1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ሰኔ 27 2003

ጀርመን ውስጥ በመካሄድ ላይ ያለው የሴቶች የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ወደ ሩብ ፍጻሜው ሊሻገር እየተቃረበ ነው።

https://p.dw.com/p/RXZO
ምስል AP

በዚህ በጀርመን በመካሄድ ላይ ባለው በስድሥተኛው የሴቶች የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር የድል ባለቤት ለመሆን ይበቃሉ ተብለው ከሚጠበቁት ቀደምት አገሮች አንዷ ብራዚልም ወደ ሩብ ፍጻሜው ማለፉ በትናንቱ ምሽት ተሳክቶላታል። ብራዚል ኖርዌይን 3-0 ስትረታ ከሶሥቱ ሁለቱን ጎሎች ያስቆጠረችው በዓለም ድንቅ ተጫዋችነት በተደጋጋሚ የተሽለመችው የቡድኑ ኮከብ ማርታ ነበረች። የማርታ አጨዋወት በዕውነትም ቀደምት ኮከብነቷን መልሶ ያረጋገጠ ነበር።
ቀደም ሲል ባለፈው ሣምንት ሂደት ከምድብ-አንድ ፈረንሣይና ጀርመን፣ ከምድብ-ሁለት ጃፓንና እንግሊዝ፣ እንዲሁም ከምድብ ሶሥት ዩ.ኤስ.አሜሪካና ስዊድን ወደ ተከታዩ ዙር መሻገራቸውን ማረጋገጣቸው አይዘነጋም። በምድብ-አራት ውስጥ ትናንት በብራዚል በለየለት ሁኔታ የተረታችው ኖርዌይ ስምንተኛዋና የመጨረሻዋ ቡድን ሆና ወደ ሩብ ፍጻሜው ለማለፍ በፊታችን ረቡዕ ምሽት አውስትራሊያን የግድ ማሸነፍ ይኖርባታል። አውስትራሊያ በአንጻሩ ኤኩዋቶሪያል ጊኒን አሸንፋ ከኖርዌይ እኩል ነጥብ ስትይዝ የጎል ብልጫ ስላላት እኩል ለእኩል ውጤት ይበቃታል። ከጠንካሮቹ አገሮች አንዷ ሆና የምትቆጠረው ኖርዌይ እንግዲህ በመጀመሪያው የምድብ ዙር ከተሰናበተች ይሄው በእስካሁኑ የውድድሩ ሂደት ትልቁ ያልተጠበቀ ነገር ነው የሚሆነው።

በሌላ በኩል በምድብ-አንድ ፈረንሣይ ናይጄሪያን 1-0 እንዲሁም ካናዳን 4-0 በማሽነፍ ብርቱ ጥንካሬ ስታሳይ አስተናጋጇ ጀርመንም ምንም እንኳ ከናዳን 2-1 እና ናይ’ጄሪያንም 1-0 ብትረታም ለሶሥተኛ ጊዜ የዋንጫ ባለቤት ለመሆን ያላትን ፍላጎት የሚያንጸባርቅ ጥንካሬ እስካሁን አልታየባትም። ቡድኑ የተደናገጠና በራስ መተማመን ያጣ ነው የሚመስለው። በመሆኑም ነገ ከፈረንሣይ ጋር በሚያደርገው የምድብ ጨዋታ ተፎካካሪዎቹን ለማስደንገጥና መንፈሱን ለማጠናከር ሃያል ሆኖ መገኘት ይጠበቅበታል። ለነገሩ ተከላካይዋ ሊንዳ ብሬዞኒክ የምታምነውም እርግጥ ይሄው እንደሚሳካ ነው።

“ሁላችንም ጨዋታችንን ለማሻሻል እንፈልጋለን። እስካሁን ባሳየነው ጨዋታ አለመርካታችን ግልጽ ነገር ነው። እናም ይህን መለወጡን አሁን በፈረንሣይ እንጀምራለን። ፈረንሣዮች 4-0 ካሽነፉ በኋላ በወቅቱ በደስታ ወደ ሰማየ-ሰማያት ከንፈው ነው የሚገኙት። እናም ወደ ምድር እንመልሳቸዋለን ብንል ነውር አይመስለኝም’”
ለጀርመን በዚህም በዚያም ድሉ ትልቅ ትርጉም የሚኖረው ነው። አለበለዚያ ቡድኑ ገና በሩብ ፍጻሜው ወድቆ እንዳይቀር በጣሙን ነው የሚያሰጋው። የጀርመን እግር ኳስ ፌደሬሺን ፕሬዚደንት ቴዎ ስቫንሲገር በበኩላቸው ቡድኑን ከዚሁ ከሶሥተኛ ግጥሚያው በፊት በመጎብኘት ሊያበረታቱ ሞክረዋል። የሆነው ሆኖ የጀርመን ብሄራዊ ቡድን ተከላካይ ባቤት ፔተር ፈረንሣይን ማሸነፍ ቀላል ነገር እንደማይሆን ነው የምትናገረው።

