1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶማሊያ ሁኔታና የሽግግር መንግስቱ

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 26 1999

በኢትዮጵያ መንግስት ወታደሮች ድጋፍ ተገድቦበት ከከረመዉ ባይደዋ ወጥቶ ደቡባዊ ሶማሊያን በስፋት ለመያዝ የቻለዉ የሶማሊያ የሽግግር መንግስት በሳምንቱ መጀመሪያ መግለጫ አዉጥቷል። በዚህ መግለጫ መሰረትም ህዝቡ ያለዉን ማንኛዉንም የጦር መሳሪያ በሶስት ቀናት ዉስጥ እንዲያስረክብ ጠይቋል።

https://p.dw.com/p/E0hW
ኢትዮጵያዊ ወታደር በመቋዲሾ
ኢትዮጵያዊ ወታደር በመቋዲሾምስል AP

ዛሬ ደግሞ የተሰጠዉ የጊዜ ገደብ የሚያበቃበት ዕለት ነዉና ወደመቋዲሾ ስልክ ደወልን። የሽግግር መንግስቱን ቃል አቀባይ አብዱራህማን ዲናሬን ጠየቅናቸዉ። ለመሆኑ ትጥቅ ማስፈታቱ ምን ያህል ተሳክቷል ስንል፣

«ትናንት የተወሰኑት የሚሊሺያ መሪዎች መሳሪያቸዉን አስረክበዋል። አሁን ተጀምሯል ማለት ይቻላል። መንግስት አሁንም ከመቋዲሾ መሪዎች በተለይም ከሚሊሺያ መሪዎቹ ጋር እየመከረበት ነዉ። እንደሚመስለኝ አሁን ተጀምሯል። በቀጣይ ቀናትም ትጥቅ ማስፈታቱን እንቀጥልበታለን።»

እሳቸዉ ይህን ቢሉም ከዜና አዉታሮች የሚነበበዉ ዘገባና እኛም ያነጋገርነዉ የመቋዲሾ ኗሪ እንደገለፀልን የከተማዋና አካባቢዉ ኗሪዎች መኣሪያችንን ብናስረክብ የታጠቁ ዘራፊዎች መጫወቻ እንሆናለን የሚል ስጋት አለዉ። እናም ቃል አቀባዩን ይህን እንዴት ያዩታል አልኳቸዉ

«ስሚኝ! መንግስትን ካላመኑ ማነዉ የህዝቡን ሰላም ማረጋጋት የሚችለዉ? መንግስት የአገር ሃላፊነት ያለዉ ነዉ። መላ አገሪቱንም ተቆጣጥሯል። ስለዚህ ይህ በፍፁም ተቀባይነት የሌለዉ አባባል ነዉ። የእስላማዊዉ ሸብጎ ርዝራዦች መኖራቸዉን በመፍራት መሳሪያቸዉን መስጠት አልፈለጉም? ይህ ቀልድ ነዉ። ዋናዉ ነገር ግን አብዛኛዉ ህዝብ መሳሪያዉን ለመስጠት እየጠበቀ መሆኑ ነዉ። ትጥቅ የመፍታትን ነገር የሚቃወሙት የጦር አበጋዞቹ ናቸዉ። እነሱ ሚሊሺያዎቻቸዉ ትጥቅ እንዳይመልሱ የሚያደርጉት።»

ዛሬ ማለዳ የተሰማ ዘገባ እንደሚያሳየዉ ነፍጥ ያነገቡት ሚሊሺያዎች የነዳጅ ታንክ መትተዉ ሰዎችን ጎድተዋል። ይህ በቃል አቀባዩ አገላለፅ ከሰዎች ገንዘብበህገ ወጥ መንገድ ለመዝረፍ የሚፈልጉ ሚሊሺያዎች የፈፀሙት ተግባርነዉ። ከዚህ ጋር በተገናኘ አሁን በመቋዲሶ አካባቢ ያለዉ ሁኔታ አሁን ተረጋግቷል ደህነቱም ተረጋግጧል ማለት ይቻላል? ለሚለዉ ቀጣይ ጥያቄ ጌዲ ይህን ብለዋል

««ሰላም ነዉ ተረጋግቷል። በጣም ጥቂት ወገኖች ለመበጥበጥ ይሞክራሉ። ፖሊሶቻችን በየስፍራዉ ጣቢያ በማቋቋም እየተንቀሳቀሱ ነዉ። በእርግጠኛነት የአገሪቱን ደህንነትና መረጋጋት እናረጋግጣለን። ምክንያቱም የመቋዲሾ ህዝብ ባለፉት 16ዓመታት ባሳለፈዉ የእርስ በርስ ጦርነት ተሰላችቷል። የመንግስትን መረጋጋት ይፈልጋሉ። ነገር ግን እንደለመታደል ሆኖ የእስላማዊዉ ሸንጎ ርዝራዦች ደግሞ አለመረጋጋትን ለመፍጠር ይሞክራሉ። አብዛኛዎቹ ከተሞች በሚገባ በደስታ ነዉ የእኛን ኃይሎች የተቀበሏቸዉ። አሁን እንዲህ በጥቅሉ የደህንነት ችግር የለም ማለት ይቻላል። ትጥቁን አስፈትተን ስናጠናቅቅ ደግሞ የተሻለ ይሆናል። ነገሩም የራሱ የሆነ ዘዴና ስልት እንደሚያስፈልገዉ እንረዳለን። ላለፉት 16 ዓመታት ወደሶማሊያ የገቡት በርካታ የጦር መሳሪያዎች ናቸዉ። በአጭር ቀነ-ገደብ ዉስጥ ይጠናቀቃል ማለት አይቻልም። እኛ ግን ደህነቱን እስክናረጋግጥ ድረስ እንቀጥላለን።»

