1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ኅዳር 27 2003

ያለፈው ሣምንት የዓለም እግር ኳስ ፌደሬሺኖች ማሕበር ፊፋ ለመጀመሪያ ጊዜ የሁለት የዓለም ዋንጫ ውድድሮች አዘጋጅ ሃገራትን መርጦ የሰየመበት ነበር።

https://p.dw.com/p/QQmq
ምስል AP

በተለይም ካታር እ,ጎ.አ. የ 2022 ዓ.ም. አዘጋጅ ሆና መመረጧ ብዙዎችን ማስገረሙና ማስቆጣቱ አልቀረም። ይህ ዛሬ ታንዛኒያ ውስጥ እየተካሄደ ካለው ኢትዮጵያም ከምትገኝበት የማዕከላዊ-ምሥራቅ አፍሪቃ ዋንጫና የሣምንቱ የአውሮፓ ሊጋዎች ውድድር ጋር ዓቢይ ትኩረት ይሰጠዋል።

የማዕከላዊና ምሥራቅ አፍሪቃ ዋንጫ

ታንዛኒያ ውስጥ በመካሄድ ላይ ባለው የማዕከላዊና ምሥራቅ አፍሪቃ የእግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ኢትዮጵያም ሰንበቱን ወደ ሩብ ፍጻሜው ለማለፍ ችላለች። በሶሥት ምድቦች ተከፍሎ በተካሄደው ቀዳሚ ዙር ውድድር የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በመጀመሪያ በኡጋንዳ 2-1 ቢሽነፍም ቀጥሎ ኬንያን 2-1 በመርታትና ከማላዊ ጋር ደግሞ 1-1 በመለያየት በሶሥተኝነት ለጥቂት ነው ያለፈው። ቡድኑ ነገ ከምድብ-አንድ አሸናፊ ከዛምቢያ የሚገናኝ ሲሆን እጅግ ከባድ ፈተና ይጠብቀዋል።
ብሄራዊው ቡድን ለመሆኑ በምን ሁኔታ ላይ ነው የሚገኘው? ዛምቢያን የመሰለ ጠንካራ ተጋጣሚ ሊቋቋምስ ይችላል ወይ? በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሺን የግንኙነት ሃላፊ የሆኑትን አቶ መላኩ አየለን አነጋግረናል፤ ቃለ ምልልሱን ያድምጡ! በተረፈ የተቀሩት የሩብ ፍጻሜ ተጋጣሚዎች ነገ አይቮሪ ኮስትና ማላዊ፤ በማግሥቱ ደግሞ ኡጋንዳ ከዛንዚባር፤ እንዲሁም ታንዛኒያ ከሩዋንዳ ናቸው።

Flash-Galerie Fussball 1. Bundesliga 15. Spieltag 1. FC Nuremberg-Borussia Dortmund
ምስል dapd

የአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች ውድድር

ወደ አውሮፓው ቀደምት ሊጋዎች የእግር ኳስ ሻምፒዮና እንሻገርና በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የለንደኑ ክለብ አርሰናል ፉልሃምን 2-1 በማሸነፍ ለመጀመሪያ ጊዜ አመራሩን ሊይዝ በቅቷል። አርሰናል አንደኝነቱን እንዲይዝ ይበልጡን የጠቀመው የከተማ ተፎካካሪው የቼልሢይ ከኤቨርተን አቻ ለአቻ 1-1 መለያየት ነው። አርሰናል ከ 16 ግጥሚያዎች በኋላ 32 ነጥቦችን ይዞ ሲመራ ማንቼስተር ዩናይትድ ሰንበቱን ከብላክፑል ባለመጋጠሙ አንድ ጨዋታ ጎሎት በአንዲት ነጥብ ልዩነት በሁለተኝነት ይከተላል።
ባለፉት ሣምንታት ብዙም ያልቀናው ቼልሢይ በሰላሣ ነጥቦች ሶሥተኛ ሲሆን በ 29 ነጥቦች አራተኛው ደግሞ ማስቼስተር ሢቲይ ነው። አራቱም ክለቦች እጅግ የተቀራረቡ በመሆናቸው በፕሬሚየር ሊጉ ሻምፒዮና ብርቱ ተፎካካሪ ሆነው ይቀጥላሉ።

በጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድር የዘንድሮው አስደናቂ ክለብ ቦሩሢያ ዶርትሙንድ ሁለተኛውን ማይንስን በአሥር ነጥቦች ልዩነት በማስከተል የበልጉ ወራት፤ ማለት የመጀመሪያው ዙር ሻምፒዮን መሆኑን ገና ሁለት ግጥሚያዎች ቀርተው ከወዲሁ አረጋግጧል። ዶርትሙንድ ትናንት ኑርንበርግን 2-0 ሲረታ እስካሁን ከ 15 ግጥሚያዎቹ 13ቱን ማሽነፉ ነው። በሌላ በኩል ታላቁ ባየርን ሙንሺን በሻልከ 2-0 ተሸንፎ ከአምሥተኛው ወደ ሰባተኛው ቦታ በማቆልቆል ሻምፒዮን የመሆን ተሥፋውን ሲቀብር ለሻልከ በአንጻሩ ድሉ ከወደቀበት አዘቅት ለመውጣት የሚያበረታታ የወደፊት ዕርምጃ መሆኑ አልቀረም። አሠልጣኙ ፌሊክስ ማጋትም በቡድኑ ጥንካሬ አድናቆቱን ነው የገለጸው።

“በመጀመሪያው አጋማሽ ላይ በማጥቃቱ ረገድ ጥቂትም ቢሆን ለዘብ ያልን ነበር። ግን 1-0 ከመራን በኋላ ሁኔታችን ፍጹም ይለወጣል። ከዚያ በኋላ ጨዋታውን በሚገባ ነው የተቆጣጠርነው። በመጨረሻም ግጥሚያውን በሚገባ ነው ያሸነፍነው ለማለት እወዳለሁ”

ከሰንበቱ የቡንደስሊጋ ግጥሚያዎች በኋላ ኮሎኝን 3-2 ያሸነፈው ሌቨርኩዝንም ሶሥተኝነቱን ሲይዝ ሃኖቨር አራተኛ ነው። ሽቱትጋርት፤ ኮሎኝና መንሸን ግላድባህ ደግሞ ሁሉም በመሽነፍ የመጨረሻዎቹን ቦታዎች እንደያዙ ናቸው።

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ላ-ሊጋ ሊዮኔል ሜሢና ክሪስቲያኖ ሮናልዶ በጎል አግቢነት ፉክክራቸው በመቀጠል ክለቦቻቸውን በየፊናቸው ለድል አብቅተዋል። ባርሣ ኦሣሱናን 3-0 ሲረታ ሁለቱን ሎሎች ያስቆጠረው ሜሢ ነበር። ሬያል ማድሪድ ደግሞ በክሪስቲያኖ ሮናልዶ ግቦች ቫሌንሢያን 2-0 አሸንፏል። ከሣምንቱ ግጥሚያዎች በኋላ ባርሤሎና በ 37 ነጥቦች ይመራል፤ ሬያል ሁለት ነጥቦች ወረድ ብሎ ሁለተኛ ነው። ሶሥተኛ ቪላርሬያል!

