1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የበርሊን ግንብ መናድና የዓለም ፖለቲካ

ሰኞ፣ ኅዳር 1 2007

ጎርቫቾቭን ታቸር ከለንደን ሬገን ከዋሽግተን እየተቀባበሉ ሲያንቆለጳጵሷቸዉ፤ መራሔ መንግሥት ሔልሙት ኮል የቀዳሚዎቻቸዉንም፤ የራሳቸዉንም የሕዝባቸዉንም ሕልም ምኞት እዉን ለማድረግ ሞስኮዎችን እንደ ጥሩ ወዳጅ ቀረቧቸዉ።አግባባቡ አባበሉ።

https://p.dw.com/p/1DkwY
ምስል Sean Gallup/Getty Images

መሽቷል።በርሊኖች ግን የነጋ ያክል ከምሥራቅም-ከምዕራብም ወደዚያ ግዙፍ ግንብ ይተማሉ።ካጠገቡ ሲደርሱግንቡን ከምሥራቅም፤ ከምዕራብም፤ ካናቱም ይወቅሩ-ይቀጠቅጡ፤ይሸራርፉ-ይቦዳድሱት ያዙ።ግንቡ ይጥፋ እያሉ፤-

በርግጥም ለበርሊኖች ሊነጋ ነዉ።ዙድዶቸ ሳይቱንግ የተሰኘዉ ጋዜጣ እንደዘገበዉ ግን የሚነጋዉ ለበርሊኖች ብቻ አይደለም ለመላዉ ጀርምን እንጂ።«በዚሕ ምሽት፤ የጀርመን ሕዝብ ከመላዉ ዓለም ሕዝብ ሁሉ እጅግ ደስተኛ ነዉ።»የምዕራብ በርሊን ከንቲባ ቫልተር ሞምፐር የጋዜጣዉን አባባል ደገሙት

«የጀርመን ሕዝብ ከዓለም እጅግ ደስተኛዉ ሕዝብ ነዉ።» ሕዳር 9 1989።ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ።የተቀረዉ ዓለም እንደ ጀርመኖች ይደሰት፤ ወይም በተቃራኒዉ ያዝን ይሆናል።ጀርመንን ለዘመናትለሁለት የገመሰዉ ግንብ- መደርመስ ግን ግንቡን ያሳጠረዉ ኮሚንስታዊ ሥርዓት መገርሰስም መሆኑ እዉነት ነዉ።የዓለም የአርባ-አምስት ዘመን ፍጥጫፍፃሜነቱም ሐቅ።ዘንድሮ ትናንት ሃያ-አምስት ዓመቱ።ላፍታ እንዘክረዉ አብራችሁኝ ቆዩ።

ሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ጀምሮ ሶቬት ሕብረት ከምትቆጣጠረዉ ወይም ከጦርነቱ ፍፃሜ በሕዋላ «የሶቬት ዞን» ተብሎ ከሚጠራዉ ምሥራቃዊ ጀርመን፤ ምዕራባዉያኑ መንግሥታት ወደ ሚቆጣጠሩት ምዕራብ ጀርመን የሚፈልሰዉ ሕዝብ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መምጣቱ ለሞስኮ ኮሚኒስቶች አሳሳቢ፤ ለምሥራቅ በርሊን ተከታዮቻቸዉ ደግሞ አስጊ ነበር።

Bildergalerie Gorbatschow
ምስል picture-alliance/dpa/F. Kleefeldt

ጀርመን በይፋ ለሁለት ተገምሳ-ቦን እና ገሚስ በርሊን ላይ-ካፒታሊስታዊ እና ኮሚኒስታዊ መንግሥታት ከቆመላት ከ1949 እስከ 1952 በተቆጠሩት ሰወስት ዓመታት ብቻ 2 ሚሊዮን ያሕል ሕዝብ ከምሥራቅ ጀርመን ወደ ምዕራብ ፈልሷል።

Frankfurter Buchmesse 2014 Helmut Kohl 8. Oktober
ምስል Reuters/R. Orlowski

ከምስራቅ ወደ ምዕራብ የሚየፈልሰዉ ጀርመናዊ ቁጥር መጨመር፤ ሶቭየት ሕብረት በምትቆጣጠራቸዉ በሌሎች የምሥራቅ አዉሮጳ ሐገራት ብልጭ-ድርግም የሚለዉ ፀረ-ኮሚኒስታዊ እንቅስቃሴ መደጋጋም ያሳሰባቸዉ የሶቭየት ሕብረቱ መሪ ጆሴፍ ስታሊን «የስታሊን ማስታወሻ» የተባለዉን «የእርቅ» ሐሳብ ፃፉ።መጋቢት 1952።