የሽግግር መንግስቱ የአገር ዉስጥ ሚኒስትር የሆኑት ሁሴንሞሃመድ ፋራህ አይዲድ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል ያለዉ ድንበር ተወግዶ አንድነት ፈጥረዉ በአንድ ፓስፖርት መጠቀም እንዳለባቸዉ የተናገሩትን በመጥቀስ ይህን ሲሉ ምን ማለት ነዉ ብያቸዉ ነበር። ሲመልሱም አይዲድ የተናገሩት እንደአንድ ግለሰብ እንጂ እንደመንግስት አይደለም ይላሉ ዲናሬ

«ይህ የግላቸዉ አስተያየት ነዉ። የመንግስት ፖሊሲ አይደለም። እንደሚታወቀዉ እኛ ብዙ ተግባራትን ማከናወን አለብን። አሁን አንድ ፓስፖርትና አንድ ወደብ እንጠቀማለን ለማለት ጊዜዉ በጣም ገና ነዉ። የመንግስት ፖሊሲ አሁን ቅድሚያ ደህንነትን ማረጋገጥ፣ አገሪቱን ማረጋጋት ነዉ። ከዚያም አስተዳደርን መመስረትና ሌሎች ግንባር ቀደም ህዝቡ የሚፈልጋቸዉን ጉዳዮች ማከናወን ነዉ።»

ከተለያየ አቅጣጫ የተለያየ አስተያየት ይደመጣል ሶማሊያ ምድር የሚገኘዉን የኢትዮጵያ መንግስት ወታደራዊ ኃይል በሚመለከት። በሶማሊያ ምድር እሰመቼ ይሰነብታሉ የሚለዉ ደግሞ አነጋጋሪ ሆኗል። ቃል አቀባዩን ለመሆኑ ሰራዊቱ የተሰጠዉን ግዳጅ አጠናቆ መቼ ይእወጣል የሚለዉ ግን ቁርጥ ያለ መልስ አልተሰጠበትምና እሰመቼ ይቆያሉ አልኳቸዉ

«በቻለ ፍጥነት በቅርቡ ይወጣሉ። ከኢትዮጵያ ወንድሞቻችን ጋ ጥሩ ግንኙነት ነዉ ያለን። የሽግግር መንግስቱ ነዉ መጥተዉ እንዲረዱት የጋበዛቸዉ። የጀመሩት እኛን የመርዳት ተግባር እንዳለቀም ይወጣሉ። አገሪቱን ለመዉረር አይፈልጉም። የእናንም ሆነ የእነሱን አገር ሰላምና ሉዓላዊነት ለማረጋግጥ እዉነተኛ ፍላጊት ነዉ ያላቸዉ። ለዚህም ነዉ ወደሶማሊያ በመምታት ምድራዊ ገነት ለመፍጠር ያሰቡትን የፅንፈኞት መንፈስ ያላቸዉን ኃይላት ከአካባቢዉ ለማፅዳት የመጡት።»

በመጨረሻም ለመሆኑ እነሱ ከሶማሊያ ምድር ቢወጡ እናንተ የሚባለዉን ችግር ሁሉ በቁጥጥር ስር የማድረግ አቅሙ አላችሁ ስል ጠየኳቸዉ። ጌዲም

«አዎ እንችላለን። ምክንያቱም ወንዶቻችን ኢትዮጵያዊያን የእኛን ኃይሎች አሰልጥነዉልናል። እነዚያ የሰለጠኑት ደግሞ ከተማዉንም ሆነ ሌሎች አካባቢችን ተቆጣጥረዉ ይዘዋል። እነሱም በስልጠናና በምልመላ እየረዱን ነዉ። ዓለም ዓቀፍ ድጋፍም እንፈልጋለን። በተለይም ከአፍሪቃ ህብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል ወደሶማሊያ የሚገባበትን ቀን እየጠበቅን ነዉ። እነሱም በዚህ ያግዙናል። እኛም ከዚያ ከዚያ በኋላ መቆጠር እንችላለን፤ አቅሙም አለን። ባለፉት ፩፮ዓመታት በመንግስት ስልጣን ላይ ነበርን። ካድሬዎችና ሃላፊዎችም በየስፍራዉ አሉን። ሁኔታዉን በአግባቡ ለማከናወን ይረዱናል። ዓለም ዓቀፉ ህብረተሰብ ግን ይህን ለማድረግና መንግስታችንን ለመርዳት ተስኖታል። አሁንም እነሱ ቆየት ብለን እንየዉ በሚለዉ መስመር ዉስጥ ናቸዉ።»