1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶሪያ ጦርነት፤ የዓለም ቸልተኝነት

ነጋሽ መሐመድ
ሰኞ፣ ኅዳር 26 2009

የሶሪያ ተፋላሚ ሐይላትን እንዲሸመግሉ ዓለም አቀፉ ድርጅት የወከላቸዉ ሰወስተኛዉ ዲፕሎማት ስቴፋን ደ ሚስቱራም ሥለሽምግልናዉ ዉጤት የሚዘግቡት ባይኖራቸዉ፤ የሚናገሩት አላጡም።የሟቾች ቁጥር።ደ ሚስቱራ ባለፈዉ ሚያዚያ እንዳሉት 400 ሺሕ ሶሪያዊ ተገድሏል።

https://p.dw.com/p/2TlyA
Aleppo Syrien Flüchtlinge
ምስል picture-alliance/AA

የሶሪያ ጦርነት፤ የዓለም ቸልተኝነት

የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ከ2012 ጀምሮ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ።ሥለ ሶሪያ እና የሶሪያን ጦርነት ያክል የተነጋገረበት ርዕሥ የለም።ሶሪያ ትወድማለች።የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ዛሬም ለተጨማሪ ጊዜ ሥለሶሪያዉ በተለይም ሥለ አሌፖዉ ጦርነት ይነጋገራል።አሌፖ እየጠፋች ነዉ።በሶሪያዉ ጦርነት በቀጥታ የሚሳተፉት የሞስኮ-ዋሽግተን-ብራስልስ ሐያላን፤ የደማስቆ-ቴሕራን፤የሪያድ-ዶሐ-አንካራ ተከታዮቻቸዉ ሥለ ሶሪያ ጦርነት ይወዛገባሉ-ይወጋገዛሉም።ሶሪያዉያን ያልቃሉ።የጀርመንዋ የምክር ቤት እንደራሴ ካትሪን ገሪንግ-ኤካርድት ሥለ ሶሪያ አለማዉራት አይቻልም አሉ ባለፈዉ ሳምንት።
                              
ኃያላንን ማወዳጀት-ማጋጨት፤ቱጃሮችን ማገበያየት-ማሻጠር፤ ሕዝብን-ማፋቀር ማፈጀት በርግጥ እንግዳዋ አይደለም።ስሟ እንኳን እያስማማ-ያጣላል።ነባር ነዋሪዎችዋ-ሐላብ ሲሏት፤ የሚያጋድሉ የሚያፋጁባት አሌፖ ይሏታል።በሁለተኞቹ በኩል የምናቃትም-እንደነሱዉ-አሌፖ።ከሰወስተኛዉ ዓመተ ዓለም ጀምሮ ሰዉ ከነሥልጣኔ-ስይጣኔዉ ተለይቷት አያዉቅም።እያለማ-ያጠፋታል፤ እያነሳ-ይጥላታል፤ እየገነባ ያወድማታል።
በጦርነት ኖሮ-በጦርነት የሚልፈዉ ዓለም «የዓለም» ከሚባለዉ ከሁለተኛዉ ታላቅ ጦርነት ወዲሕ ጦርነትን በድርድር-ዉይት የሚያስቀርበት፤ ማስቀረት ቢያቅተዉ የሚቀንስበት ሥልት፤ ሥልቱን የሚያስፈፅም የጋራ ድርጅት ፈጥሯል።የተባበሩት መንግሥታት-የሚለዉ።እርግጥ ድርጅቱ በ1945 እንደታለመ፤ እንደተነገረ፤ እንደተወራለት ዓለምን ከእልቂት-ጦርነት ማላቀቅ አልቻለም።መቀነሱ፤ መቀነስ ቢቀር ለመቀነስ መጣሩ ግን ሐቅ ነዉ።
45 ዘመናት የዘለቀዉ «ቀዝቃዛዉ ጦርነት» የሚባለዉ የኮሚንስት-ካፒታሊስቶች ግጭት፤ ሽኩቻ፤ተዘዋዋሪ ዉጊያ ጦርነት ከ1990ዎቹ ወዲሕ ማብቃቱ ተነገሮ፤ የሰላም ልዕልና ተሰብኮ፤ የሰዉ ልጅ እልቂት የመቆሙ ተስፋ ተዘምሮ ነበር።ከሩዋንዳ-እስከ ቦሲኒያ፤ከአፍቃኒስታን እስከ ኢራቅ፤ከሊቢያ እስከ ደቡብ ሱዳን ያየንና የምናየዉ ግን ተቃራኒዉን መሆኑ እንጂ ቀቢፀ ተስፋዉ።ሰሞኑን ተረኛዋ አሌፖ ናት።
በጀርመን ምክር ቤት የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ እንደራሴ ካትሪን ገሪንግ-ኤካርድት ባለፈዉ ሳምንት ለምክር ቤት ባልደረቦቻቸዉ እንደነገሩት ሥለአሌፖ ሳይናገሩ ምክር ቤት መሰብሰብ አይቻልም።
                             
