1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ሰኔ 14 2002

ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ የሚካሄደው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ዛሬ 11ኛ ቀኑን ሲይዝ አርጄንቲና፣ ኔዘርላንድና ብራዚል ወደ ተከታዩ ዙር ማለፋቸውን ከወዲሁ አረጋግጠዋል።

https://p.dw.com/p/NzIb
ምስል picture alliance / dpa

በሌላ በኩል ታላላቅ የሚባሉት ፈረንሣይ፣ ያለፈው ውድድር የዋንጫ ባለቤት ኢጣሊያ፣ ስፓኝና ምናልባትም ጀርመን ገና በመጀመሪያው የምድብ ዙር ስንብት እንዳያደርጉ እያሰጋቸው ነው። የላቲን አሜሪካ አገሮች በአንጻሩ እስካሁን ከተጠበቀው በላይ ጠንክረው ሲታዩ ትልቁ ድክመት የሚታይባቸው የአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም ተጠሪዎች ናቸው።

በወቅቱ ከስምንቱ ምድቦች አራቱን የላቲን አሜሪካ ቡድኖች መምራታቸው በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ውድድር ላይ እስካሁን የደቡብ አሜሪካ እግር ኳስ ጠንካራ ሆኖ ለመገኘቱ ምልክት ነው። በምድብ-አንድ ውስጥ ከ 80 ዓመታት በፊት የመጀመሪያው የዓለም ወንጫ ውድድር አዘጋጅና ባለድል የነበረችው ኡሩጉዋይ ከፈረንሣይ ባዶ-ለባዶ ከተለያየች በኋላ አስተናጋጇን ደቡብ አፍሪቃን 3-0 በማሽነፍ በአራት ነጥብ ትመራለች። በዓለም ዋንጫው መክፈቻ ግጥሚያ ከደቡብ አፍሪቃ 1-1 የተላያየችው ሜክሢኮም ፈረንሣይን አሸንፋ እንደ ኡሩጉዋይ ሁሉ አራት ነጥቦች ሲኖሯት እነዚሁ ሁለት የላቲን አሜሪካ ተጠሪዎች ነገ እርስበርስ ይገናኛሉ።

ከምድብ-አንድ በአሁኑ ሁኔታ እነዚሁ ሁለት ቡድኖች ወደ ተከታዩ ዙር የሚሻገሩ ነው የሚመስለው። ለአስተናጋጇ ደቡብ አፍሪቃ በመጀመሪያው የምድብ ዙር ተወስኖ መቅረቱ እጅግ የሚያሳዝን ሲሆን ለፈረንሣይ ደግሞ በደካማ አቀራረብ ከወዲሁ መሰናበቱ የውርደትን ያህል ነው። ደቡብ አፍሪቃ በነገው ወሣኝ ግጥሚያ ቀላል ነገር አይጠብቃትም። ቢሆንም የቡድኑ አምበል አሮን ማኬና በራስ መተማመን ለስኬት ቁልፍ ሊሆን ይችላል።

“በራሳችን ማመን አለብን። ምናልባትም ከፈረንሣይ ጋር በምናደርገው ግጥሚያ እንደገና ተመልሰን ይህን በራስ መተማመን ማሳየቱ ይሳካልን ይሆናል። ገና አንድ ጨዋታ አለን። ምርጫው ይህን ዕምነት መከተል ብቻ ነው”

