1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የናይል ተፋሰስ ሀገራት ትብብር

ሐሙስ፣ ጥር 24 2010

ሰሞኑን አዲስ አበባ ውስጥ በተካሄደው 30 ኛው የአፍሪቃ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ የተካፈሉት የሦስቱ ሃገራት መሪዎች ባለፈው ሰኞ በግድቡ ዙሪያ የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት ጥናት እና ክትትል የሚያደርግ ከሶስቱም ሃገራት የተውጣጣ ጊዜያዊ ኮሚቴ እንዲዋቀር ከስምምነት ላይ ደርሰዋል ::

https://p.dw.com/p/2rxoz
Äthiopien Grand Renaissance Staudamm al-Sisi al-Bashir Desalegn
ምስል Ashraf Shazly/AFP/Getty Images

የሶስትዮሹ ውይይትእና የናይል ተፋሰስ ሀገራት ትብብር

ኢትዮጵያ በምትገነባው ታላቁ የህዳሴ ግድብ የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት ሶስቱ ሃገራት የጀመሩትን የሰላም ውይይት እንደሚደግፈው የናይል ተፋሰስ ሃገራት ትብብር አስታወቀ። የቡድኑ ዋና ዳይሬክተር ኢኖሰንት ናትባና በተለይ ለዶቸቨለ እንደገለጹት ብዙ ሃገራት በሚጋሩት የናይል ወንዝ ላይ መግባባት እንጂ ግጭት ጠቃሚ ባለመሆኑ ኢትዮጵያ ግብጽ እና ሱዳን ተቋርጦ የቆየውን ውይይት ዳግም መጀመረቸው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።በሶስቱ ሃገራት የሶስትዮሽ ውይይት እና ድርድር ትብብሩ እስካሁን ምንም ቀጥተኛ ተሳትፎ እንደሌለው የሚናገሩት ሃላፊው ሆኖም በማንኛውም ጊዜ በውሃ ሀብት ልማት አስተዳደር እና ፍትሃዊ አጠቃቀም ዙሪያ የቴክኒክ ድጋፍ ከተጠየቀ ለድርድሩ ስኬት አስፈላጊውን ትብብር ሁሉ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

ሦስቱ የተፋሰሱ ምሥራቃዊ ክፍለ ተቋርጦ የነበረውን ድርድር ዳግም ጀምረዋል።በዚህ የሶስትዮሽ የውይይት እና ድርድር ሂደትም ሃገራቱ ቀደምት ታሪካዊ ግንኙነታቸውን ተጠቅመው በአባይ ወንዝ የጋራ ጥቅማቸውን ለማስከበር እና ለመተባበርየሚያስችላቸውን የጋራ ስልት ለመንደፍ በርዕሰ ብሄራት እና በሚኒስትሮች ደረጃ ጭምር ጥምር ውይይቶችን በማካሄድ ላይ ይገኛሉ። ሰሞኑን አዲስ አበባ ውስጥ በተካሄደው 30 ኛው የአፍሪቃ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ የተካፈሉት የሦስቱ ሃገራት መሪዎች ባለፈው ሰኞ በግድቡ ዙሪያ የተፈጠረውን አለምግባባት በድርድር ለመፍታት ጥናት እና ክትትል የሚያደርግ ከሶስቱም ሃገራት የተውጣጣ ጊዜያዊ ኮሚቴ እንዲዋቀር ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።

Äthiopien Grand Renaissance Staudamm
ምስል Reuters/T. Negeri

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በመግለጫው እንዳስታወቀው ቀሪ ልዩነቶቻቸውን ለማጥበብ እና  ዘላቂ መፍትሄን ለማፈላለግ ዳግም ተገናኝተው ለመምከር ቀጥሮ ይዘዋል። ከዚህ ሌላ መሪዎቹ ትብብራቸውን ለማጠናከር ሶስቱ ሃገራትን ያቀፉ የጋራ የመሰረተ ልማት መዋቅሮችን ለመዘርጋት የሚያስችል ዕቅድ ለመንደፍ መስማማታቸውንም መግለጫው ያብራራል። ከውይይቱ በኋላ የሱዳኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢብራሂም ጋሃንዶር ለሱዳን ትሪቡን በሰጡት ቃለ መጠይቅ ሶስቱ ሃገራት ለሃገራቸው እና ለህዝባቸው በሚጠቅሙ እንዲሁም የልማት መርሃ ግብሮቻቸውን እና የምጣኔ ሃብት ውህደታቸውን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ዙሪያ የጋራ መግባባት ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል። ኢትዮጵያ የምትገነባው ግድብ ለሶስቱም ሃገራት ጠቀሜታ ይሰጣል የሚሉት የሱዳኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ያም ቢሆን በግብጽ እና ሱዳን የውሃ ድርሻ ላይ ተጽዕኖ ማሳደር የለበትም ባይ ናቸው።