«በዚሕ ሳምንት እዚሕ ፓርላማ ዉስጥ ተቀምጠን ሥለ አሌፖ አለመናገር አንችልም።በጦር በተከበበችዉ ከተማ ባሁኑ ወቅት 250 ሺሕ ሕዝብ ይኖራል።እነዚሕ ነዋሪዎች በየቀኑ የሶሪያ መንግሥትና የሩሲያ የጦር ጄቶች በሚጥሉት ቦምብ ይደበደባሉ።ከ2012 ጀምሮ መደበኛ የሚባል ኑሮ የለም።አራት ዓመት ጦርነት-እና በየቀኑ።»
በዚሕ ሳምንት የሶሪያዋ ትልቅ፤ ጥንታዊ፤ ታሪካዊ ከተማ እልቂት ፍጅት ደመቀ እንጂ ሌሎቹ የሶሪያ ከተማ፤ መንደሮችም ሰላም አያዉቁም።ሰላማዊ ሰዎች በየዕለቱ ያልቃሉ።የተረፉት ይሰደዳሉ ወይም ይፈናቀላሉ።በየተሰደዱ-በየተጠለሉበትም ይገደላሉ።በየዕለቱ-አራት ዓመት።
                                       
«በየዕለቱ ነጭ ቆብ አጥላቂዎች እና በሕይወት የተረፉት ሰዎች የሞቱና የቆሰሱ ሰዎችን (ያነሳሉ)።በቦምብ ከወደሙ ቤቶች አስከሬንና ቁስለኛ ያወጣሉ።ይሕ አሌፖ ዉስጥ ይፈፀማል።ማዳያ፤ ደማ፤ፈበዳኒ፤ ያሙስም የተለየ አይደለም።»
የዓለምን ሠላም እንዲያስከብር የተመሠረተዉ ዓለም አቀፍ ድርጅትም ሰላም ማስከሩን ትቶት ወይም አቅቶት አስከሬን ይቆጥራል።የሶሪያ ተፋላሚ ሐይላትን እንዲሸመግሉ ዓለም አቀፉ ድርጅት የወከላቸዉ ሰወስተኛዉ ዲፕሎማት ስቴፋን ደ ሚስቱራም ሥለሽምግልናዉ ዉጤት የሚዘግቡት ባይኖራቸዉ፤ የሚናገሩት አላጡም።የሟቾች ቁጥር።ደ ሚስቱራ ባለፈዉ ሚያዚያ እንዳሉት 400 ሺሕ ሶሪያዊ ተገድሏል።
የሶሪያዉ የሰብአዊ መብት መረብ የተባለዉ ድርጅት እንዳስታወቀዉ ደግሞ ጦርነቱ ከተጀመረ ከመጋቢት 2011 እስካለፈዉ ቅዳሜ ድረስ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ከ450 ሺሕ በልጧል።በድርጅቱ ዘገባ መሠረት ብዙ ሰዉ በመግደል የሶሪያ መንግሥት፤ የሩሲያ ጦር፤ ISIS እና አልኑስራ የተባሉት ድርጅቶች፤የአማፂያኑ ሕብረት፤ ዩናይትድ ስቴትስ መራሹ ሕብረ-ብሔር ጦር፤ ከአንድ እስከ አምስተኛ ያለዉ ደረጃ ይይዛሉ።
የዓለም አቀፉ ድርጅት ዘዋሪዎች በተለይም በፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ድምፅን በድምፅ የመሻር ሥልጣን ያላቸዉ ሐይላት ያዘመቱት ወይም የሚደግፉና የሚያስታጥቁት ጦር ሶሪያዉያንን እየፈጀ ሥለሰላም እንነጋገር ይላሉ።የሐያላኑ ዲፕሎማቶች ከኒዮርክ እስከ ብራስልስ፤ ከዤኔቭ እስከ ኩዌት ይሰበሰባሉ፤ ይነጋገራሉ።መሪዎቻቸዉ ከዋሽግተን-ሞስኮ፤  በሚያስተላልፉት መልዕክት ለሰላም መቆማቸዉን ያወራሉ።ጦርነቱን ግን ከመሰብሰብ-መነጋገራቸዉ፤ መናገራቸዉ  በፊት እንደነበረዉ ይቀጥላሉ-ያስቀጥላሉ።አምስት ዓመት።ባለፈዉ ወርም ያዉ ነበር።ኒዮርክ-ስብሰባ ዉይይት ሶሪያ እልቂት።እንዲያዉም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ርዳታ ጉዳይ ምክትል ዋና ፀሐፊ ስቴፈን ኦብሬይን ለፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ስብሰባ እንደነገሩት ዓለም እልቂት ፍጅት ለሶሪያዉያን የተለመደ አይነት ስሜት እያደረበት ነዉ።
                         
