፍ እንዳሰበ ይፋ ባያደርግም ኦሮምኛ ቋንቋም እንዲጨመር የሚጠይቅ ዓለም አቀፍ የፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻም እየተካሄደ ነዉ። በማህበራዊ ድረ-ገጶች አማካኝነት በሚሰበሰበዉ ፊርማላይ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ የኦሮሞ ዲያስፖራ አባላት እየተሳተፉ ነው። እስካሁንም ከ 40ሺ በላይ ፊርማዎችን ማሰባሰብ ተችሎአል።

መርጋ ዮናስ/ናትናኤል ወልዴ

ሒሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