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ኤ.ሢ.ሚላን ብሬሺያን 3-0 በመርታት በሶሥት ነጥቦች ልዩነት መምራቱን ሲቀጥል ላሢዮ ደግሞ ኢንተር ሚላንን 3-1 በመርታት ሁለተኛ እንደሆነ ነው። ያለፉት ዓመታት ሻምፒዮን ኢንተር በአንጻሩ ወደ ስድሥተኛው ቦታ አቆልቁሏል። በፈረንሣይ ሊጋ ሊል ሎሪየንትን 6-2 በመቅጣት አመራሩን ሲይዝ ሁለተኛው ፓሪስ-ሣን-ዠርማን ነው። በኔዘርላንድ አንደኛ ዲቪዚዮን አይንድሆፈን ኤንሼዴን በጎል ብልጫ አስከትሎ በአንደኝነት ሲመራ በፖርቱጋል ሻምፒዮና ደግሞ ፖርቶ ቀደምቱ እንደሆነ ቀጥሏል።

ያለፈው ሣምንት የዓለም እግር ኳስ ፌደሬሺኖች ማሕበር ፊፋ ለሁለት ተከታታይ የዓለም ዋንጫ ውድድሮች አዘጋጆችን የመረጠበትም ነበር። ሩሢያ ከመጪው የብራዚል የዓለም ዋንጫ ቀጥላ እ.ጎ.አ. የ 2018-ን ውድድር እንድታዘጋጅ መመረጧ በተወሰነም ደረጃ ቢሆን የተጠበቀ ቢሆንም የካታር ግን ያለመው አልነበረም። የሆነው ሆኖ በ 2022 የዓለም ዋንጫ ውድድር በመካከለኛው ምሥራቅ የሚካሄድ መሆኑን የፊፋ ፕሬዚደንት ሤፕ ብላተር ባስተዋወቁበት ጊዜ የአረቡ ዓለም በታላቅ ደስታ ነበር የተዋጠው።

ሩሢያ በበኩሏ እስካሁን የዓለም ዋንጫ ውድድር አዘጋጅታ ባታውቅም በጊዜው ግሩም መስተንግዶ እንደምታደርግ ቢቀር ቭላዲሚር ፑቲን በምርጫው ወቅት ቃል ገብተዋል።

“በውሣኔያችሁ ክብር ይሰማናል። ለዚህም ከልቤ አመሰግናለሁ። እግር ኳስ በሰውልጅ ሕይወት ውስጥ ወጣት ይሁን አንጋፋ ብርሃንን የሚፈነጥቅ ነው። ሩሢያ ውስጥ በ 2018 የሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ውድድር ከፍተኛ ደረጃን የጠበቀ ሆኖ እንደሚዘጋጅ ቃሌን እሰጣለሁ”

በሌሎች የስፖርት ውድድሮች ላይ እናተኩርና ጃፓን-ፉኩኦካ ላይ ትናንት በተካሄደ የማራቶን ውድድር የሞሮኮው የሁለት ጊዜ የዓለም ሻምፖዮን ጃዋድ ጋሪብ አሸናፊ ሆኗል። የሩሢያው ዲሚትሪ ሣፍሮኖቭ ሁለተኛ ሲወጣ እስከ ሰላሣ ኪሎሜትር ርቀት ድረስ ከቀደምቶቹ አንዱ የነበረው ተከስተ ከበደ ደግሞ በመጨረሻ ሰባተኛ ሆኗል። ሌላው የአትሌቲክስ ዜና የሊቱዋኒያው የአውሮፓ የማራቶን ሻምፒዮን ሲቪሌ ባልቹናይቴ አጎልባች መድሃኒት ወስዷል በሚል ከቀረበበት ክስ ነጻ መሆኑ ነው። የአገሪቱ ብሄራዊ የአትሌቲክ ፌደሬሺን እንዳስታወቀው በጉዳዩ ክሱን የሚያጠናክር በቂ መረጃ ለማግኘት አልተቻለም።

ዘገባችን ለማጠቃለል በቴኒስ ዴቪስ-ካፕ ሰርቢያ ፈረንሣይን ትናንት 3-1 በማሸነፍ ለመጀመሪያ ድሏ ስትበቃ በብራዚል እግር ኳስ ውድድር ደግሞ ፍሉሚኔዘ ለሁለተኛ ጊዜ የአገሪቱ ሻምፒዮን ለመሆን ችሏል።

መሥፍን መኮንን
ነጋሽ መሐመድ