«እንደገና በዚሕ ወር እዚሕ ስንሰበሰብ የአሌፖ እና የመላዉ ሶሪያ ሕዝብ ስቃይ እንደቀጠለ ነዉ።ዘግናኝ ድርጊት አሁን የዕለት-ከዕለት እዉነት ነዉ።ዓለምም ለሶሪያና ለሶሪያዉያን እንደተመደ ድርጊት እየቆጠረዉ ነዉ።»
ባለፈዉ ሳምንትም የተለየ አልነበረም።ማክሰኞ፤ ሞስኮ።የሩሲያዉ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ሶሪያ ያዘመቱት ጦር አሸባሪነትን የመዋጋት ተልዕኮዉን እየተወጣ አሉ።
                               
«ልበወለዱን የአለም ስጋት የሚባለዉን ሳይሆን እዉነተኛዉን አሸባሪነትን ለመዋጋት ሐይላችንን ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር እንደምናስተባብር ጥርጥር የለዉም።ሶሪያ የዘመቱት ወታደሮቻችን ይሕን ተልዕኮ እየተወጡ ነዉ።አሸባሪዎች ከፍተኛ ጥፋት እያደረሱ ነዉ።የሩሲያ ጦር ከነባሩ የጦር ሰፈሩ ዉጪም የተሳካ ሥራ መስራት እንደሚችል አረጋግጧል።»
ለፕሬዝደንት ፑቲን፤ ለፕሬዝደንት በሽር ዓል አሰደ፤ ምናልባት ለቴሕራን አያቱላሆች የሩሲያ ጦር ሶሪያ ዉስጥ የሚዋጋዉ አሸባሪዎች ነዉ።ተመራጩ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደት ዶናልድ ትራምፕ የፕሬዝደትነቱን ስልጣን ሲይዙ እስካሁን ያሉትን ገቢር ማድረግ-አለማድረጋቸዉ በርግጥ ወደፊት ነዉ የሚታየዉ።ዛሬ ያሉትን ነገ አለመድገማቸዉ ወይም መቀየራቸዉም ተደጋግሞ ታይቷል።
የተናገሩትን አደረጉትም አላደረጉት በሶሪያዉ ጦርነት ከእስካሁኑ የአሜሪካ መርሕ የተለየ መርሕ እንደሚከተሉ አስታዉቀዋል።ትራምፕ በምርጫዉ ማሸነፋቸዉ በተነገረ በሁለተኛዉ ሳምንት ለዎልስትሪት ጆርናል በሰጡት መግለጫ ከፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ይልቅ የፕሬዝደንት አሰድን ወይም የፑቲንን ሐሳብ የሚጋሩ መስለዋል።ትራምፕ «እንደሚመስለኝ» አሉ «እኛ ሶሪያን እንወጋለን፤ ሶሪያ ደግሞ እስላማዊ መንግስት (IS) ትዉጋለች።---ባሁኑ ወቅት የሶሪያ መንግሥትን የሚወጉ አማፂያንን እንደግፋለን፤ እነዚሕ አማፂያን እነማ እንደሆኑ ግን አናዉቅም።»
ትራምፕ የሚከተሉት መርሕ በገቢር ለማየት ወራት መጠበቅ ግድ ነዉ።የፑቲን ንግግር ከሞስኮ በተሰማ ማግስት የጀርመን የክርስቲያን ዴሞክራቶቹ ሕብረት (CDU) የምክር ቤት እንደራሴ ኖርበርት ሮቲገን ከበርሊን እንዳስታወቁት ግን ሞስኮ፤ ደማስቆም ሆነች ቴሕራን ሰላም እንዲሰፍን እይፈልጉም።
                              
