1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 24 2003

የጀርመን ቡንደስሊጋ የእግር ኳስ ውድድር ሊጠናቀቅ ገና ሁለት ግጥሚያዎች ቀርተውት ሳለ ቦሩሢያ ዶርትሙንድ ሰንበቱን ቀድሞ ሻምፒዮነቱን አረጋግጧል።

https://p.dw.com/p/RLSC
ምስል picture alliance/dpa

የ 2011 ዓ.ም. የጀርመን ሻምፒዮን ቦሩሢያ ዶርትሙንድ! በጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድር የዘንድሮው ሻምፒዮና ገና ሁለት ግጥሚያዎች ቀርተው ሳለ ከወዲሁ ለይቶለታል። ባለፈው ቅዳሜ ግጥሚያው ኑርንበርግን 2-0 በመርታት ለሰባተኛ የቡንደስሊጋ ውድድር ድሉ የበቃው ወጣቱ የቦሩሢያ ዶርትሙንድ ቡድን ነው። እርግጥ ሻምፒዮናው ከወዲሁ እንዲለይለት ኮሎኝም ሁለተኛውን ሌቨርኩዝንን በተመሳሳይ ውጤት በማሸነፍ አስተዋጽኦ ማድረጉ አልቀረም። ያም ሆኖ እጅጉን የሚያስደንቀው ማንም ያላሰበው ዶርትሙንድ ከጅምሩ አንስቶ አስደናቂ ጨዋታ በማሳየት ከመጨረሻ ግቡ ላይ መድረሱ ነው። በዚህ ታላቅ ስኬት አሠልጣኙ ዩርገን ክሎፕ ሳይቀር ጥቂትም ቢሆን መደነቁ አልቀረም።

“ስሜቱ ከጠበቅሁት የተለየ ነው። ከፈንጠዝያ ይልቅ እፎይታው ያመዝናል። ለማንኛውም ግን በቡድኑ በጣሙን ነው የምኮራው”

በ 80 ሺህ ተመልካች ፊት ሁለቱን ጎሎች ያስቆጠሩት ሉካስ ባሪዮስና ሮበርት ሌቫንዶቭስኪ ነበሩ። የመሃል ሜዳ ተጫዋቹን ኬቪን ግሮስክሮይስን የመሳሰሉት ወጣት ተጫዋቾች ክለቡ ቀድሞ ድሉን በማረጋገጡ በጣሙን ነው የተደነቁት። በረኛው ሮማን ቫይደንፌለር እንዳለው የጠበቀውም አልነበረም።

“ሻምፒዮናው በዛሬው ዕለት እንዲለይለት ለማድረግ መብቃታችን ልዩ ስሜትን የሚሰጥ ነገር ነው። መላው ዶርትሙንድና አካባቢው የተመኘው ነበር ብዬ አስባለሁ። እናም ይሄው ዛሬ ተሳክቶልናል”

በሁለተኝነት የሚከተለው ሌቨርኩዝን በበኩሉ ጨዋታ በኮሎኝ 2-0 ሲሽነፍ እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ ወሣኝ በሆኑ ግጥሚያዎች ላይ የተለመደው ድክመት እንደገና ታይቶበታል። ለቡድኑ ሻምፒዮንነቱ ካመለጠው አሁን የሚቀረው ዕድል ለመጪው የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር በቀጥታ ለማለፍ የሚያስችለውን ሁለተኛ ቦታውን ማስከበር ነው። ይህም አሁን ከሶሥተኛው ክለብ ባለው የአምሥት ነጥብ ብልጫ የሚሳካለት ይመስላል። የብዙ ጊዜው ሻምፒዮን ባየርን ሙንሺን ደግሞ በሃኖቨር መሸነፍ ወደ ሶሥተኛው ስፍራ ከፍ ሲል ይህንኑ ቦታውን በመጠበቅ ለአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ማጣሪያ የመድረስ ዕድል አለው። ሆኖም ባየርን በሰንበቱ ግጥሚያው ሻልከን በፍጹም የበላይነት 4-1 ይርታ እንጂ ጊዜያዊ አሠልጣኙ አንድሪስ ዮንከር የሶሥተኝነቱ ቦታ እ’ንዳይታጣ መስጋቱን አልሸሸገም።

“የሁለት ነጥብ ብልጫ ብቻ ነው ያለን። በዚህ የውድድር ወቅት ደግሞ ብዙ ጊዜ የነጥብ ብልጫችንን አሳልፈን መስጠታችን የሚታወቅ ነው። እናም ይህ እንዳይሆን ካልፈለግን ለመጪው ከሣንት ፓውሊ ጋር ለምናደርገው ግጥሚያ በሙሉ ትኩረት መጓዝ ይኖርብናል”

