1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አቶ ደሳለኝ ከበደ

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 2 2011

ከኢትዮጵያ እና ከኤርትራ በባህር ወደ አውሮጳ ተሰደው ጀርመን ከገቡት መካከል ከተወሰኑት ጋር ያደረጉትን ቃለ መጠይቅ በመጸሐፍ አሳትመዋል።«የስደት ማስታወሻ»በተሰኘው በዚህ መጸሐፍ ስደተኞችን በስም ሳይጠቅሱ ቁጥር ሰጥተው የአደገኛውን የባህር እና የበረሀ ጉዞአቸውን አሳዛኝ እና አስገራሚ ታሪኮች አስነብበዋል።የጻፉትም ሌሎች እንዲማሩበት ነው።

https://p.dw.com/p/3Lol7
Desalegn Kebede
ምስል Privat

በጎ አድራጊው አቶ ደሳለኝ ከበደ በጀርመን


እዚህ ጀርመን በሚኖሩበት ከተማ ኢትዮጵያውን በተሰባሰቡበት ማህበር ውስጥ በተለያዩ የበጎ ፈቃድ ሥራዎች ውስጥ ይሳተፋሉ። በአካባቢያቸው የሚገኙ እዚህ የተወለዱ ኢትዮጵያውያን ልጆች ፣ቋንቋቸውን እና ባህላቸውን እንዲያውቁ ማስተማር እና ስደተኞችን መርዳት ከበጎ ፈቃድ ሥራዎቻቸው መካከል ተጠቃሽ ናቸው።የአማርኛ ቋንቋ መማሪያ ኣና ሌሎች መጸሀፎችንም አሳትመዋል፤አቶ ደሳለኝ ከበደ ይባላሉ ጀርመን ሲኖሩ 24 ዓመት አስቆጥረዋል። ከዚያ በፊት ኢትዮጵያ እያሉ በተሰማሩበት የውትድርና ሙያ እስከ ሻለቃ ማዕረግ ደርሰዋል።እርሳቸው እንደሚሉት በወቅቱ ወታደር የሆኑት በነበረው የፖለቲካ ችግር ምክንያት እንጂ ፍላጎታቸው በቀለሙ ትምሕርት መግፋት በተለይም ስነ ጽሁፍ ማጥናት ነበር።በውትድርናው ዓለም በአብዛኛው በመመህርነት ያገለገሉት አቶ ደሳለኝ በቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት ለ4 ዓመት ወታደራዊ ሳይንስም አጥንተዋል።ኢህአዴግ ኢትዮጵያን ተቆጣጥሮ ወታደሩን ሲበተን በግል መሥራት ጀመሩ። ከሁለት ዓመት በኋላ ወደ ሠራዊቱ እንዲመለሱ ጥሪ ሲደርግላቸው ለጊዜው እሺ ብለው ነበር።ሆኖም ብዙም ሳይቆዩ ወደ ጀርመን መጡ። አሁንም የሚኖሩት የዛሬ 24 ዓመት በመጡባት በፍራንክፈርት ከተማ ነው።
ከኢትዮጵያውያን የመረዳጃ ማህበር  መሥራቾች አንዱ የሆኑት አቶ ደሳለኝ ማህበሩን ለብዙ ዓመታት በፀሀፊነት በሰብሳቢነት አገልግለዋል።አሁን ግን በማስተባበሩ ሥራ ላይ አትኩረዋል።
አቶ ደሳለኝ ከዚህ ሌላ በአካባቢያቸው የሚገኙ ስደተኞችንም ይረዳሉ።ለስደተኞች በማስተርጎም እና  ልዩ ልዩ ድጋፎችን በመስጠትም ይተባበራሉ። 
በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከኢትዮጵያ እና ከኤርትራ በባህር ወደ አውሮጳ ተሰደው ጀርመን ከገቡት መካከል ከተወሰኑት ጋር ያደረጉትን ቃለ መጠይቅ በመጸሐፍ አሳትመዋል።«የስደት ማስታወሻ»በተሰኘው በዚህ መጸሐፍ ስደተኞችን በስም ሳይጠቅሱ ቁጥር ሰጥተው የአደገኛውን የባህር እና የበረሀ ጉዞአቸውን አሳዛኝ እና አስገራሚ ታሪኮች አስነብበዋል። መጸሐፉን  በተመሳሳይ መንገድ ከኢትዮጵያ ለመሰደድ ለሚያስቡ ወጣቶች ትምሕርት እንዲሆን አስበው እንደጻፉት ይናገራሉ።በዚህ መጸሐፍ ከተካተቱት ታሪኮች መካከል በተለይ የአንዱ የስደት ገጠመኝ በጣም ያዘኑበት ነበር።አቶ ደሳለኝ የታተሙ እና ያልታተሙ ሌሎች የስነ ጽሁፍ ሥራዎችም አሏቸው።በተሰደዱ በ23 ዓመታቸው ባለፈው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የሄዱት አቶ ደሳለኝ አሁን ጠቅለው ወደ ሀገራቸው ለመግባት በዝግጅት ላይ ናቸው።
ኂሩት መለሰ

Desalegn Kebede
ምስል Privat

ሸዋዬ ለገሠ