1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቡሩንዲ ውዝግብ እና የቀጣዩ ድርድር እድል

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 8 2009

ለቡሩንዲ ውዝግብ መፍትሔ የሚያፈላልግ ድርድር በዚህ በተያዘው ሀምሌ ወር መጨረሻ ገደማ ይደረጋል። በቡሩንዲ መንግሥት እና በተቀናቃኞቹ መካከል በተጓደለው መተማመን የተነሳ ድርድሩ አዳጋች እንደሚሆን ተገምቷል።

https://p.dw.com/p/2gaAS
Burundi Proteste
ምስል picture-alliance/AA/R. Ndabashinze

Amh. Fokus Afrika A (15.07.2017) - MP3-Stereo


የቡሩንዲ ፕሬዚደንት ፒየር ንኩሩንዚዛ ሕገ መንግሥቱን በመጣስ እና ከሕዝባቸው የገጠማቸውን ተቃውሞ ችላ በማለት ሶስተኛ የስልጣን ዘመናቸውን ከጀመሩ ሁለት ዓመት ሆኗቸዋል። ከዚያን ጊዜ ወዲህ ፕሬዚደንት ንኩሩንዚዛ የስልጣን ዘመናቸውን በማራዘማቸው ተቃውሞ ከወጡት መካከል 3000 የሚሆኑት የፀጥታ ኃይላት በወሰዱት ርምጃ መገደላቸውን የተቃዋሚ ወገኖች የሚያወጧቸው ዘገቦች ያሳያሉ።  የተመድ የስደተኞች ጉዳይ ተመልካች መስሪያ ቤት፣ በምህጻሩ «ኤንኤችሲአር» እንዳስታወቀውም፣ ከ400,000 የሚበልጡ ደግሞ ተሰደዋል።   
በሰሜን ቡሩንዲ በሚገኘው የካያንዛ ግዛት በሺንያ መንደር ባለፈው እሁድ ከቀትር በኋላ አንድ ማንነቱ ያልታወቀ ግለሰብ በጣለው የእጅ ቦምብ ጥቃት ስምንት ሰዎች ሲገደሉ፣ 50 መቆስለዋል። የፖሊስ ቀል አቀባይ ፒየር ንኩሪኪዬ ጥቃቱን የጣለውው  ማንነት በግልጽ ባይናገሩም፣  የዶይቸ ቬለ ግዌንዶሊን ሂልዘ እንዳለችው፣ ጥቃቱ የአሸባሪዎች ስራ መሆኑን አመልክተዋል። በመገናኛ ብዙኃን ዘገቦች መሰረት፣ ለዚህ ዓይነቱ ጥቃት የቡሩንዲ ፖሊስ ሁሌ የፕሬዚደንት ፒየር ንኩሩንዚዛ ተቃዋሚዎችን ተጠያቂ ያደርጋል።
ዩጋንዳ እና ታንዛንያ በቡሩንዲ መንግሥት እና በተቃዋሚዎቻቸው መካከል ከብዙ ጊዜ ጀምረው የሽምግልና ጥረት ቢጀምሩም፣ ጥረታቸው ፍሬ አልባ እንደሆነ ይገኛል። ሸምጋዮቹ እስከዛሬ ድረስ ሁለቱን ተቀናቃኝ ወገኖች በአንድ ጠረጴዛ ዙርያ አገናኝተው ማወያየት አልተሳካላቸውም። የታንዛንያ የቀድሞ ፕሬዚደንት ቤንጃሚን ምካፓ ሁኔታዎች ይህን በመሰሉበት ባሁኑ ጊዜም፣ ለሀምሌ ወር መጨረሻ በታንዛንያ የአሩሻ ከተማ አዲስ ድርድር ለማካሄድ አቅደዋል።  
የትብብር እና ዴሞክራሲ ንቅናቄ፣ በምህጻሩ «ኤምኤስዲ» የተባለው የተቃዋሚ ፓርቲ ቡሩንዲን እስከ ጎርጎሪዮሳዊው 2020 ዓም ድረስ  ወደ ነፃ እና ግልጽ ምርጫ ያመራል በሚል እቅድ አውጥቷል፣ የ«ኤምኤስዲ» ሊቀ መንበር አሌክስ ሲንዱሂዥየም  እቅዱን ለካባቢው ቡድን፣ ለምሥራቅ አፍሪቃ ማህበረሰብ በመላክ ቡድኑ ፕሬዚደንቱ በእቅዱ የሰፈሩትን ሀሳቦች እንዲደግፉ እንዲያግባቡ ጠይቀዋል። አሌክስ ሲንዱሂዥየ ከዶይቸ ቬለ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በእቅዱ ከተካተቱት ሀሳቦች መካከል አንዳንዶቹን ጠቅሰዋል። 