«ወታደራዊ እርምጃ መፍትሔ እንደማይሆን በተደጋጋሚ እንናገራለን።ዓረፍተ ነገሩ ልክ ነዉ።ይሁንና ፕሬዝደንት ፑቲን የሚያስቡትና የሚያደርጉት ተቃራኒዉን ነዉ።»
ጦርነቱን በድርድር ለማቆም የቀድሞዉ የዓለም ትልቅ ዲፕሎማት ኮፊ አናን ሞከረዋል።ከስድት ወር በላይ መቀጠል አልቻሉም።ሌላዉ ዕዉቅ ዲፕሎማት ላሕዳር ብራሒሚ ከዓመት ከመንፈቅ በላይ ጥረዋል።ጠብ ያለ ነገር ሳይኖር በበቃኝ አቁመዋል።አሁን ስታፋን ደ ሚስቱራ ላይ ታች እያሉ ነዉ።ተፋላሚ ኃይላት ጦርነቱን ማቆም አይደለም ሥለሚቆምበት መንገድ ለመነጋገር እንኳን ፈቃደኛ አይደሉም።ፍቃደኛ ቢሆኑ እንኳን የደጋፊ፤ አስታጣቂያዎቻቸዉን ፊት ማየት ግድ አለባቸዉ።
የሞስኮ-፤ ዋሽግተን፤በርሊን ፖለቲከኞች ሥለሶሪያ ጦርነት በተለይም ስለ አሌፖዉ ዉጊያ በሚያወሩበት፤ ባለፈዉ ሳምንትም ሎዛን-ስዊዘርላንድ ዉስጥ ድርድር የሚባል ስብሰባ ነበር።በስብሰባዉ ላይ የብዙ ሐገራት ተወካዮች ተገኝተዋል።
የጀርመኑ የምክር ቤት እንደራሴ ኖርበርት ሮቲገን እንዳሉት ስብሰባዉ እና የተስብሳቢዎቹ ማንነት አስገራሚ፤ አጠያያቂም ብጤ ነዉ።ጀርመን እንደሐገር፤ የአዉሮጳ ሕብረት እንደትልቅ ድርጅት አልተካፈለም።
                                     
«አዉሮጳ ተፅዕኖ ማሳረፍ አለመቻሉን የሚጠራጠር ካለ የመንግሥታት ተወካዮች ፖለቲካዊ መፍትሔ ለማፈላለግ ወደ ተሰበሰቡበት ወደ ሎዛን ይመልከት።በዚሕ ድርድር ላይ ቱርክ ትሳተፋለች።በዚሕ ድርድር ላይ ሰወስት መቶ ሺሕ ሕዝብ ያላት ቀጠር ተሳታፊ ናት።ከ28ቱ የአዉሮጳ ሕብረት አባል ሐገራት አንድም ሐገር አልተሳተፈም።ሕብረቱ ራሱም አልተካፈለም።»
ሶሪያ ምን ይላል።አጃኢብ ይልሆናል።ግን የእልቂት-ዉድመት ሽሽት-ሥጋቱን አቁሞ ሎዛን-በርሊን፤ ሞስኮ ዋሽግተኖችን ማድመጥ መቻሉ ግን አጠራጣሪ ነዉ።አሌፖ ሮብ። 
                                      
«ከቤት ልንወጣ ስንል እናቴ የሆነ ነገር ለመያዝ ትታገል ነበር።ድንገት ፍንዳታዉን ሰማን።ሮጥን።እነሱን ለማየት ስንመለስ እናቴ ሞታለች።እሕቴም ሞታለች።ሌለኛዋ እሕቴ አልሞተችም ነበር።ግን እስካሁን ሥለሷ ምንም አልሰማንም።ሆስፒታል ሳትሆን አትቀርም።ምን ማለት እችላለሁ።ፈጣሪ ይሕን ፈልጎ ይሆን?»
መልስ የሰጠ የለም። ካለም አይታወቅም።የሚታወቀዉ ዉጊያ መቀጠሉ ነዉ።ሕዝብ ማለቅ፤መቁሰል፤ መሰደድ፤ መራብ መጠማቱ ነዉ።አምስት ዓመት።እስከ መቼ? ቸር ያሰማን። 

Syrien Aleppo Trümmer Kinder Ruinen
ምስል Reuters/A. Ismail
Staffan de Mistura, Syrien Gespräche
ምስል UN Photo/Violaine Martin
US-Außenminister John Kerry Staffan de Mistura und Sergey Lavrov
ምስል picture alliance/abaca/F. Aktas
Aleppo Syrien Ruinen
ምስል Reuters/Sana

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