“በከፍተኛ የቴክኒክ ደረጃ ነው እግር ኳስ የሚጫወቱት። ባለፉት ዓመታት ደግሞ በታክቲክ ረገድም ብዙ ትምሕርት ቀስመዋል። ስለዚህም ከነርሱ ጋር መጫወት በጣም ከባድ ነገር ነው። ለማሽነፍ ከተፈለገ ኋላ ጥቅጥቅ አድርጎ መዝጋትና ከፊት ደግሞ በብልህነት ማጥቃት ግድ ይሆናል”

ሁለቱ ቡድኖች የሚጫወቱት የምድባቸው አንደኛ ለመሆን ሲሆን ለዚሁ ታዲያ ጀርመን ማሸነፍ፤ ፈረንሣይ ግን በጎል ብልጫ የተነሣ እኩል ለእኩል ውጤት ይበቃታል። በተቀረ እስካሁን በአራቱ ቡድኖች ውስጥ በተካሄዱት ግጥሚያዎች ለምሳሌ ዩ.ኤስ.አሜሪካ ኮሎምቢያን 3-0፤ እንዲሁም ጃፓን ሜክሢኮን 4-0 በማሸነፍ ያሳዩት ጥንካሬ በሩብ ፍጻሜው ዙርም እንዲፈሩ የሚያደርጋቸው ነው። የምድቡ ዙር ከነገ በስቲያ ረቡዕ የሚጠቃለል ሲሆን አራቱ የሩብ ፍጻሜ ግጥሚያዎች በፊታችን ቅዳሜና ዕሑድ ይካሄዳሉ።

Copa America Finalespiel Brasilien - Argentinien 3:0 Robinho und Teamkameraden jubeln mit Flagge nach Sieg
ምስል AP

ኮፓ አሜሪካ

አርጄንቲና ውስጥ በመካሄድ ላይ ባለው የላቲን አሜሪካ እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር በኮፓ አሜሪካ ሰንበቱ ቀላል የሚባሉት ቡድኖች ታላላቆቹን የተፈታተኑበት ነበር። አስተናጋጇ አገር አርጄንቲና ባለፈው አርብ ከቦሊቪያ ጋር ባደረገችው ግጥሚያ ለዚያውም በመከራ 1-1 ስትለያይ የዋንጫው ባለቤት ብራዚልም በምድብ-ሁለት ከቬኔዙዌላ ጋር ባዶ-ለባዶ በሆነ ውጤት መወሰኑ ግድ ነው የሆነባት። የብራዚል ቡድን በመጀመሪያው አጋማሽ ብዙ ቢያጠቃም ግጥም አድርገው የዘጉት የቬኔዙዌላ ተከላካዮች የሚበገሩ አልሆኑም። እርግጥ ብራዚል አንድ የፍጹም ቅጣት ምት ተከልክላለች ለማለት ይቻላል። የሆነው ሆኖ ጅማሮው አልሰመረላትም፤ ለቬኔዙዌላ በአንጻሩ ውጤቱ የታላቅ ድልን ያህል ነው የሆነው።
በሌላው የምድብ-ሁለት ጨዋታ ኤኩዋዶርና ፓራጉዋይም እንዲሁ ባዶ-ለባዶ ተለያይተዋል። በምድብ-አንድ ኮሎምቢያ ኮስታሪካን 1-0 ስትረታ ባለፈው የዓለም ዋንጫ እስከ ግማሽ ፍጻሜ ደርሳ የነበረችው ኡሩጉዋይ ደግሞ ዛሬ ማምሻውን የምድብ-ሶሥትን ግጥሚያ ትከፍታለች። የተቀሩት የምድቡ ተጋጣሚዎች ቺሌና ፔሩ ናቸው። ወደ ሩብ ፍጻሜው የሚያልፉት የሶሥቱ ምድቦች አንደኛና ሁለተኛ አገሮች እንዲሁም ሌሎች ሁለት የተሻለ ነጥብ ያላቸው ሶሥተኛ ቡድኖች ይሆናሉ። በነገራችን ላይ ውድድሩ የሚካሄደው ብርቱ ቅዝቃዜ በሰፈነበት ሁኔታ ሲሆን እስካሁን በአራት ግጥሚያዎች ከሶሥት ጎሎች በላይ ማስቆጠር አልተቻለም። አዝማሚያው ከቀጠለ ብራዚልና አርጄንቲና ከጅምሩ ከስረው እንዳይቀሩ ምናልባትም የሚያሰጋቸው ነው።