ምድብ-ሁለት የአርጄንቲና ልዕልና የሰመረበት ሲሆን በቀድሞው ድንቅ ተጫዋች በዲየጎ ማራዶና የሚሰለጥነው ቡድን እስካሁን ሁለቱንም ግጥሚያዎቹን አሸንፎ ነገ ከግሪክ ጋር ለሚያካሂደው ሶሥተኛ ጨዋታ እየተዘጋጀ ነው። ቡድኑ እስካሁን ናይጄሪያን 1-0፤ ከዚያም ደቡብ ኮሪያን 4-1 ሲያሸንፍ ብዙ ታዛቢዎች ለዋንጫ ባለቤትነት የቀረበው ነው ማለት ይዘዋል። በዕውነትም የአርጄንቲና ብሄራዊ ቡድን ጥንካሬ እጅግ ጎልቶ የሚታይ ነገር ነው። ናይጄሪያ በዚህ ምድብ ውስጥ በዜሮ ነጥብ አራተኛ ስትሆን ወደፊት ለመዝለቅ ግሪክ በአርጄንቲና ተሸንፋ እርሷ ደግሞ ደቡብ ኮሪያን ቢቀር በሁለት ጎሎች ልዩነት መርታት ይኖርባታል። ዕድሏ እጅግ የጠበበ ነው የሚመስለው።
በምድብ-ሶሥት ውስጥ እንግሊዝ ከዩ.ኤስ.አሜሪካና ከአልጄሪያ እኩል ለእኩል በሆነ ውጤት ከመወሰኗ ባሻገር በአጨዋወት ድክመቷም ብዙዎችን አሳዝናለች። ምድቡን በአራት ነጥቦች የምትመራው ማንም ያልጠበቃት ስሎቬኒያ ስትሆን አሜሪካና እንግሊዝ እያንዳንዳቸው ሁለት ነጥቦች ይዘው ይከተላሉ፤ አልጄሪያ ደግሞ በአንዲት ነጥብ የመጨረሻዋ ናት። እንግሊዝ ከነገ በስቲያ ከስሎቬኒያ በምታደርገው ግጥሚያ ካሽነፈች የማታ ማታ ራሷን አዳነች ማለት ነው። በተረፈ የአሜሪካና የአልጄሪያ ዕድልም ገና ጨርሶ አላከተመም።

በምድብ-አራት ጀርመን ከሣምንት በፊት በመክፈቻ ግጥሚያዋ አውስትራሊያን 4-0 ስትረታ ሃያል በመባል ነበር ከያቅጣጫው አድናቆትን ያተረፈችው። ሆኖም ጀርመን በሁለተኛ ግጥሚያዋ በሰርቢያ 1-0 ስትረታ አሁን ምድቡን በአራት ነጥቦች የምትመራው ጋና ናት። ጀርመንና ሰርቢያ በእኩል ሶሥት ነጥብ ሁለተኛና ሶስተኛ ሲሆኑ ጀርመን ከነገ በስቲያ ከጋና የምታደርገው ግጥሚያ ዕጣዋን የሚወስን የፍጻሜን ያህል ነው። የጋና ለቁንጮነት መብቃት በአገሪቱ ብሄራዊ ቡድን ደጋፊዎች ዘንድ ታላቅ ስሜትን ነው የቀሰቀሰው።
“እግር ኳስ አወዳለሁ። እኔም ራሴ ተጫዋች ነበርኩ፤ ምንም እንኳ ለታላቅ ቡድን ለመሰለፍ ባልበቃም። ግን ጋናን እወዳለሁ። እናም ፍላጎቴ እንድናሸንፍ ነው”

ለጀርመን ተጫዋቾች ሁኔታው ከባድ ቢሆንም አሠልጣኙ ዮአኺም ሉቭ ቡድኑ ወደ ተከታዩ ዙር እንደሚያልፍ እርግጠኛ ነኝ ባይ ነው።

“እንደማስበው አሁን በዚህ ሰዓት አንገታችንን መድፋት የለብንም። ይልቁንም በልዩ ትኩረት መዘጋጀት ነው የሚገባን። ለተከታዩ ዙር ለመድረስ ዕድሉ በዕጃችን ነው። እንደርሳለንም”

