1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ

ሰኞ፣ ኅዳር 4 2010

ዚያድ ባሬን ወታደራዊ የሶማሊያ መንግስት መዉደቅ ተከትሎ ራሷን እንደ ሀገር ማስተዳደር የጀመረችዉ ሶማሌላንድ በዛሬዉ እለት አዲስ ፕሬዚዳንት ለመምረጥ ነዋሪዎቿ ድምፅ ሲሰጡ ዉለዋል።

https://p.dw.com/p/2nYNu
Somaliland Wahlen
ምስል Getty Images/AFP

Somali Land presidental Election 2017 - MP3-Stereo

 700 መቶ ሽህ መራጮች ይሳተፉበታል በተባለዉ በዚህ ምርጫ ፤ ለሀገሪቱም ሆነ ለአፍሪቃ የመጀመሪያ ነዉ የተባለ  አዲስ የመራጮች መመዝገቢያ ቴክኖሎጅ  ጥቅም ላይ መዋሉን ዓለም አቀፍ የምርጫ ታዛቢወች ገልጸዋል።
ፕሬዚዳንት አህመድ መሀመድ ማህሙድን  ለመተካት የሶማሌላንድ  ነዋሪወች ዛሬ ከማለዳዉ ጀምሮ ለ3 እጩ ተወዳዳሪዎች ድምፅ  ሲሰጡ  ዉለዋል።በዚህ ምርጫ ሙሴ ባሂ ከገዥዉ

« ኩልሚየ» ፓርቲ ፣እንዲሁም አብዱራህማን ኢሮና ፈይሰል አሊ ዋራቢ የተቃዋሚ ፓርቲን ወክለዉ ተወዳድረዋል።የተቃዋሚ ፓርቲ እጩዎቹ ከዚህ ቀደም በጎርጎሮሳዊዉ  2010  ዓ/ም በተካሄደዉ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተሸናፊ የነበሩ ናቸዉ ተብሏል። እጩዎችም ከምርጫዉ ከመካሄዱ በፊት ለመራጩ ህዝብ በሀገሪቱ የፓለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የስራ እድል ፈጠራና እንዲሁም በሀገሪቱ አለም አቀፋዊ እዉቅና ዙሪያ በቴሌቪዥን ክርክር ማድረጋቸዉ ተገልጿል።
በሀገሪቱ በየ 5 አመቱ ምርጫ የሚካሄድ ቢሆንም በድርቅና ተዛማጅ ችግሮች ሳቢያ የዘንድሮዉ ምርጫ መካሄድ ከነበረበት ግዜ  በሁለት አመት መዘግየቱ ተመልክቷል። ሀገሪቱ ከአሁን ቀደም 3 ምርጫወችን ያካሄደች ሲሆን በአለም አቀፍ ታዛቢዎች ዘንድ ሰላማዊና የተረጋጋ መሆኑ ሲገለፅ ቆይቷል።በዛሬዉ እለት ለአራተኛ ጊዜ የተካሄደዉን  የሀገሪቱ ምርጫም ፤  ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ በጠዋት መጀመሩን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል የተቃዋሚ ፓርቲ እጩወችን ጠቅሶ  ዘግቧል።
ከ700 ሺህ በላይ መራጮች ተመዝግበዉበታል በተባለዉ በዚህ ምርጫ በአፍሪካ የምርጫ ሂደት የመጀመሪያ ነዉ የተባለ ያለምንም ንክኪ በአይን ብቻ መራጮችን መቆጣጠር የሚያስችል መሳሪያ ጥቅም ላይ መዋሉን ታዛቢወች ገልፀዋል።   በሀገሪቱ  ከ60 በላይ ታዛቢወች የተሰማሩ  ሲሆን በለንደን ዩንቨርሲቲ የምስራቃዊና የአፍሪቃ ጥናቶች ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ላዉራ ሃሞንድ  አለም አቀፍ የታዛቢወች ተልዕኮ በምህጻሩ /EOM/ ካሰማራቸዉ ታዛቢወች መካከል አንዷ ናቸዉ።ባለሙያዋ ምርጫዉን በተመለከተ ለዶቼ ቬለ በሰጡት ማብራሪያ  በሀገሪቱ  ከምርጫዉና  ከዉጤቱ  ይልቅ ሌሎች ሊተኮርባቸዉ የሚገቡ ጉዳዮች አሉ።