«በዚሕ ሐሳብ መሠረት የሶሻሊስት ሶቪየት ሕብረት ሪፐብሊክ መንግሥት የሠላም ሥምምነት ለመፈራረምና የጀርመንን አንድነት ዳግም ለመመሥረት በፅናት መቆሙን ያረጋግጣል።የሶቪየት መንግሥት በመጋቢት 10ሩ ማስታወሻዉ፤ምዕራባዉያኑ ሐያላንም ሆኑ ቦን ተቃራኒ መልስ ለመስጠት በማያሻማ ሁኔታ አቋሙን ግልፅ አድርጓል።»

የያኔዉ የምሥራቅ ጀርመን ሶሻሊስት አንድነት ፓርቲ ዋና ፀሐፊ ኦቶ ግሮተቮል።በግልፅ ከቀረበዉ ጥያቄ ይልቅ ከጥያቄዉ ጀርባ ያለዉን አላማ መስተንተኑን የመረጡት የዋሽግተን፤ ለንደን-ፓሪስ ተሻራኪዎች ጥያቄዉን ዉድቅ አደረጉት።

ሰዉዬዉ ተናደዱ።እድሜም፤ የጤና እጦትም ተጫችኗቸዋል። ምዕራባዉያኑን ለመበቀል ግን አልሰነፉም።የምዕራባዉያኑን ስስ ብልት እንዲጠቁሟቸዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ቫየስላቭ ሚኻኢሎቪች ሞሎቶቭን አዘዙ።ሞሎቶቭ ጊዜ አላጠፉም የምሥራቅ ጀርመን መሪዎች ወደ ምዕራብ ለመጓዝ በሚፈልገዉ ሕዝብ ላይ ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል ያድርጉ የሚል ሐሳብ ጠቆሙ።

ስታሊን ተቀበሉት።የምሥራቅ ጀርመን መሪዎችን ወደ ሞስኮ አስጠሩ።«ሁኔታዉ ሊታገሱት የማይገባ ነዉ» አሉ ጠንካራዉ ሰዉዬ።ምሥራቅና ምዕራብን የሚለያየዉ መስመር-እንደ ድንበር መቆጠር አለበት።እንደ ማንኛዉም ድንበር አይደለም-እንደ አደገኛ ድንበር እንጂ።ጀርመኖች ድንበሩን በሕይወታቸዉ ጭምር ማስከበር አለባቸዉ።»

ትዕዛዙ አይጣስም።የምሥራቅ ጀርመን መሪዎች መስመሩን በሽቦ አሳጠሩት።ሚያዚያ 1952።የሞስኮ-ምሥራቅ ን እርምጃ ምዕራቦች አወገዙት።ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ የሚደረገዉ ጉዞ ግን በእጅጉ ቀነሰ።እየተሽሎከለከ-ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ የሚሰርገዉን ሕዝብ ሙሉ በሙሉ ማስቆም ግን አልተቻለም።

ስታሊንን የተኩት ግዮርጊ ማሌንኮቭ-ብዙም ሳይሉ፤ ምንም ሳያደርጉ በኒኪታ ኽሩስቾቭ ተፈነገሉ።ክሩስቾቭ ስታሊን በሽቦ-ያሳጠሩትን ወሰን በግምብ በማስለሰን የስታሊን ተገቢና ጠንካራ ወራሽነታቸዉን አረጋገጡ።ነሐሴ 1961።እንደተለመደዉ ምዕራቦች ተቃወሙት።በ1963 በርሊንን የጎበኙት የዩናይትድ ስቴትስ ፓሬዝዳንት ጆን አፍ ኬኔዲ ዝነኛ ንግግር የዉግዘቱ ንረት መገለጫ ነበር።«በርሊናዊ ነኝ።»«ነፃ ሰዎች በሙሉ የትም ቢኖሩ የበርሊን ዜጎች ናቸዉ።ሥለዚሕ እንደነፃ ሰዉ እኔ በርሊናዊ ነኝ የሚሉትን ቃላት እስጠቀም ኩራት ይሰማኛል።»