ጋና ወደ ተከታዩ ዙር ለማለፍ እኩል-ለእኩል ውጤትም ይበቃታል። በአንዲት ነጥብ ብቻ አራተኛ የሆነችው አውስትራሊያ ደግሞ ዕድል የሚኖራት ጀርመን በጋና ተረትታ ከሰርቢያ ጋር የምታደርገውን የራሷን ግጥሚያ በስድሥት ጎሎች ልዩነት ማሽነፍ ከቻለች ነው። ሆኖም ይህ ሊያምኑት ያዳግታል።

በምድብ-አምሥት ኔዘርላንድ በሁለት ግጥሚያዎች ሁለት ድሎችን በማግኘት ለመጪው ዙር ማለፏን ከወዲሁ አረጋግጣለች። ዴንማርክን 2-0፤ እንዲሁም ጃፓንን 1-0 ስታሸንፍ በፊታችን ሐሙስ ታታሚዋ ካሜሩን ናት። ግጥሚያው በተለይም ለመጨረሻዋ ለካሜሩን አንዳች ትርጉም የለውም። አፍሪቃዊቱ አገር ሰንበቱን ከዚህ የዓለም ዋንጫ ውድድር ቀድማ በመሰናበት የመጀመሪያዋ ሆናለች።
የካሜሩን ብሄራዊ ቡድን በጃፓን 1-0 እና በዴንማርክ 2-1 ተሽንፎ በባዶ ነጥብ ሲቀር በተለይም በኋላኛው ግጥሚያ ጎል ለማስቆጠር የነበረውን መዓት ዕድል ሳይጠቀም መቅረቱ በጣሙን ያሳዝናል። በጥቅሉ በአፍሪቃ ቡድኖች ዘንድ እስካሁን ጎልቶ የታየው ይሄው ዕድልን የመጠቀም ጉድለት ነው። የቀድሞው የኢትዮጵያ ወጣት ብሄራዊ ቡድን አሠልጣኝ ስዩም አባተ እንደሚለው ጉድለቱ አገርን በክብር የመወከሉ መንፈስ አለመኖሩ ላይ ነው።

ምድብ-ስድሥትም ብዙ ተመልካችን ወቼ-ጉድ ማሰኘት የያዘ ምድብ ነው። ያለፈው የዓለም ዋንጫ ባለቤት ኢጣሊያ ከፓራጉዋይም ከኒውዚላንድም 1-1 በሆነ ውጤት ስትለያይ በአጭሩ ወደ ሮማ መልስ እንዳይሆን በፊታችን ሐሙስ የመጨረሻዋን ስሎቫኪያን የግድ ማሸነፍ አለባት። የኢጣሊያ ጋዜጦች ቡድኑን ደካማ በማለት በጅምላ ሲነቅፉ ከነዚሁ አንዱ ኮሪዬሬ-ዴ-ላ-ሤራ “ኢጣሊያ፤ ጥራት አልባ” ሲል ተችቷል። በምድቡ ውስጥ በወቅቱ ፓራጉዋይ በአራት ነጥቦች አንደኛ ስትሆን ኢጣሊያና ኒውዚላንድ እያንዳንዳቸው ሁለት ነጥቦች ነው ያሏቸው። ለነገሩ ሁለቱ ቡድኖች ከተሽነፉ ስሎቫኪያም የማለፍ ዕድል ይኖራታል።

Fußball WM 2010 Südafrika Portugal gegen Nordkorea
ምስል AP

ምድብ-ሰባትም በላቲን አሜሪካ፤ በአምሥት ጊዜዋ የዓለም ዋንጫ ባለቤት በብራዚል ቁጥጥር ስር እንዳለ ነው። ብሄራዊው ቡድን ሤሌሳኦ በቅድሚያ ሰሜን ኮሪያን 2-1፤ እንዲሁም ባለፈው ምሽት ደግሞ አይቮሪ ኮስትን 3-1 አሸንፎ በስድሥት ነጥቦች የሚመራ ሲሆን ለተከታዩ ዙር መድረሱን ቀድሞ አረጋግጧል። ስዊድናዊው የአይቮሪ ኮስት አሠልጣኝ ስቬን-ጉራን-ኤሪክሶን በተዘዋዋሪም ቢሆን የብራዚልን ልዕልና አምነው ነው የተቀበሉት።