በቡንደስሊጋው ውድድር ከእንግዲህ በቀሩት ሁለት ሣምንታት ትኩረቱ ይበልጡን የሚያመዝነው ከአንደኛው ዲቪዚዮን ወደታች ላለመከለስ በስድሥት ክለቦች መካከል በሚደረገው የጦፈ ፉክክር ነው። ከ 12 እስከ መውረጃው 16ኛ ቦታ ባሉት ክለቦች መካከል የነጥቡ ልዩነት አምሥት ብቻ ሲሆን የመጨረሻው ሣንት ፓውሊ ከወዲሁ ያለቀለት ይመስላል። ሌሎቹ ላለመውረድ የሚታገሉት ቡድኖች ሽቱትጋርት፣ ብሬመን፣ ኮሎኝ፣ ቮልፍስቡርግ፣ ፍራንክፉርትና ግላድባህ ናቸው። በሌላ በኩል በሁለተኛው ዲቪዚዮን በርሊን ባለፈው ሣምንት ወደ ከፍተኛው ቡንደስሊጋ መመለሱን ቀድሞ ማረጋገጡ አይዘነጋም።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሻምፒዮናው ወደ ማንቼስተር ዩናይትድ ያጋደለ መስሎ ከቆየ በኋላ በመጨረሻዋ ሰዓት ግን የሁለት ክለቦች ፉክክር የሚታይበት እየሆነ ነው። ማንቼስተር ዩናይትድ በአርሰናል 1-0 ሲረታ አመራሩ ወደ ሶሥት ነጥቦች ብቻ ሊጠብ ችሏል። ውጤቱ የጠቀመው ቶተንሃም ሆትስፐርን ሣሙዔል ካሉ በ 89ኛዋ ደቂቃ ላይ ባስቆጠራት ወሣኝ ግብ 2-1 ላሸነፈው ለቼልሢይ ነው። የፕሬሚየር ሊጉ ውድድር ሊጠናቀቅ የቀሩት ሶሥት ግጥሚያዎች ብቻ ናቸው። አርሰናል ከሁለተኛው ከቼልሢይ ስድሥት ነጥቦች ወረድ ብሎ ሶሥተኛ ሲሆን ማንቼስተር ሢቲይ ደግሞ በአራተኝነት ይከተላል።

በስፓኝ ላ-ሊጋ ሁለቱም ቀደምት ክለቦች ባርሤሎናና ሬያል ማድሪድ በመሸነፋቸው በአመራሩ ላይ የተከተለ ለውጥ የለም። ሬያል ማድሪድ በገዛ ሜዳው በሣራጎሣ 3-2 ሲረታ ባርሤሎናም በሬያል ሶሢየዳድ 2-1 ተሸንፏል። ሁለቱም ቡድኖች ካለፈው ማክሰኞ የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ግማሽ ፍጻሜ ግጥሚያ ድክመታቸው ያገገሙ መስለው አልታዩም። በአጠቃላይ ባርሣ በስምንት ነጥቦች ብልጫ መምራቱን ሲቀጥል አራት ግጥሚያዎች ቀርተው ሳለ ለሻምፒዮንነቱ ጥሩ ዕድል ያለው ነው የሚመስለው።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ውድድሩ ሊጠቃለል ሶሥት ግጥሚያዎች ቀርተው ሳለ ቦሎኛን 1-0 ያሽነፈው በስምንት ነጥቦች የሚመራው ኤ.ሢ.ሚላን ሻምፒዮን ለመሆን አንዲት ነጥብ ብቻ ትበቃዋለች። ሁለተኛው ቼሤናን 2-1 ያሸነፈው ኢንተር ሚላን ሲሆን ጌኖዋን 1-0 የረታው ናፖሊ አንዲት ነጥብ ዝቅ ብሎ ይከተለዋል። በፈረንሣይ ሻምፒዮና አምሥት ግጥሚያዎች ቀርተው ሳለ ሊል የተከለሰውን አርልስ-አቪኞንን 5-0 በመሽኘት አመራሩን መልሶ ይዟል። ሆኖም ኦላምፒክ ማርሤይ አንዲት ነጥብ ብቻ ዝቅ ብሎ የሚከተለው ሲሆን ፉክክሩ እንደጦፈ ቀጣይ ነው። በኔዘርላንድ ሻምፒዮናም የዘንድሮው ውድድር በአንዲት ነጥብ ልዩነት በመከታተል አመራሩን በያዙት በኤንሼዴና በአያክስ አምስተርዳም ቀጥተኛ ግጥሚያ በመጨረሻው ቀን ይለይለታል።