Bildergalerie Gorbatschow
ምስል picture-alliance/dpa

የኬኔዲ ንግግር የምዕብ በርሊንን ሕዝብ ስሜት መነቅነቅ ብቻ ሳይሆን ምዕራባዉያን መንግሥታት ግንቡን ለማፈረስ መቁረጣቸዉንም ጠቋሚ ነበር።በዲፕሎማሲዉም፤ በስለላ፤ በገንዘብ-ማስፈራራቱም ያን ግዙፍ ግንብ ከነ-ኮሚንስታዊዉ ሥርዓት ለመናድ ይወዘዉዙት ገቡ።የሞስኮዎች አፀፋም ቀላል የሚባል አይደለም።

ምሥራቅ ጀርመኖች «የፀረ-ፋሽት ትግል መከላከያግንብ« Anti-Faschistischer Schutzwall»የሚሉትን ግንብ የሚዳፈርን እንደሚያጠፉት ዛቱ።«ድንበራችንን የማያከብር ዋጋዉ-ጥይት ነዉ።»አሉ አንዱ ጄኔራል።ዛቻዉ በዛቻ አልቀረም።ከወላጅ-ወዳጅ ዘመዱ ለመቀየጥ፤ ከጎመራዉ ምጣኔ ሐብት ለመቋደስ፤ አለያም ከኮሚስታዊ ሥርዓት ለማምለጥ እስከዚያች ቀን ድረስ ከሞከሩ ቢያንስ አንድ መቶ ያሕል ሰዎች ተገድለዋል።ቁጥሩ አወዛጋቢ ነዉ።ሰዉ ግን ተገድሏል።

የምሥራቅ-ምዕራቦች ጉልበት መፈታተሻ የሆነዉን ያን ግንብ ለማስፈረስ ምዕራባዉያን መንግሥታት ያላወገዙ፤ ያልዛቱ፤ያላስጠነቀቁበት ዘመን የለም።የግንቡ መናድ በዉጤም የኮሚኒዝም ሥርዓት ፍፃሜ ብቅ ያለዉ ግን ከራሷ ከኮሚንስታዊ ሥርዓት መስራችና አራማጅ ከሶቭየት ሕብረት እንጂ ከሌላ አልነበረም።ሚኻኤል ሰርግየቪች ጎርባቾቭ።

ጎርቫቾቭ በ1985 በዉርስ ያገኙትን ሥልጣን በተደላደሉ ማግሥት ያን ከ1917 ጀምሮ ሞስኮ ላይ የፀናዉን ኮሚንስታዊ ሥርዓት ቀስበቀስ ይመነጋግሉት ገቡ።የዋሽግተን-ለንድን፤ የፓሪስ-ቦን ፖለቲከኞችን የጎርቫቾቭ እርምጃን እርምጃ ለማፋጣን፤ ጎሮቫቾቭን ለማጃገን-እንዳዴም ለመጫን ይረባረቡ ያዙ የብሪታንያዋ ጠቅላይ ሚንስትር ማርጋሬት ታዘር ከዚሕ ሰዉዬ ጋር ተግባብቶ መሥራት አይከብድም እያሉ ሲያሞጋግሷቸዉ፤ የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ሮናልድ ሬገን ደግሞ እባክዎ ይሕን ግንብ ይናዱ እያሉ ይጎተጉቷቸዉ ነበር።

Bildergalerie amerikanische Präsidenten
ምስል picture-alliance/dpa/Cecil Stoughton

«ሶቭየት ሳትሳሳት ልትወስደዉ የምትችለዉ አንድ እርምጃ አለ።ይሕ እርምጃ የሰላምና የነፃነትን መሠረት ያጠናክረዋል።ዋና ፀሐፊ ጎርቫቾቭ ሠላም ከፈለጉ፤ ለሶቭየትና ለምሥራቅ አዉሮጳ ብልፅግናን ከተመኙ፤ ነፃነትን ከፈለጉ ወደዚሕ በር ይምጡ።ሚስተር ጎርቫቾቭ ይሕን በር ይክፈቱ።ሚስተር ጎርቫቾቭ ይሕን ግንብ ያፍርሱ።»

ጎርቫቾቭን ታቸር ከለንደን ሬገን ከዋሽግተን እየተቀባበሉ ሲያንቆለጳጵሷቸዉ፤ መራሔ መንግሥት ሔልሙት ኮል የቀዳሚዎቻቸዉንም፤ የራሳቸዉንም የሕዝባቸዉንም ሕልም ምኞት እዉን ለማድረግ ሞስኮዎችን እንደ ጥሩ ወዳጅ ቀረቧቸዉ።አግባባቡ አባበሉ።እና ጎርቫቾቭ «አንድ ሕዝብ በግንብ ለሁለት ተገምሶ መኖር የለበትም አሉ።»ትክክለኛዉ ትዕዛዝ ከሞስኮ ምሥራቅ በርሊን ደረሰ።

