1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጥቃት በበርሊን

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 11 2009

ትናንት ምሽት ጀርመን ርዕሰ ከተማ በርሊን የሚገኝ አንድ የገና ገበያን ጥሶ በገባ ከባድ የጭነት መኪና የደረሰው ጥቃት ጀርመናውያን በእጅጉ አስደንግጧል ። የጀርመን መሪዎች እና ፖለቲከኞች በስፍራው የደረሰው የሽብር ጥቃት ሳይሆን አይቀርም እያሉ ነው ።

https://p.dw.com/p/2UcCJ
Deutschland Breitscheidplatz nach dem Anschlag in Berlin
ምስል DW/M. Stefanek

Aleppo- Resolution - MP3-Stereo

ጀርመን ውስጥ በከባድ መኪና የተፈፀመ እንዲህ ዓይነት ዘግናኝ ጥቃት ሲደርስ የትናንት ምሽቱ የመጀመሪያው ነው ።ከባድ መኪናው በርካታ ሰዎች ለገበያ ፣ ለመዝናናት አለያም ለጉብኝት በዚህ ወቅት ላይ በሚያዘወትሩት በበርሊን ምዕራባዊ ክፍል በሚገኘው የገና ገበያ ላይ ጥቃት ያደረሰው ከምሽቱ ሁለት ሰዓት አካባቢ ነበር ። ጥቃት አድራሹ ሰዎችን በከባድ መኪና እየደፈለቀ የገደለው እና ያቆሰለው የቀድሞ የጀርመን ንጉስ ቪልሄልም መታሰቢያ ቤተክርስቲያን ስር ነው ። የቤተክርስቲያኗ ሰበካ ጉባኤ ሊቀመንበር አንስለም ላንገ አደጋው ታስቦበት የተፈፀመ ነው የሚመስለው  ።
« ምናልባት ስፍራው ሆነ ተብሎ ተመርጦ ይሆናል ። ምክንያቱም ቦታው ለሰላም እና ለእርቅ የቆመ ነው ። ይህን መሰሉ የገና ገበያ፤ ሰዎች ርስ በርስ ለመገናኘት የሚመጡበት ቦታ ነው ። በርካታ ሰዎች ከጀርመን ከአውሮጳ እንዲሁም ከተለያየ የዓለም ክፍል እዚህ ይመጣሉ ። ከገና በፊት ያለው ጊዜ የወዳጅነት እና የሰላም ጊዜ ተደርጎ ነው የሚወሰደው ። ሰዉ ይህን ነው የተነጠቀው ።»
ከባዱ የጭነት መኪና በሰዎች በተጨናነቀው የመሀል በርሊኑ የገና ገበያ ውስጥ ሰተት ብሎ ገብቶ ወደ 80 ሜትር ያህል መጓዙ ተነግሯል ። እስካሁን በገና ገበያው የተፈፀመው የሽብር ጥቃት ነው አልተባለም ። ሆኖም 12 ሰዎች የተገደሉበት እና 48 ሰዎች የቆሰሉበት ይህ ጥቃት የተፈፀመበት መንገድ፣ ወቅት እና ቦታ የሽብር ጥቃት ሳይሆን አይቀርም እያስባለ ነው ።የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክልን  ጨምሮ በርካታ የጀርመን ፖለቲከኞች ጥቃቱ የሽብር ጥቃት ሳይሆን እንዳልቀረ ግምታቸውን ሰንዝረዋል ። ጥቃቱን በመፈፀም የተጠረጠረው የ23 ዓመት ወጣት ባለፈው ዓመት ጀርመን የገባ የፓኪስታን ስደተኛ ነው መባሉ ደግሞ ነገሩን ግራ አጋቢ አድርጎት ነበር ። በደረሰው ጥቃት በእጅጉ መደንገጣቸውን እና ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማቸው የተናገሩት የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ይህን አሰቃቂ አደጋ ያደረሰው ጀርመን በሰብዓዊነት ያስጠጋችው ስደተኛ መሆኑ ከተረጋገጠ የሁላችንንም ልብ የሚሰብር  ነው ብለዋል ። 
«እስካሁን ስለጥቃቱ በእርግጠኝነት የማናውቃቸው ብዙ ነገሮች አሉ ። ሆኖም በአሁን ደረጃ የተፈፀመው የሽብር ጥቃት ሳይሆን አይቀርም ብለን መገመት አለብን ። ጥቃቱን የተፈፀመውም ጀርመን ከለላ እና ተገን እንዲሰጠው በጠየቀ ሰው መሆኑ የሚረጋገጥ ከሆነ ለሁላችንም እጅግ ከባድ እንደሚሆን አውቃለሁ ።በተለይ ጥገንኘት የጠየቁ  እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ስደተኞች ከህብረተሰቡ ጋር ተዋህደው እንዲኖሩ በመርዳት ላይ ላሉ በርካታ ጀርመናውያን እጅግ አስከፊ ይሆናል ።»
 ምርመራ ቀጥሏል ። ጥቃቱን በመፈፀም የተጠረጠረው ፓኪስታናዊ ትናንትናውኑ አደጋው ከደረሰበት ስፍራ ሁለት ኪሎሜትር ርቀት ላይ በፖሊስ መያዙ ተነግሯል ። በርሊን የስደተኞች መጠለያ ውስጥ ይኖር የነበረው ይኽው ተጠርጣሪ ከዚህ ቀደም ቀላል የሚባሉ ጥፋቶችን በማድረስ ፖሊስ ያውቀዋል ። ሆኖም እስካሁን ታስሮ አያውቅም ነበር።ዛሬ ከቀትር በኋላ ፖሊስ በሰጠው መግለጫ ደግሞ የታየዘው ወጣት ስደተኛ የመኪናው ሾፌር መሆን አለመሆኑ ገና ግልጽ አልሆነም ። ፖሊስ እንዳለው ወጣቱ ጥቃቱን አላደረስኩም ሲል ቃሉን ሰጥቷል ።ዲ ቬልት የተባለው ጋዜጣ አንድ የፖሊስ ባለሥልጣንን ጠቅሶ እንደዘገበው የተያዘው ጥፋተኛ ያልሆነ ሰው ሳይሆን አይቀርም ። ትክክለኛው ጥቃት አድራሽ  የታጠቀ አና የት እንዳለም የማይታወቅ በመሆኑ ተጨማሪ አደጋ ሊያደርስ ይችላል የሚል ስጋት አለ ። ጥቃት ባደረሰው የፖላንድ ታርጋ በነበረው ከባድ መኪና ውስጥ አንድ ፖላንዳዊ ተጠርጣሪ ተገድሎ ተገኝቷል ።  የጀርመን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ቶማስ ደሚዜር ሰውየው የተገደለበት መሣሪያ አለመገኘቱን ተናግረው ነበር ። 

Deutschland Weihnachtsmarkt Tradition
ምስል Reuters/C. Mang
Deutschland Merkel Statement zum Anschlag in Berlin
ምስል Reuters/H. Hanschke
Deutschland Berlin nach Anschlag auf Breitscheidplatz
ምስል DW/M. Heuer

ኂሩት መለሰ 

ነጋሽ መሀመድ