Somaliland Wahlen
ምስል Getty Images/AFP

«ማንያሸንፋል የሚለዉን ከማየታችን በፊት መነሳት ያለባቸዉና ሊያወያዩ የሚቺሉ ብዙ አስፈላጊ  ነገሮች አሉ።በሶማሌ ላንድ   ዉስጣዊ የፓለቲካ  ሁኔታወችና አዳዲስ አደረጃጀቶች ፣ ሀገሪቱ ከኢትዮጵያና  ከተባበሩት አረብ ኢሜሬትስ ጋር ያላት የንግድ ጝንኙነት ፣ ከሶማሊያ ጋር ያላት የወደፊት ግንኙነትና ሌሎችም ጉዳዮች ሊተኮርባቸዉ የሚገቡ  ጥያቄወች ናቸዉ።»
 የ4 ሚሊዮን ሰወች መኖሪያ የሆነችዉ ሶማሌ ላንድ፤ተደጋጋሚ  ምርጫች ብታካሂድም በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ እስከ አሁን  ሙሉ ለሙሉ እንደሀገር  እዉቅና አማግኘቷ ይነገራል።  ያም ሆኖ ግን አለም አቀፍ ታዛቢወች ምርጫወቹን ሲታዘቡ ይታያል።ይህ ለሀገሪቱ  እዉቅና እንደ መስጠት አይቆጠርምን? ለባለሙያዋ የቀረበ ጥያቄ ነበር። 
«እንደማስበዉ አለም አቀፉ የታዛቢወች ቡድን በእርግጠኝነት  የሚፈልገዉና የሚያተኩረዉ   የሶማሌ ላንድ ምርጫ ያለምንም ችግር ሰላማዊና ህግን የተከተለ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ለአለም አቀፉ መህበረሰብ ማሳየት ነዉ።ይህ ምርጫ አለም አቀፉ ማህበረሰብ የሀገሪቱን እዉቅና መደገፉን የሚያሳይ ምልክት ነዉ ብዬ አላስብም።የሀገሪቱ እዉቅና በማንኛዉም ጊዜ ከደቡቡ ክፍል ጋር በሚደረግ ድርድርና  ስምምነት የሚመጣ ነዉ።»
 የሀርጌሳና የሞቃዲሾ መንግስታት  ከእዉቅና በፊት ለዉሳኔ  የሚያደርሱ ዉጤታማ ዉይይቶችን ሊያደርጉ ይገባል ሲሉም  ዶክተር ራሞንድ ያብራራሉ።  
« በሀርጌሳና በሞቃዲሾ መንግስታት መካከል የንግድ፣አለም አቀፍ ወንጀልን በጋራ የመከላከል፣ በስደት ፣ በመገናኛ ዘዴዎችና በሌሎች ጉዳዮች ከመጨረሻዉ የእዉቅና ዉሳኔ በፊት  ዉይይት ሊካሄድባቸዉ ይገባል። ያ ነዉ ለዉጤታማ ዉይይት በር የሚከፍተዉ።»
ሶማሌላንድ በጎርጎሮሳዊዉ 1960  ከብሪታንያ የሞግዚት አስተዳደር ነጻነቷን አግኝታ ከሶማሊያ ጋር ብትቀላቀልም በሀገሪቱ ከተካሄደዉ መራራ ጦርነትና ከሲያድ ባሬ መንግስት ዉድቀት በሁዋላ በ1991 ከቀሪዉ የሶማሊያ ግዛት ተገንጥላ ራሷን እንደ ሀገር ማስተዳደር መጀመሯን  መረጃዎች ያመለክታሉ።  

Somaliland Wahlen
ምስል Getty Images/AFP

ፀሐይ ጫኔ

ሂሩት መለሰ