ሕዳር 9 1989።ከምሽቱ አንድ ሰዓት።ዜና።«ከዚሕ ጊዜ ጀምሮ የጀርምን ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ዜጎች በሁሉም አቅጣጫ ወደ ፌደራል ጀርመን መጓዝ ይችላሉ።»

ሕዝበ-በርሊን ከምሥራቅም ወደ ምዕራብ፤ ከምዕራብም ወደ ምሥራቅ ይግተለተል ያዘ።መሐል ተገናኙ።ግንቡ ጋ።ግንቡን ይቀጠቅጡት ያዙ።ግንቡም፤ኮሚንስታዊዉ ሥርዓትም ይቀረደድ ያዘ።ትናትን ሐያ አምስት ዓመቱ።

ግንቡ የተናደበት፤ እንደ ግንቡ ሁሉ የዓለም ልዕለ ሐያል የነበረችዉ ሶቮየት ሕብረት ምሥራቅ አዉሮጳን ጨምድዳ የያዘችበት ጥርስ-ጥፍሯ መርገፍ የጀመረበት፤ ሪፐብሊኮችዋ እያፈተለኩ ታላቅ ግዛትዋ መሸራረፍ የጀመረበት ሃያ አምስተኛ ዓመት ትንት በርሊን ላይ ተከበረ።

በዓሉ «ቀዝቃዛ ጦርነት» ይባል የነበረዉ የኮሚንስት ካፒታሊስቶች የጦር ፍጥጫ ያበቃበት፤ ከኢትዮጵያ እስከ አንጎላ፤ ከአልባኒያ እስከ ካምቦዲያ፤ ከደቡብ የመን እስከ ደቡብ አሜሪካ ተዘርግቶ የነበረዉ ኮሚንስታዊ ሥርዓት መንኮታኮት የጀመረበት ዝክርም ነበር።ለጀርመኖች በያኔዉ የበርሊን ከንቲባ ቋንቋ ከዓለም ሕዝብ ሁሉ እጅግ የተደሰቱበት ዕለት መታሰቢያ።

ከሚኒዝም ከተገረሰ ወይም መገርሰስ ከጀመረ እነሆ-ሃያ አምስተኛ ዐመቱ።ከአይዘናወር እስከ ከኬኔዲ፤ ከችርችል እስከ ታቸር የተፈራረቁት የምዕራብ ሐያላን መሪዎች አሸናፊነታቸዉ በርግጥ ተመስክሯል።በኮሚስቱ ጨቋኝ ሥርዓት መወገድ ያኔ-የቦረቀ፤የፈነደቀ፤ የነ ማርክስ-ኤንግሊስ፤ ሌኒን ሐዉልት ለመገርሰስ የተጣደፈዉ ሕዝብ ዛሬ ከጭቆና ግፍ መላቀቁ ግን ዛሬም በየሐገሩ እንዳጠያየቀ ነዉ።ዓለምስ ሰላም ነች።አይደለችም ይላሉ---ጎርቫቾቭ።

«የአዉሮጳ እና የአለም አቀፍ ፖለቲካ ከቀዝቃዛዉ ጦርነት ፍፃሜ በሕዋላ የገጠመዉን ፈተና መቋቋም አልቻለም።ምዕተ-ዓመቱ መባቻ ላይ አዲሱ (የዓለም) ስራዓት ከተቀረፀ ወዲሕ አሁን ያለንበትን ዓይነት ዉጥረትና አደገኛ አጋጥሞን እንደማያዉቅ መቀበል አለብን።ሐያላኑ መነጋገር ባለመቻላቸዉ አዉሮጳና መካከለኛዉ ምሥራቅ የሚፈሰዉ ደም በጣም አሳሳቢ ነዉ።ዓለም ከአዲስ «ቀዝቃዛ ጦርነት አፋፍ ላይ ናት።አንዳዶች እንዲያዉም ቀዝቃዛዉ ጦርነት ተጀምሯል እያሉ ነዉ።»

ሚኻኤል ጎርቫቾቭ።በትናንቱ የበርሊን በዓል የክብር እንግዳ ነበሩ።ለጉድ ያስቀመጣቸዉ።ነጋሽ መሐነድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