1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ መጋቢት 27 2002

በጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድር ቀደምቱ ክለብ ባየርን ሙንሺን እያየለ በመሄድ ላይ ነው።

https://p.dw.com/p/Mnbh
ምስል AP

በአውሮፓ ቀደምት የእግር ኳስ ሊጋዎች ውስጥ ሰንበቱን በተካሄዱት ግጥሚያዎች በዚህ በጀርመንና በእንግሊዝ ቼልሢይና ባየርን-ሙንሺን በየፊናቸው የቅርብ ተፎካካሪዎቻቸውን በማሸነፍ መልሰው አመራር ለመያዝ በቅተዋል። በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ሬያልና ባርሤሎና በነጥብ እኩል እንደሆኑ ሲቀጥሉ በፈረንሣይ አንደኛ ዲቪዚዮን ውስጥ ደግሞ የሻምፒዮናው ፉክክር በሶሥት ክለቦች መካከል እየጦፈ ነው። በአውሮፓ ክለቦች ሻምፒዮና ሊጋም የያዝነው ሣምንት ለግማሽ ፍጻሜው የሚያልፉት ክለቦች ማንነት የሚለይበት ነው።

በአንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ያለፈው ሰንበት ሁለቱ ቀደምት ክለቦች ቼልሢይና ማንቼስተር-ዩናይትድ እርስበርስ የተገናኙበት ነበር። በዚሁ ግጥሚያ ማንቼስተር-ዩናይትድ ለዚያውም በገዛ ሜዳው 2-1 ሲሸነፍ አመራሩን ለኤፍ.ሢ.ቼልሢይ ማስረከቡ ግድ ነው የሆነበት። ሣምንቱ በጠቅላላው በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋም ሆነ በፕሬሚየር ሊጉ ጨርሶ አልቀናውም። ለቼልሢይ ግቦቹን ያስቆጠሩት በሃያኛዋ ደቂቃ ላይ ጆው ኮልና በ 79ው ደቂቃ ላይ ደግሞ ተቀይሮ የገባው ዲዲየር ድሮግባ ነበሩ። የድሮግባ ግብ በኦፍሣይድነት ቢያከራክርም በውጤቱ ላይ ያስከተለው ለውጥ የለም። ለዩናይትድ ብቸኛዋን ጎል ያስቆጠረው ፌደሪኮ ማቼዳ ነበር።

ቼልሢይ ከ 33 ግጥሚያዎች በኋላ በ 74 ነጥቦች የሚመራ ሲሆን ማንቼስተር-ዩናይትድ 72 ነጥቦች አሉት። አንዲት ነጥብ ወረድ ብሎ የሚከተለው አርሰናል በበኩሉ ግጥሚያ ዋንደረርስን 1-0 ሲረታ ሻምፒዮናው የሶሥት ክለቦች ፉክክር የሰፈነበት ሆኖ እንዲቀጥል አድርጓል። ማንቼስተር-ሢቲይ ደግሞ ከርእሰናል 12 ነጥቦች ዝቅ ብሎ አራተኛ ሲሆን ቶተንሃም-ሆትስፐር፣ ሊቨርፑልና ኤስተን-ቪላ እስከ ሰባተኛው ቦታ ያሉት ተከታዮቹ ናቸው። ፖርትማውዝም የመጨረሻ፤ ሃያኛ እንደሆነ ቀጥሏል።

በስፓኝ ላ-ሊጋ አመራሩን በተመለከተ በሰንበቱ የተለወጠ ነገር የለም። ሬያል-ማድሪድ ሬሢንግ-ሣንታንዴርን ክሪስቲያኖ ሮናልዶና ጎንዛሎ ሂጉዌይን ባስቆጠራቸው ጎሎች 2-0 ሲረታ ባርሤሎናም ቢልባዎን 4-1 አሸንፏል። ከባርሣ ጎል አግቢዎች መካከል አንዱ አዘውትሮ እንደተለመደው ድንቁ ሊዮኔል ሜሢ ነበር። ከሰንበቱ ውጤት በኋላ ሁለቱም ክለቦች እኩል ነጥብ ሲኖራቸው ሬያል የሚመራው በአንዲት ጎል ብልጫ ብቻ ነው። ሁለቱ ቀደምት ክለቦች በፊታችን ሰንበት በሬያሉ በርናቤው ስታዲዮም እርስበርስ የሚገናኙ ሲሆን ጨዋታው ምናልባት ወሣኝነት ሊኖረው ይችላል። በሌላ በኩል ሶሥተኛው ቫሌንሢያ ኦሣሱናን 3-0 ቢያሽንፍም ከአመራሩ በ 11 ነጥቦች ዝቅ ያለ በመሆኑ የስፓኝ ሻምፒዮና በሁለቱ ክለቦች መካከል የሚለይለት ነው የሚመስለው።

በጀርመን ቡንደስሊጋም ሰንበቱ እንደ እንግሊዙ ፕሬሚየር ሊግ ሁሉ በቀደምት ክለቦች ግጥሚያ የአመራር ለውጥ የተደረገበት ሆኖ ነው ያለፈው። ባየርን-ሙንሺን ሻልከን ከሜዳው ውጭ 2-1 በማሽነፍ በአንዲት ነጥብ ብልጫ አመራሩን መልሶ ተረክቧል። ለባየርን ሁለቱን ጎሎች በአንድ ደቂቃ ጊዜ ውስጥ ያስቆጠሩት ፈረንሣዊው ፍራንክ ሪቤሪይና ቶማስ ሙለር ነበሩ። ለሆላንዳዊው አሠልጣኝ ለሉዊስ-ፋን-ኸል ድሉ በተለይም ከሁለተኛው አጋማሽ ጥንካሬ አንጻር ለባየርን የሚገባው ነው።
“እንደማስበው ጨዋታው ከባድ ነበር። ዕድል ሆኖ ግን ሁለት ጎሎች ለማስገባት ችለናል። በሁለተኛው አጋማሽ ለተጋጣሚያችን አንድም ዕድል አልሰጠንም። እና ከዚህ አንጻር ድሉ የሚገባን ነበር ባይ ነኝ”