“በቀላሉ ነው ጎል እንዲገባብን ያደረግነው። እርግጥ የብራዚል የመጀመሪያ ግብ በጣም ውብ ነበረች። በጨዋታው ሂደት 3-0 ከተመራን በኋላ እንደገና ጠንክረን ብንመለስም፤ ያሳስናል፤ ከአንዲት ጎል በላይ ለማስቆጠር አልቻልንም።

በምድቡ ውስጥ ቀጣዩ ትግል የሚደረገው ለሁለተኝነቱ ቦታ ነው። ይሄው ደግሞ የምድቡ ዙር እስከሚጠናቀቅበት እስከፊታችን አርብ ድረስ ይለይለታል።

በመጨረሻው ምድብ-ስምንት የዛሬው ምሽት በተለይም ለአውሮፓ ሻምፒዮኗ ለስፓኝ የሞት የሽረት ነው። ስፓኝ በመጀመሪያ ግጥሚያዋ በስዊትዘርላንድ 1-0 ስትረታ ውጤቱን የጠበቀው ማንም አልነበረም። በዚሁ ምድብ ውስጥ ሆንዱራስን ያሽነፈችው ቺሌም ከስዊስ ጋር በሶሥት ነጥቦችና አንድ ጎል እኩል በመሆን አመራሩን ስትይዝ ስፓኝና ሆንዱራስ ለመጀመሪያ ነጥቦቻቸው መታገል ይኖርባቸዋል። በዚህ በምሽቱ ግጥሚያ የሚሽነፈው ቡድን ከወዲሁ የሚሰናበት ነው።

በሌላ በኩል ስፓኝ ዛሬ ከቀናት በፊታችን አርብ ከቺሌ ጋር የምታደርገው ሶሥተኛ ግጥሚያ ከባድ ትግል የሰመረበት እንደሚሆን ከወዲሁ ግልጽ ነው። ምክንያቱም ቺሌም ሆነች ስፓኝ በሁለተኝነት በማለፍ በሚቀጥለው ዙር ከምድብ-ሰባት አሸናፊ ከብራዚል መገናኘቱን አይሹም። በተረፈ እስካሁን ከታየው ውጤት አንጻር ግምት ቢወሰድ በመጪው የመጀመሪያ ጥሎ-ማለፍ ዙር የአርጄንቲና ተጋጣሚ ኡሩጉዋይ ወይም ሜክሢኮ ልትሆን ትችላለች።
ያሳዝናል፤ ሁለት የላቲን አሜሪካ ቡድኖች ከወዲሁ መገናኘታቸው። ሌላው ሁኔታ መልሳ የምታንሰራራ ከሆነ ኢጣሊያ አለበለዚያም ፓራጉዋይ የኔዘርላንድ ተጋጣሚ ልትሆን መብቃቷ ነው። ብራዚል ቺሌም ላቲኖ የእርስበርስ ተጋጣሚዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ታዲያ የላቲን አሜሪካ የእስካሁን ጥንካሬ ሲታይ ቢቀር ሁለቱ ከሩብ ፍጻሜው ቀድመው የሚሰናበቱ መሆናቸው ጥቂትም ቢሆን የሚያሳዝን ነው። ለማንኛውም በትክክል የሚሆነውን በሣምንቱ መጨረሻ ላይ እንደርስበታለን። በነገራችን ላይ እንደ ስዩም አባተ ከሆነ ዋንጫዋ በመጨረሻ ምናልባትም ወደ ላቲን አሜሪካ የምታደላ ነው የሚመስለው። በዕውነትም የእስካሁኑ አካሄድ ከታየ አርጄንቲናና ብራዚል ፍጹም ልዕልና ነው የሚታይባቸው። ግን መጪው አይታወቅም።

መሥፍን መኮንን

አርያም ተክሌ