በእሢያ ለመጪው የብራዚል የዓለም ዋንጫ በተካሄዱ የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ የመልስ ግጥሚያዎች ደግሞ ማሌይዚያ፣ በርማ፣ ባንጋዴሽ፣ ፊሊፒን፣ ቪየትናም፣ ፍልሥጤም፣ ኔፓልና ላኦስ ወደ ሁለተኛው ዙር ለማለፍ በቅተዋል። በሁለተኛው ዙር ወደፊት ከሚገናኙት መካከል ቻይና ከላኦስ፣ ሶሪያ ከታጂኪስታን፣ ታይላንድ ከፍልሥጤም፣ እንዲሁም ኢራቅ ከየመን ከብዙ ጥቂቶቹ ናቸው።

Tennis Wimbledon Djokovic Nadal
ምስል dapd

የኖቫክ ጆኮቪች ታሪካዊ ድል በዊምልደን

የሰርቢያው ተወላጅ ኖቫክ ጆኮቪች ትናንት በታላቁ የዊምብልደን ቴኒስ ፍጻሜ ታላቅ ተጋጣሚውን ራፋኤል ናዳልን ሁለት ሰዓት ተኩል በፈጀ ግሩም ጨዋታ በማሸነፍ ለመጀመሪያ ጊዜ የክቡሩ ዋንጫ ባለቤት ለመሆን በቅቷል። ጆኮቪች ለድል የበቃው በአራት ምድብ ጨዋታ 6-4, 6-1, 1-6, 6-3 በሆነ ውጤት፤ በጥቅሉ ሶሥት ለአንድ ካሽነፈ በኋላ ነው። በዚሁ በስፓኙ ራፋኤል ናዳልና በስዊዙ ሮጀር ፌደረር ለስምንት ዓመታት ያህል በሞኖፖል ተይዞ የቆየውን የለንደኑን የቴኒስ መድረክ ሊቆጣጠር በቅቷል። ለ 24 ዓመቱ ወጣት የሰርቢያ ኮከብ የትናንቱ ድል በዓለም የማዕረግ ተዋረድ ላይ ናዳልን በአንደኝነቱ ቦታ ለመተካት ያበቃም ነው የሆነው። ጆኮቪች በበኩሉ ለጋዜጠኞች እንደገለጸው ከሕጻንነት ጀምሮ የነበረው ምኞቱ ዕውን መሆኑን በቀላሉ ሊያምነው አልቻለም።

“ይህ የምወደውና የማልምለት ውድድር ነበር። እናም የሚሰማኝን መግለጽ ያስቸግረናል። በቀላሉ በቂ ቃላት አላገኝም። በሕይወቴ ታላቁ ቀን መሆኑን ከመናገር ሌላ ምንም ለማለት አልችልም”

ባለፈው ቅዳሜ የሴቶች ፍጻሜ ግጥሚያም የቼኳ ፔትራ ክቪቶቫ ሩሢያዊቱን ኮከብ ማሪያ ሻራፖቫን በለየለት 6-3, 6-4 ውጤት ስታሽንፍ ዓለም በጣሙን እንዲደነቅ ነው ያደረገችው። የቼኮች ድል በዚህ ብቻ አላበቃም። በሴቶች ጥንድ ፍጻሜም ክቬታ ፔሽከ ከስሎቬኒያ ተጣማሪዋ ከካቴሪና ስሬቦትኒክ ጋር በመሆን ለድል በቅታለች። በወንድ-ሴት ቅይጥ ጥንድ የፍጻሜ ድልም እንዲሁ የቼክ ዕጅ ነበረበት። ከአውስትሪያው ተወላጅ ከዩርገን ሜልሰር ጋር በመሆን ያሸነፈችው የቼኳ ኢቬታ ቤኔሶቫ ነበረች። ይህ የሰንበቱ ታሪካዊ ውጤት የቼክን ወጣት ቴኒስ ተጫዋቾች ስሜት ይበልጥ የሚያጠናክር ለመሆኑ አንድና ሁለት የለውም።