የናይል ተፋሰስ ትብብርን የመሰረቱት አስሩ ሃገራት በበኩላቸው የአባይ ወንዝን የጋራ ፍትሃዊ አጠቃቀምን በተመለከተ በምክር ቤት ደረጃ አንድ ረቂቅ ህግ አቅርበዋል። ምንም እንኳ ግብጽ እና ሱዳን ረቂቅ ህጉን ለመፈረም ፍላጎት ባያሳዩም በስድስቱ ፈራሚ ሃገራት አብላጫ ድምጽ ህጉ ገዥ ሆኖ ተግባራዊ እንዲሆን ግፊቱ ቀጥሏል።  አለመግባባት ለማንም አዋጭ አይደለም የሚለው የናይል ተፋሰስ ሃገራት ትብብር ቡድን አሁን ሶስቱ ሃገራት በግድቡ ምክንያት የሻከረ ግንኙነታቸውን ለማሻሻል እና የሰላም ውይይቱ እንዲቀጥል የጀመሩትን ጥረት በሙሉ ልብ እንደሚደግፈው ገልጹዋል።

የትብብሩ ዋና ዳይሬክተር ኢኖሰንት ናትባና በስልክ እንደገለጹልን ገለልተኛ አቋም ያለው ቡድኑ ሃገራቱ እስካሁን በሚያካሂዱት የሶስትዮሽ ውይይት ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ባይኖረውም እንዲህ ዓይነቱ ድርድር በቀጣናው የሰፈነውን ውጥረት አስወግዶ ሰላምን እና ልማትን ለማፋጠን ጠቃሚ ፋይዳ ስለሚኖረው ክፍተኛ ትኩረት እና ድጋፍ ሊሰጠው ይገባል ብለዋል። "ሶስቱ ሃገራት በግድቡ ዙሪያ ያላቸውን አለመግባባት በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት የጀመሩት ውይይትእጅግ ጠቃሚ እና የሚደገፍ ነው። ጥቅሙ ለሶስቱ ወገኖች ብቻ ሳይሆን ለአካባቢው ሃገራትም ጭምር ነው። ተደራዳሪዎቹ የሃገራቸውን ልማት እንዲያፋጥኑ እና በቀጠናውም የተረጋጋ ሰላምን ለማስፈን የጎላ ሚና ስለሚኖረው በጎ ጅማሮ ነው "

Außenminister von Ägypten und Äthiopien
ምስል DW/G.T. Hailegiorgi

ኢትዮጵያን ጨምሮ ዘጠኝ አባል ሃገራትን እና ኤርትራን በታዛቢነት አካቶ የተመሰረተው የናይል ተፋሰስ ሃገራት ትብብር እ.ኤ.አ ከ 1999 ዓ.ም ጀምሮ በውሃ ሃብት ልማት አስተዳደር እና ሀሃገራቱም መካከል የናይል ውሃ ፍትሃዊ አጠቃቀምን ለማገዝ የሚረዱ ረቂቅ ህጎችን በማዘጋጀት ልዩ ልዩ የቴክኒክ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን የትብብሩ ዋና ዳይሬክተር ኢኖሰንት ናትባና  ያስረዳሉ።

አሁን የተጀመረው ጥረት ይሳካል የሚል እምነት ያላቸው ሃላፊው ምንም እንኳ ትብብሩ ኢትዮጵያ ግብጽ እና ሱዳን በሚያካሂዱት የሰላም ውይይት እስካሁን ቀጠተኛ ተሳትፎ ያልነበረው ቢሆንም ለስኬቱ በማንኛውም ጊዜ ድጋፍ ከተጠየቀ በድርድሩ ለመሳተፍም ሆነ የቴክኒክ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ነው የገለጹልን። " እኔ አሁን የተጀመረው ውይይት ይሳካል የሚል እምነት ነው ያለኝ :: በዚህ አጋጣሚ የናይል ተፋሰስ ሃገራት ትብብር በማንኛውም ጊዜ በውይይቱ ላይ እንዲሳተፍ ጥያቄ እና ግብዣ ከቀረበለት ለመሳተፍ ዝግጁ ነን።"

ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ የጀመረችው የልማት ስራ ለግብጽ የእራስ ምታት ሆኖባታል :: በተለይም የህዳሴው ግድብ ግንባታ የውሃውን መጠን ይቀንስብኛል የሚል ስጋት ያሳደረባት ግብጽ በውሃው ላይ ያላትን ተፈጥሯዊ መብት እና ጥቅም ለማስጠበቅ የሞት ሽረት ትግል እንደምታደርግ በተደጋጋሚ ስትገልጽ ቆይታለች :: በአንጻሩ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ 2012 ዓ.ም መገንባት የጀመረችው እና 6000 ሜጋ ዋት ሃይል ያመነጫል ተብሎ የታሰበው ታላቁ የህዳሴ ግድብ 65 በመቶ  መጠናቀቁን የኢትዮጵያ መንግስት አስታውቋል።

እንዳልካቸው ፈቃደ

ኂሩት መለሰ