1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ኅዳር 18 2004

በአውሮፓ የቀደምቱ የእግር ኳስ ሊጋዎች መደበኛ ሻምፒዮና በአስደናቂ ሁኔታ ቀጥሏል። ታንዛኒያ ውስጥ ደግሞ የምሥራቅና ማዕከላዊ አፍሪቃ የእግር ኳስ ዋንጫ ውድድር በመካሄድ ላይ ነው።

https://p.dw.com/p/Rz0f
ምስል dapd

በጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድር ያለፈው ወቅት ሻምፒዮን ዶርትሙንድና ግላድባህ በእኩል ነጥብ አመራሩን ሲይዙ ባየርን ሙንሺን በማይንስ በደረሰበት ሽንፈት ወደ ሶሥተኛው ቦታ አቆልቁሏል። በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ሻምፒዮኑ ባርሤሎና በጌታፌ ሲሸነፍ አትሌቲኮ ማድሪድን 4-1 የረታው ሬያል ማድሪድ አመራሩን ወደ ስድሥት ከፍ ሊያደርግ በቅቷል።
በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሁለቱ የማንቼስተር ከተማ ተፎካካሪዎች በየፊናቸው በእኩል ለእኩል ውጤት መወሰናቸው በአመራሩ ላይ የደረሰ ምንም ለውጥ የለም። ማንቼስተር ሢቲይ ማኒዩን በአምሥት ነጥቦች ልዩነት ይመራል። በኢጣሊያ ጁቬንቱስ በአመራሩ ሲቀጥል በፈረንሣይ ሞንትፔሊየር፣ በፖርቱጋል ፖርቶና በኔዘርላንድ አልክማር ቀደምቱ ናቸው።

በአፍሪቃ ላይ እናተኩርና ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው የምሥራቅና ማዕከላዊ አፍሪቃ የእግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ባለፈው አርብ ታንዛኒያ ውስጥ ተከፍቶ እየተካሄደ ነው። ኢትዮጵያም የውድድሩ ተሳታፊ ስትሆን የብሄራዊውን ቡድን ዝግጅት፣ ብቃትና ዕድል በተመለከተ የፌደሬሺኑን የግንኙነት ሃላፊ አቶ መላኩ አየለን ዛሬ አነጋግረናል።
ቴኒስ

Tennis French Open 2011 Roger Federer
ምስል dapd

በዓመቱ ማጠቃለያ የለንደን የዓለም የቴኒስ ውድድር ፍጻሜ ግጥሚያ ትናንት የስዊሱ ሮጀር ፌደረር ፈረንሣዊውን ጆ-ዊልፍሪድ-ሶንጋን በአራት ምድብ ጨዋታ 3-1 በማሸነፍ ማንም ላልደረሰበት ስድሥተኛ የኤቲፒ-ቱውር ድሉ በቅቷል። ዋነኛ ተፎካካሪዎቹ ኖቫክ ጆኮቪች፣ ራፋኤል ናዳልና ኤንዲይ መሪይ በዓመቱ መገባደጃ ወቅት ሲዳከሙ ፌደረር በአንጻሩ ውጣ ውረድ የበዛውን ዓመት የሚሰናበተው በደስታና በተሥፋ ነው።

Sebastian Vettel und Mark Webber in Sao Paulo Brasilien 2011 Formel 1
ምስል AP

የአውቶሞቢል እሽቅድድም

የፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል የዓለም ሻምፒዮናም ትናንት ብራዚል ውስጥ በተካሄደው በዓመቱ የመጨረሻ እሽቅድድም ተፈጽሟል። የዘንድሮው የዓለም ሻምፒዮን ጀርመናዊው ዜባስቲያን ፌትል ምንም እንኳ ከመጀመሪያው ተርታ ቢነሣም በእሽቅድድሙ ያሸነፈው የአውስትራሊያው ዘዋሪ ማርክ ዌበር ነው። ፌትል ሁለተኛ ሆኗል።

መሥፍን መኮንን
ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