EM Leichtathletik in Spanien
ምስል AP

አትሌቲክስ
ባለፈው ሣምንት አጋማሽ ስዊትዘርላንድ-ሉዛን ላይ በተካሄደው የአትሌቲክስ ውድድር የጃሜይካው አሣፋ ፓውል የቀደምት ተፎካካሪዎቹን የዩሤይን ቦልትንና የታይሰን ጌይን አለመኖር በመጠቀም የዓመቱን ፈጣን የመቶ ሜትር ጊዜ ለማስመዝገብ በቅቷል። 9,78 ሤኮንድ ጊዜ ነው ያስመዘገበው። ሌላው ጃሜይካዊ ማይክል ፍራተር ሁለተኛ ሲሆን ሩጫውን በሶሥተኝነት’ የፈጸመው ፈረንሣዊው የአውሮፓ ሻምፒዮን ክሪስቶፍ ሌሜትር ነበር። በአራት መቶ ሜትርም ጃሜይካዊው ጀርሜይን ጎንዛሌስ ሲያሸንፍ በስምንት መቶ ሜትር ደግሞ ከአካል ጉዳቱ አገግሞ የተመለሰው የሁለት ጊዜ የዓለም ክብረ-ወሰን ባለቤት ኬንያዊው ዴቪድ ሩዲሻ አንደኛ ሆኗል።

በአምሥት ሺህ ሜትርም የኬንያው ቪንሤንት ቼፕኮፕ ቀዳሚ ሲሆን የኢትዮጵያው አትሌት ኢማነ መርጋ ሁለተኛ ወጥቷል። በዚሁ ሩጫ የኬንያና የኢትዮጵያ አትሌቶች ከአንድ እስከ ስምንት ሲከታተሉ ደጀን ገ/መስቀል አምሥተኛ፤ እንዲሁም ታሪኩ በቀለ ስምንተኛ ሆኗል። በአጭር ርቀት ሩጫ፣ በውርወራና ዝላይ እንደተለመደው የአሜሪካና የአው’ሮፓ አትሌቶች ግንባር ቀደም ሲሆኑ በሴቶች ሶሥት ሺህ ሜትር ሩጫ ኬንያዊቱ ሚካህ ቼይዋ ሶፊያ አሰፋን በሁለተኝነት በማስከተል ለድል በቅታለች። ብርቱካን ዓዳሙና ብርቱካን ዓለሙ ደግሞ አምሥተኛና ስድሥተኛ ሆነዋል። በተረፈ ትናንት ሩሢያ-ሱኮቭስኪይ ላይ በተካሄደ የአትሌቲክስ ውድድር በሴቶች አሥር ሺህ ሜትር ሩጫ የኢትዮጵያ ተወዳዳሪዎች ሱሌ ጌዶና ውዴ አያሌው አንደኛና ሁለተኛ በመሆን ድል ተጎናጽፈው ነበር።

ቡጢ/የቢስክሌት እሽቅድድም

ባለፈው ቅዳሜ ሌሊት በዚህ በጀርመን በሃምቡርግ ከተማ በኡክራኒያው የዓለም ሻምፒዮን በቭላዲሚር ክሊችኮና በእንግሊዛዊ ተጋጣሚው በዴቪድ ሄይ መካከል የተደረገው የዓለም ቡጢ ማሕበር WBA የከባድ ሚዛን ግጥሚያ በክሊችኮ የነጥብ ድል ተፈጽሟል። በዚሁ ታሪካዊ ድል የስድሥቱም የቡጢ ማሕበራት ሻምፒዮንነት የወንድሙ የቪታሊ ታክሎበት በሙሉ ከክሊችኮ ቤተሰብ ዕጅ መግባቱ ነው። በሌላ በኩል ቭላዲሚር ክሊችኮ በዚሁ ግጥሚያ ለ 50ኛ ጊዜ በመዘረር ለማሸነፍ የነበረው ውጥን ዕውን ሳይሆንለት ቀርቷል።

በፈረንሣዩ አገር-አቋራጭ የቢስክሌት እሽቅድድም ቱር-ዴ-ፍራንስ የስፓኙ ሻምፒዮን አልቤርቶ ኮንታዶር የሚወደው ተራራ የመውጣቱ ደረጃ እስከሚደርስ ከአመራሩ በነጥብ ብዙ እንዳይርቅ ለማድረግ እየሞከረ ነው። ከትናንቱ ሁለተኛ ደረጃ እሽቅድድም በኋላ የቤልጂጉ ፊሊፕ ጊልበርት በ 45 ነጥቦች የሚመራ ሲሆን የአውስትሪያው ካዴል ኤባንስና የኖርዌዩ ትሆር ሁስሆፍድ በ 35 እና 30 ነጥቦች ይከተሉታል። በዛሬው የሶሥተኛ ደረጃ የ 198 ኪሎሜትር እሽቅድድም ደግሞ እንግሊዛዊው ማርክ ካቬንዲሽ አይሎ እንደሚታይ እየተጠበቀ ነው።

መሥፍን መኮንን

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