1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶማሊያ የሰላም ንግግር

ረቡዕ፣ ሐምሌ 12 1998

የሶማሊያ የሽግግር መንግስት ፕሬዝዳንት አብዱላሂ ዩሱፍ

https://p.dw.com/p/E0iQ
ምስል AP

የሶማሊያ የሽግግር መንግስት አብዛኛውን የሶማሊያ ደቡባዊ ክፍል ከተቆጣጠረው የሸሪያ ፍርድ ቤቶች ህብረት ጋር ለመነጋገር ተስማማ ። በአሁኑ ሰዓት በእጅጉ የተዳከመው የሽግግር መንግስቱ በዕርቀ ሰላሙ ንግግር ለመሳተፍ የተስማማው በዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ግፊት መሆኑን የሽግግር መንግስቱ ቃል አቀባይ አብዱራህማን ሞሀመድ ዲናሪ አስታውቀዋል ። በቅርቡ ሞቃዲሾን ከተቆጠረ በህዋላ ይዞታውን ያስፋፋው የሸሪዓ ፍርድቤቶች ህብረት የህዝቡ ድጋፍ ቢኖረውም በውጭው ዓለም ዘንድ ግን በጥርጣሬ ነው የሚታየው ። የቀድሞው የሶማሊያ መሪ ዚያድ ባሬ ከስልጣን ከወረዱ ከዛሬ አስራ አምስት ዓመት ወዲህ በሶማሊያ ብጥብጥ ረሀብ ሽብር እና ጥፋት ነው ሰፍኖ የቆየው ። ዋና ከተማይቱ ሞቃዲሾም ከባግዳድ ቀጥሎ በዓለማችን አደገኛ ከሚባሉት ከተሞች አንድዋ ናት ። እአአ ከሺህ ዘጠኝ መቶ ዘጠና አንድ አንስቶ ሞቃዲሾን ሲቆጣጠሩ የቆዩት የጦር አበጋዞች ባለፈው ወር በሸሪዓ ፍርድቤቶች ህብረት ተሸንፈው ከተማይቱን ለቀው ወጥተዋል ። በጦር አበጋዞቹ ዘመን ህዝቡ በፍርሀትና በጭንቀት ነበር የሚኖረው ። ህብረቱ ሞቃዲሾን ከተቆጣጠረ ወዲህ ግን ሁኔታው ተቀይሮዋል ። በከተማይቱ ፀጥታ ሰፍኖዋል ። ለዚህም ህዝቡ ትልቅ ግምት ሰጥቶታል ። በዚህ ባልተጠበቀ ሁኔታ ሙስሊም ሚሊሽያዎቹ በሶማሊያ ሰላም የማያመጡ ነው የሚመስለው ። ከዚህ ቀድም ሰላም በሶማሊያ ትርጉም የለሽ ተደርጎ ነበር የሚወሰደው ። አሁን ግን የሰላም ተስፋ ይታያል ። ሆኖም ግን አሁንም ቢሆን በሞቃዲሾ መቶ በመቶ ፀጥታ ሰፍኖዋል ማለት አይቻልም ። በኬንያ የሶማሊያ አምባሳደር ሞሀመድ አፌይ
“በሞቃዲሾ በአጠቃላይ የፀጥታው ሁኔታ ፍፁም አይደለም ። እንደምታውቁት በዋና ከተማይቱ በሞቃዲሾ መቶ በመቶ ፀጥታ አለ ብለን ማረጋገጥ አንችልም ።ነገርግን እንደሚመስለኝ የሶማሊያ ህዝብ ውይይት እንዲደረግ ቁርጠኝነቱን አሳይቶዋል ። ሁሉም የፍርድቤቱ ህብረት አባላት አይደሉም ። ሆኖም ህብረቱ የህዝቡ ፣ የሲቪል ማህበራት ፣ የንግዱ ማህበረሰብና የባህላዊ መሪዎች ከፍተኛ ድጋፍ አለው ። ሁሉም ፀጥታና መረጋጋት ስለሚፈልጉ አንድ ሆነዋል ። “
የሸሪዓ ፍርድቤቶች ህብረት በራሳቸው የቆሙ አክራሪ የሀይማኖት መሪዎችንና ነጋዴዎችን ያቀፈ ነው ። ህብረቱ በዩናይትድ ስቴትስ የሽብርተኝነት መፈልፈያ ተደርጎ ነው የሚወሰደው ። ከዋና ከተማይቱ ከሞቃዲሾ ሁለት መቶ ሀምሳ ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የተዳከመው የሶማሊያ የሽግግር መንግስት ህብረቱን በይፋ እንደ ተደራዳሪ አይቀበለውም ።ይሁንና የሽግግር መንግስቱ አሁን ከህብረቱ ጋራ ለመደራደር ተስማምቶዋል ። የሶማሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር አሊ ሞሀመድ ጌዲ
“ ለሸሪዓ ፍርድቤቶች ህብረት ዕውቅና እንሰጣለን ። ሆኖም ግን ከአልቃይዳና ከሽብርተኞች ጋር ግንኙነት ካላቸው አክራሪዎች ጋር አንደራደርም ። ከሼህ አዌይስ ጋር መደራደር ማለት ከቢን ላደንና ከአጋሩ ከአልቄይዳ ጋር መነጋገር ማለት ነው ። “

የህብረቱ መሪ ሀሰን ዳሂር አዌይስ ሶማሊያን ለአፍሪቃ የቀንደኛ ሽብርተኞች ማገናኛ ድልድይ ያደርግዋትዋል ተብለው በሶማሊያ የሽግግር መንግስትና በዩናይትድ ስቴትስ ይጠረጠራሉ ። ይሁና የዚህ ጥርጣሬ ማረጋገጫ ግን እስካሁን አልተገኘም ። ህዝቡ ደግሞ ከደካማው የሽግግር መስግስት ሚሊሽያዎቹን ነው ያመነው ። በዚህ የተነሳም የሽግግር መንግስቱ ለመግባባት ራሱን ማዘጋጀት እንዳለበት ነው የሚታመነው ። ከዚህ አንፃር ይመስላል የሽግግር መንግስቱ ፕሬዝዳንት አብዱላሂ ዩሱፍ ከዚህ ቀደም የተቃወሙትን የድርድር ሀሳብ እንደገና ተቀብለውታል ።
የሶማሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር አሊ ሞሀመድ ጌዲ

“ከሸሪዓ ፍርድቤት አባላት ጋር እንገናኛለን ። ሆኖም ግን ባለፉት ጥቂት ሳምንታት የተኩስ አቁም ስምምነቱን ከጣሱት በሞቃዲሾ የርስ በርሱ ጦርነት የዘር ማጥፋት ወንጀል ከፈፀሙትና ንብረት ካወደሙት ጋር ግን አብረን አንቀመጥም ። “

ወደፊት የታሰበው የሰላም ንግግር በትክክል ተሳክቶ ከተካሄደ ከዓመታት በህዋላ በሶማሊያ ሰላም የመስፈኑን ተስፋ አሳድሮዋል ። ይህ ካልሆነ ግን ሀገሪቱ በሞላ ጦርነት ያሰጋታል ።