Der frühere Präsident Tansanias Benjamin Mkapa
ቤንጃሚን ምካፓምስል Abbas Mbazumutima/Iwacu

« ስደተኞች የሚመለሱበት፣ ተቃዋሚዎች የሚመለሱበት እና ለነሱ መደረግ ያለበት ከለላ፣ የፖለቲካ እስረኞች የሚፈቱበት፣ የ«ኢምቦኔራኩሬ» ሚሊሺያዎች ቡድን የሚበተንበት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሙሉ መብታቸው ጋር እንደገና የሚንቀሳቀሱበት  እና የግል መገናኛ ብዙኃን መልሶ ስራ የሚጀምሩበት አሰራርን ይመለከታል። ባጭሩ፣ በሀሳቦቹ ላይ ውይይት የሚደረግበትን መንፈስ መፍጠር አስፈላጊ ነው ብዬ አስባለሁ። »
ይሁንና፣ ፕሬዚደንት ንኩሩንዚዛ የሚመሩት  መንግሥት እንደ ትክክለኛ ተደራዳሪ ከማይመለከተው «ኤምኤስዲ» ጋር፣  መደራደር አይፈልግም። መንግሥት «ኤምሲዲ»ን የትጥቅ ትግል አቅዷል በሚል ምክንያት ከስድስት ወር በፊት ሕጋዊ የፓርቲነት አቋሙን መንጠቁ የሚታወስ ነው። ይሁንና፣ የ«ኤምኤስዲ» ሊቀ መንበር አሌክስ ሲንዱሂዥየ ወቀሳውን ሀሰት ሲሉ አስተባብለዋል።
« በራሴ እተማመናለሁ። በአሁኑ ጊዜ በቡዡምቡራ መንግሥት አንጻር የትጥቅ ትግል የሚያካሂድ የማንም ድርጅት መሪ አይደለሁም። »
የቡሩንዲ መንግሥት የ«ኤምኤስዲ»ን ሕጋዊነት የሻረው የተቃዋሚው ፓርቲ በሀገሪቱ ያሳረፈውን ተፅዕኖ እና የደቀነበትን ፉክክር በመፍራት መሆኑን ሲንዱሂዥየ ገልጸዋል። የተቃዋሚው ፓርቲ ሊቀ መንበር  በጎርጎሪዮሳዊው 2007 ዓም ለፕሬዚደንታዊው ምርጫ በእጩ ተወዳዳሪነት ቀርበው እና ከአንድ ዓመት በኋላ በ 2008 ዓም ፕሬዚደንቱን ሰድበዋል በሚል ክስ ወህኒ ወርደው ነበር።  
ይሁን እንጂ፣ ዶይቸ ቬለ ያነጋገራቸው የቡሩንዲ ምክትል ፕሬዚደንት ጋስቶ ሲንዲምዎ መንግሥታቸው ፖለቲካዊ ፉክክር በትክክለኛ መንገድ የሚካሄድበትን ሁኔታ እንዳመቻቸ ነው የገለጹት። 

Burundi Opppositionspolitiker Alexis Sinduhije
አሌክሲስ ሲንድሂዥየምስል Getty Images/AFP/E. Ndikumana