Spanien Fußball Champions League Real Madrid gegen FC Barcelona
ምስል dapd

የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ

ያለፈው ሣምንት አጋማሽ ደግሞ በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ግማሽ ፍጻሜ የመጀመሪያ ጨዋታዎች በተለይም በባርሤሎናና በሬያል ማድሪድ ግጥሚያ የስነ ምግባር ጉድለት የታየበት ሆኖ ነው ያለፈው። ባርሣ እርግጥ ድንቅ ተጫዋቹ የአርጄንቲናው ኮከብ ሊዮኔል ሜሢ ባስቆጠራቸው ሁለት ጎሎች ሲያሸንፍ ከሬያል በኩል ግን ከጅምሩ አንስቶ የታየው ሁሉ ከስፖርት የሚጻረር ነበር። ሬያል ማድሪድ ለዚያውም በገዛ ሜዳው ከባድ ተጋጣሚውን ለመግታት የመረጠው በመከላከል፣ በመራገጥና በትንኮሣ ዘዴ ነው። የሬያሉ አርቤሎዋ ሆን ብሎ የባርሣን ተቀያሪ በረኛ ሆሴ ፒንቶን በመልከፍ በጨዋታው አጋማሽ ቀይ ካርድ ሲያሰጥ ፒንቶ ደግሞ ዳኒ አልቬስን አስከፊ በሆነ መንገድ በመርገጥ በ 61ኛው ደቂቃ ከሜዳ ይሰናበታል።
ከዚያ ሁለት ደቂቃ አልቆየም አሠልጣኙ ሆሴ ሞሪኞም በብልግናው ወደ ትሪቡን ይሸኛል። ሬያል ማድሪድ በጨዋታ የማይችለውን በዚህ የትንኮሣ ዘዴ ለማግኘት መሞከሩ በጣሙን የሚያሳፍር ነው። የፖርቱጋሉ ተወላጅ ሞሪኞ በተለይም ባርሤሎናን የመሰለ ታላቅ ክለብ የሚደላለት አድርጎ በማቅረቡና በመዝለፉ ከባድ ቅጣት ነው የሚጠብቀው። ሁለቱ ቡድኖች ነገ በባርሣ ኖው-ካምፕ ስታዲዮም በመልሱ ግጥሚያ እንደገና የሚገናኙ ሲሆን የባርሣ ለፍጻሜ የማለፍ ዕድል ከፍተኛ ነው። በማግሥቱ ረቡዕም ማንቼስተር ዩናይትድ የጀርመን ተጋጣሚውን ሻልከን ያስተናግዳል። ማኒዩ በመጀመሪያው ግጥሚያ ሻልከን 2-0 ሲያሸንፍ ዘንድሮ በዚያው በእንግሊዝ በዌምብሌይ ስታዲዮም ለሚደረገው ፍጻሜ ግጥሚያ መድረሱን የሚጠራጠር የለም። የጀርመኑ ክለብ በአብዛኛው ተበልጦ መሸነፉን አሠልጣኙ ራልፍ ራንግኒክ ጭምር አምኖ የተቀበለው ጉዳይ ነው።

“በመጀመሪያው ሩብ ሰዓት ውስጥ ጥሩ ስንጫወት በተሳካ ሁኔታ ለማጥቃት አንዳንድ ዕድል ማግኘታችንም አልቀረም። ግን ጊዜው እየገፋ ሲሄድ ሂደታችን የኋልዮሽ ብቻ ነበር። ታዲያ ማኒዩ ደግሞ በያንዳንዷ ባገኛት የጎል ዕድል ሊበረታታና በራስ መተማመንን ሊያዳብር በቅቷል”

ያም ሆነ ይህ በጥቅሉ ሲታይ የዘንድሮው የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ የፍጻሜ ተጋጣሚዎች ማንቼስተር ዩናይትድና ባርሤሎና የሚሆኑ ነው የሚመስለው።

