1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶማሊያ ስደተኞችና ጀርመን

ዓርብ፣ ጥቅምት 23 2005

በዓለም ውስጥ እጅግ በዛ ያሉ ስደተኞች በሚገኙበት በኬንያ ሰሜናዊ የድንበር ግዛት ፤ ዳዳብ ላይ 150,000 ሰዎችን የሚረዳውን መታከሚያ ክሊኒክ ለመደገፍ በጎ ፈቃድ ቢኖርም፤ በሥራ አመራር ረገድ ፤ የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚንስቴርና የልማት፤

https://p.dw.com/p/16c8E
ምስል AP

ተራድዖ ሚንስቴር እስከመነታረክ ደርሰዋል። የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር፤ በመጪው 2013 ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት በተጠቀሰው ቦታ ለሚገኙ ስደተኞች ገንዘብ አላወጣም በማለቱ ፣ መቶ ሃምሳ ሰዎች የተጠለሉበት ጣቢያ ሳይዘጋ አይቀርም የሚል ጭምጭምታ አለ።

Flüchtlingslager Dadaab Kenia
ምስል AP

ዘለቄታ ላላቸው የልማት ፕሮጀክቶች እርዳታ የሚሰጠው የጀርመን የልማት ተራድዖ ሚንስቴር ሲሆን ፣ ካለፈው ዓመት ከግንቦት ወር አንስቶ ሰብአዊ እርዳታ መለገስ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ብቻ ሥልጣን ነው።

የልማት ተራድዖ ሚንስትሩ የነጻ ዴሞክራቱ ፓርቲ (FDP) ኣባላ ዲርክ ኒበል፣ ከትናንት በስቲያ Volkszeitung ለተሰኘው የላይፕዚኽ ጋዜጣ በሰጡት ቃል፣ የፓርቲያቸው አባል ፣ ጊዶ ቬስተርቭለ የሚመሩትን ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር፣ «የሶማልያ ስደተኞች በቂ እርዳታ እንዲደርሳቸው አላደረገም» በማለት ወቅሰዋል።

በጀርመን ዓለም አቀፍ የቴክኒክ ተራድዖ ድርጅትና በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን በኅብረት ሲንቀሳቀስ የቆየው ክሊኒክ፣ ሥራ ማስኬጃው ገንዘብ እስከ ታኅሳስ ወር መጨረሻ ገደማ ሳይሟጠጥበት እንደማይቀር በሚነገርበት ባሁኑ ወቅት፣ የሁለቱ መሥሪያ ቤቶች ጭቅጭቅ፣ ስደተኞቹ እርዳታው እንዲጓደልባቸው ያደርግ ይሆን?! የሚል የአንክሮ ጥያቄ ከታዛቢዎች በኩል ማስነሳቱ አልቀረም።

ተረጂዎቹንም በአጅጉ ያሳስባቸው ይሆናል። የሁለቱን መ/ቤቶች ንትርክ በጥሞና የተከታተለው የዶጨ ቨለ የአንግሊዝኛው ክፍል ባልደረባ ዳንኤል ፔልትዝ እንዲህ ይላል።

Dossierbild Afrika Hungersnot 2011 Bild 2
ምስል AP

«እንደሚመስለኝ፤ በአሁኑ ሰዓት ድንጋጤ የሚያስከትል ምክንያት የለም። ምክንያቱም የውጭ ጉዳይ ሚንስቴሩ ቃል አቀባይ፣ በዚህም ሆነ በዚያ፣ በዳዳብ የሚገኙትን ስደተኞች በአርግጥኝነት እንረዳለን ሲሉ ቃል ገብተዋል ። ልብ ማለት ያለብን፤ የቢሮክራሲ አሠራር በመኖሩ፣ እንዲሁ በመሥሪያ ቤቱ አንድ ጧት ተነስቶ፣ አሁን ለስደተኞቹ ገንዘብ እንስጥ እንደማይባል ነው። የተለያዩ መ/ቤቶችን የሚያገናኝ አሠራር ይኖራል። ማሳሰቢያዎችና የበጀት ሂሳብ ---ይህ ሁሉ ይዘጋጃል። ስለሆነም፣ ሚንስቴሩ ምናልባት ለመዘጋጀት፣ በጀቱን ለመመደብ በ UNHCR ከሚገኙ ተባባሪዎች ጋራም ለመመካከር ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልገው ይሆናል። አሁን የሚሻለው፣ ሚንስቴሩ ምን እንደሚወስን ጉዳዩን ከቅርብ በጥሞና መከታተል ነው።»

Hungersnot in Somalia
ምስል dapd

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን በበኩሉ፤ ከሌሎች ተባባሪዎች ጋር ተባብሮ በመሥራት የዳዳብ መጠለያ ጣቢያ ክሊኒክ፣ በመጪው ዓመት ጎርጎሪዮሳዊ ዓመትም ሥራውን እንዲቀጥል እናደርጋለን ነው ያለው። የሥራ ተባባሪዎች ሳይሆኑ አይቀሩም ተብለው ከታሰቡት መካከል፣ የኬንያ ቀይ መስቀል ማህበርና ድንበር አያግዴው የሀኪሞች ማኅበር ይገኙበታል። ከጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ብቻ UNHCR በመጪው 2013 ጎርጎሪዮሳዊ ዓመትም፣ 3,2 ሚሊዮን ዩውሮ ያገኛል እንደሚያገኝ ነው የተነገረው። በጀርመን ፓርላማ ፣ የነጻ ዴሞክራቱ ፓርቲ አባላት የሰብአዊ መብትና ሰብአዊ እርዳታ ጉዳይ ቃል አቀባይ ወ/ሮ ማሪና ሹስተር ለሶማሊያ ስደተኞች የሚሰጠው እርዳታ እንደማይቋረጥ ነው የገለጡት።

የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚንስቴርና የልማት ተራድዖ ሚንስቴር በቃላት ቢነታረኩም፣ ለሶማሊያ ስደተኞች የህክምናው እርዳታ እስካሁን እንዳልተጓደለባቸው፤ ከዳዳብ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ አንዲት ቃል አቀባይ ትናንት አረጋግጣለች።

500,000 ገደማ ስደተኞችን የሚያስተናግደው፣ ዳዳብ፤ በዓለም ውስጥ እጅግ ግዙፉ የመጠለያ ጣቢያ መሆኑ ይነገርለታል። በዚያ የሚገኙት በአመዛኙ የሶማልያ ስደተኞች ናቸው። አንዳንዶቹ ፤ ከ 20 ዓመት ገደማ በፊት በመጀመሪያው ዙር የእርስ-በርስ ጦርነት ሸሽተው ዳዳብ የገቡ ናቸው። በዳዳብ፤ ተላላፊ በሽታ፤ የንጽህና ጉድለትና ንፁህ የሚጠጣ ውሃ አቅርቦት ችግር አልተወገደም። ያም ሆነ ይህ፤ ከሞላ ጎደል የተሟላ የጤና አገልግሎት ማቅረብ ፍጹም ችላ ሊባል የማይገባ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግዴታ ነው።

ተክሌ የኋላ

ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