« የፖለቲካ ተዋናዮቹን በካያንዛ፣ ቡሩንዲ ማሰባሰብ ችለናል። እና ድርድሩን ለምንድን ነው እዚህ የማናደርገው? ለዚህ ግን ትክክለኛ መልስ አናገኝም።  በአሩሻ ድርድር የሚቋቋም የሽግግር መንግሥትን መቀበልም አንችልም፣ ምክንያቱም፣ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ መንግሥት አለን። ይህ መንግሥት እያንዳንዱ የፖለቲካ ተዋናይ በሀገሪቱ ስራውን ካላንዳች ችግር ማከናወን የሚችልበትን ፀጥታ እና ሰላም ማረጋገጥ ይችላል። የፖለቲካ ፉክክሩ ጤናማ የሚሆንበትን ሁኔታ ፈጥረናል። »

ሁሉም የሚቀበሉት ሕገ መንግሥት ማውጣት አዳጋች ነው ያሉት ሲንዲምዎ መንግሥት ቀጣዩን ምርጫ   የተሳካ በማድረጉ ተግባር ላይ ሁሉም ኃላፊነቱን በሚገባ እየተወጣ አይደለም በሚል ባንዳንድ አንደራሴዎች ላይ ወቀሳ ሰንዝረዋል።
«  ወደ 2020 ዓም ምርጫ የሚያመራንን እቅድ ለማውጣት እየሰራን ነው። ከነዚህ ሰዎች መካከል ለምክር ቤት እንደራሴነት የተመረጡ ይገኙባቸዋል። ግን ይህንኑ ስራቸውን ለመጀመር ፈቃደኞች አልሆኑም። ምንድን ነው የሚፈልጉት? »
ሲንዱሂዥየ እንደሚሉት፣  ለተቃዋሚ ቡድኖች የፕሬዚደንቱ በስልጣን የመቆየት ጥያቄ መልስ ማግኘት ያለበት ጉዳይ ነው።
« ይህ በድርድር የሚፈታ ጉዳይ ነው። ነፃ እና ግልጽ ምርጫ የሚካሄድበትን ሁኔታ መፍጠር ከፈለግን  እና ፕሬዚደንት ንኩሩንዚዛም ምርጫውን እንዳያዘጋጁ ከጠየቅን፣ ንኩሩንዚዛ ስልጣናቸውን ይልቀቁ አይልቀቁ በሚለውም ጉዳይ ላይ መደራደር መቻል አለብን። » 
የቡሩንዲ ጊዚያዊ ሁኔታ አሳሳቢ ውጥረት እንደሚታይበት ከአንድ ወር ገደማ በፊት ቡሩንዲን የጎበኙት የአንድ የጀርመናውያን እና የትልቆቹ ሀይቆች አካባቢ ማዕከላይ አፍሪቃ ሀገራት አብያተ ክርስትያን መረብ ባልደረባ ጌዚኔ አሜስ ገልጸዋል።

Gaston Sindimwo, Vizepräsident von Burundi
ጋስቶ ሲንድሚዎምስል DW/A. Niragira
Burundi leere Tankstelle
ነዳጅ የሌለው ማደያምስል DW/A. Niragira