አፍሪቃ ውስጥ ደግሞ ለያዝነው 2011 ዓ.ም. የመላው አፍሪቃ የእግር ኳስ ጨዋታ የመጨረሻ ማጣሪያ ዙር ለማለፍ ሰንበቱን በርካታ ሁለተኛ ዙር ግጥሚያዎች ተካሂደው ነበር። በነዚሁ ግጥሚያዎች ናይጄሪያና ደቡብ አፍሪቃ ወደ መጨረሻው ማጣሪያ ዙር ሲሻገሩ ጊኒ ቢሣውና ኡጋንዳም ባልተጠበቀ ስኬት ታዛቢዎችን አስደንቀዋል። የናይጄሪያ ድንቅ ቡድን ላይቤሪያን ከኋላ ተነስቶ 6-1 ሲያሰናብት ካለፈው መጋቢት ወር ወዲህ ባደረጋቸው አራት ግጥሚያዎች 16 ጎሎች ማስቆጠሩ ነው። ከጎል አግቢዎቹ መካከልም ለኢጣሊያው ቀደምት ክለብ ለኤ.ሢ.ሚላን የሚጫወተው ናማዲ ኦዱዋማዲ ይገኝበታል። ደቡብ አፍሪቃ ምንም እንኳ በውጭ በማላዊ 2-1 ብትረታም በአጠቃላይ 5-3 ውጤት ለማለፍ በቅታለች።

አፍሪቃ ውስጥ በእግር ኳስ ደካማ ከሚባሉት አገሮች አንዷ ጊኒ ቢሣው ከሤኔጋል 2-2 በመውጣት ወደ ተከታዩ ዙር ለማለፍ መቻሏም በጣሙን አስደናቂ ነው። በተጨማሪ ዴሞክራቲክ ሬፑብሊክ ኮንጎና ጋቦን በመጀመሪያ ግጥሚያቸው 2-1 ሲለያዩ የመልሱ ጨዋታ ኪንሻሣ ላይ ይካሄዳል። በመጀመሪያ ግጥሚያቸው 2-2 የተለያዩት ዚምባብዌና ቦትሱዋና ደግሞ ሃራሬ ላይ ይገናኛሉ። ኤርትራም በመጀመሪያ ግጥሚያዋ ኬንያን ባልተጠበቀ ውጤት 4-1 ስትረታ ናይሮቢ ላይ በሚካሄደው የመልስ ግጥሚያ ወደተከታዩ ዞር ለመሻገር ትልቅ ዕድል ነው ያላት። እግር ኳስና አትሌቲክስ ዓበይቱ ለሚሆኑበት ለፊታችን መስከረም ወር የሞዛምቢክ የመላው አፍሪቃ ጨዋታ ለመድረስ በሚደረገው የመጨረሻ ማጣሪያ ናይጄሪያ ከጋና የምትገናኝ ሲሆን ደቡብ አፍሪቃ ከዚምባብዌ ወይም ከቦትሱዋና፤ ጊኒ ቢሣው ከጊኒ፤ እንዲሁም ኡጋንዳ ከኤርትራ ይገናኛሉ።

Caroline Wozniacki Tennis Dänemark U.S. Open Flash-Galerie
ምስል AP

ዓለምአቀፍ ቴኒስ

በስፓኝ የማድሪድ ዓለምአቀፍ የቴኒስ ውድድር በሴቶች ከቀደምቱ መካከል አብዛኞቹ የመጀመሪያ ግጥሚያቸውን በስኬት ተወጥተዋል። የዓለም አንደኛ የሆነችው የዴንማርኳ ካሮሊን ቮዝኒያችኪ ጃፓናዊቱን አዩሚ ሞሪታን ስታሸንፍ መሰሎቿ ማሪያ ሻራፖቫ፣ ፍራንቼስካ ሺያቮኔና የለና ያንኮቪችም ወደ ሁለተኛው ዙር አልፈዋል። በወንዶች ወደፊት ከተሻገሩት መካከል ሁዋን ሞናኮ፣ ጆ ትሶንጋ፣ ሣንቲያጎ ዢራልዶና ጂላርሞ ሎፔዝ ይገኙበታል። በፖርቱጋል የኤስቶሪል ፍጻሜ ግጥሚያ ደግሞ አርጄንቲናዊው ሁዋን ዴል ፖትሮ በስፓኝ ተጋጣሚው በፌርናንዶ ቫርዳስኮ ላይ ባለድል ሆኗል። ዴል ፖትሮ ለፍጻሜ ድል ሲበቃ በጠቅላላው ለዘጠነኛ ጊዜ መሆኑ ነው። በቤልግሬድ-ኦፕን ደግሞ በዓለም የማዕረግ ተዋረድ ላይ ሁለተኛ የሆነው የሰርቢያው ተወላጅ ኖቫክ ጆኮቪች የስፓኝ ተጋጣሚውን ፌሊቺያኖ ሎፔዝን አሸንፏል። የ 23 ዓመቱ ወጣት እስካሁን በተከታታይ ለ 27ኛ ጊዜ አንድም ሽንፈት አልገጠመውም። በያዝነው ዓመት እስካሁን ለአምሥተኛ የፍጻሜ ድል በቅቷል።

መሥፍን መኮንን