« ሕዝቡ ከሁሉም አቅጣጫ ችግር እየደረሰበት ነው። የምግብ እና የነዳጅ እጥረት ገጥሞታል። አንዳንዴም የመጓጓዣ ዘዴ ስለማይኖር እንቅስቃሴ ሁሉ ይቋረጣል። ከዚህ በተጨማሪ በበሀገሪቱ ፍርሀት የሰፈነበት የተካረረ የፖለቲካ ሁኔታ ተስፋፍቷል። ቡሩንዲ ውስጥ በሕዝቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ ውስጥ የፍርሀት እና የአቅም አልባነት ስሜት ይታያል።  አንዱ ሌላውን አያምንም።  » 
የአውሮጳ ህብረት መንበሩን በፓሪስ፣ ፈረንሳይ ያደረገው በምህጻሩ «ኤፍአይዲኤች» የተባለው የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች  ድርጅቶች ፌዴሬሽን፣ ስለቡሩንዲ ያወጣውን ዘገባ ተከትሎ  በቡሩንዲ ላይ የጣለው የኤኮኖሚ ማዕቀብ ከአንድ ወር በፊት አራዝሟል።  ይህም እንደ ጀርመናዊቷ የማዕከላይ አፍሪቃ ሀገራት አብያተ ክርስትያን መረብ ባልደረባ ጌዚኔ አሜስ አስተያየት፣ የቡሩንዲን ውዝግብ ለማብቃት በአሩሻ የሚደረገው ጥረት ቀላል አይሆንም።
« በአንድ በኩል ከዚህ መንግሥት ጋር ቀጣይ ድርድር ማድረግ አይቻልም። ዓለም አቀፍ ማዕቀብ ተጥሎበታል።  የአውሮጳ ህብረት እና ጀርመን ለቡሩንዲ መንግሥት የሚሰጡትን ገንዘብ አሁንም እንዳቋረጡ ይገኛሉ። በሌላ በኩል፣ የቡሩንዲ መንግሥት የፖለቲካ ዘርፉን ክፍት ማድረግ ስለሚቻልበትም ሆነ  ሕገ መንግሥቱን ስለማክበሩ ጉዳይም ለመነጋገር አንዳችም ጥረት ለማድረግም ሆነ የፖለቲካ ፈቃደኝነትን ለማሳየት ዝግጁ አልሆነም።  በአንጻሩ፣ መንግሥት፣ በሕገ መንግሥቱ ላይ አንዳንድ ለውጦችን  በማድረግ፣ የ2020 ዓም ምርጫን የማዘጋጀት እቅዱን በመገናኛ ብዙኃን በይፋ አሳውቋል፣ በዚሁ እቅዱ መሰረት፣ ንኩሩንዚዛ  ሕገ መንግሥቱን ምን ያህል መቀየር ይቻላል የሚለውን ጉዳይ በስድስት ወራት የሚያጣራ አንድ የግል ኮሚሽን ያቋቁማሉ። ይህ ይደረግ የሚባለው ለውጥ አደገኛነቱ፣    በፕሬዚደንቱ የስልጣን ዘመን ላይ ያረፈውን ገደብ ማንሳት ብቻ ሳይሆን፣ ጎሳን የተመለከቱ አንዳንድ የኮታ ደንቦችንም  ሊሽር የሚችልበትን  ስጋት መደቀኑ ላይ ነው። ይህ ከብዙ ዓመታት የርስበርስ ጦርነት በኋላ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት በጠቅላላ ትርጉም አልባ እንዳያደርገው ያሰጋል። » 
የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች  ድርጅቶች ፌዴሬሽን  የቡሩንዲ ፕሬዚደንት ንኩሩንዚዛ  እና መንግሥታቸው የሚከተሉት አምባገነናዊ ስርዓት ሀገሪቱን ወደ እርስበርሱ ጦርነት እንዳያስገባ አስግቷል ሲል አስጠንቅቋል። ከሁቱ ጎሳ የሚወለዱት ፕሬዚደንት ንኩሩንዚዛ የሀገሪቱን ጦር ከቱትስሲ ጎሳ አባላት ነፃ ለማድረግ በሚል በጦሩ የተሰለፉትን የቱትሲ ጎሳ ተወላጆች ሆን ብለው በማጥፋት ላይ መሆናቸውን የፌዱሬሽኑ ዘገባ አመልክቷል።  በመቶዎች የሚቆጠሩ የቱትሲ ወታደሮች ተገድለዋል፣ የት እንደደረሱ ሳይታወቅ ጠፍተዋል ወይም ታስረዋል። ይህ ሁኔታም ፣ በብዙ የፖለቲካ ታዛቢዎች ዘንድ፣ በቡሩንዲ የተካሄደውን እና በጎርጎሪዮሳዊው 2005 ዓም ያበቃውን ደም አፋሳሹን የርስበርስ ጦርነት እንደሚያስታውስ ዘገባው ገልጿል።  በዚያን ጊዜ በብዙኃኑ ሁቱዎች  እና በውሁዳኑ ቱትሲዎች መካከል በተካሄደውው ጦርነት ከ400,000 የሚበልጥ ሰው ተገድሏል።

Burundi Proteste
ምስል picture-alliance/AA/R. Ndabashinze

አርያም ተክሌ

ልደት አበበ