የሊጋው ቀደምት ጎል አግቢ ኬቪን ኩራኒ ምንም እንኳ የሻልከን አንዲት ጎል በ 30ኛዋ ደቂቃ ላይ ቢያስቆጥርም በዕውነትም የጨዋታውን ሂደት ሊቀይረው አልቻለም። ባየርን ሙንሺን የመሃል ተጫዋቹ አልቲንቶፕ ከሜዳ ወጥቶበት እንኳ የሚበገር አልነበረም። ለዚህም በተለይ ምክንያቱ የሻልከ አሠልጣኝ ፌሊክስ ማጋት እንዳለው የቡድኑ አጨዋወት ወኔ የጎደለው መሆን ነው።

“ጨዋታችን ከጅምሩ አንስቶ በማጥቃት ላይ ያተኮረ አልነበረም። ፍጥነት አላሳየንም፤ በቂ ግፊትም አላደረግንም። በአንጻሩ አቀራረባችን ፍርሃት የተመላበት ነበር። እና በዚህ መልክ አንድን ቀደምት ክለብ ማሽነፍ አይቻልም”

በሌላ በኩል ሊጋውን ለ 24 ጊዜ ሳይሽነፍ በቁንጮነት ሲመራ ቆይቶ ባለፉት ሣምንታት መንገዳገድ የያዘው ባየር ሌቨርኩዝን በዚህ ሰንበትም ጠቃሚ ሶሥት ነጥቦችን አጥቷል። ሌቨርኩዝን በፍራንክፉርት 3-2 ሲሸነፍ አሁን ከአመራሩ የሚለየው’ በስድሥት ነጥቦች ነው። ይህ ደግሞ አንደኝነቱ ቀርቶ ለአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ማጣሪያ የሚያበቃውን ሶሥተኛ ቦታ እንኳ እንዳያጣ ያሰጋዋል። ዶርትሙንድና ብሬመን በቅርብ የሚከተሉት ተፎካካሪዎቹ ናቸው።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ኢንተር ሚላን ቦሎኛን 3-0 በመርታት አመራሩን እንደጨበጠ ሊቀጥል በቅቷል። ሁለተኛው ሮማም ባሪን 1-0 ሲያሸንፍ ኢንተርን በአንዲት ነጥብ ልዩነት እንደተከተለ ነው። ሮማ ባለፈው ሣምንት ኢንተርን ማሽነፉ ፉክክሩን ይበልጥ ሲያደምቅ ኤ.ሢ.ሚላንም በሶሥተኝነት ይከተላል። የሻምፒዮና ፉክክርን መጠናከር ካነሣን በፈረንሣይ አንደኛ ዲቮዚዮንም ትግሉ የሶሥት ክለቦች እየሆነ ነው። ኦላምፒክ ሊዮን፣ ሞንትፔልዬርና ኦግዜር ከትናንት ወዲህ እኩል 57 ነጥቦች ሲኖራቸው ሊዮን የሚመራው በጎል ልዩነት ብቻ ነው።
በፖርቱጋል ሻምፒዮና ብራጋ ጊማሬሽን 3-2 ረትቶ ቀደምቱን ቤንፊካን በሶሥት ነጥቦች ልዩነት ሲቃረብ ሶሥተኛው ፖርቶም ማሪቲሞን 4-1 ሸኝቷል። ቤንፊካ ሊዝበን ከናቫል ጋር የሚጋጠመው በዛሬው ምሽት ነው። በኔዘርላንድ ደግሞ ውድድሩ ሊጠናቀቅ አራት ግጥሚያዎች ብቻ ቀርተው ሳለ ትዌንቴ-እንሼዴ ለብቻው እንደመራ ነው። ቡድኑ ፌንሎን 2-0 ሲረታ ተከታዮቹ አያክስ-አምስተርዳምና አይንድሆፈንም የየበኩላቸውን ግጥሚያዎች አሸንፈዋል። ኤንሼዴ በወቅቱ አያክስን አስከትሎ የሚመራው በአራት ነጥብ ልዩነት ነው።

የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ

Deutschland Fußball Champions League Bayern München gegen Manchester United
ማንቼስተር ዩናይትድና ባየርንምስል AP

በእግር ኳሱ መድረክ በተረፈ የያዝነው ሣምንት የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ሩብ ፍጻሜ ግጥሚያዎች የሚጠናቀቁበት ነው። በነገው ምሽት ባርሤሎና በመልስ ጨዋታው ከአርሰናል የሚገናኝ ሲሆን ባለፈው ሣምንት የመጀመሪያ ግጥሚያ ሁለቱ ክለቦች እኩል-ለእኩል መለያየታቸው የሚታወስ ነው። ያለፈው ውድድር ወቅት ሻምፒዮን ባርሤሎና 2-0 ከመራ በኋላ ያንኑ ያህል ገብቶበት ድሉን ይነጠቃል ብሎ የጠበቀ ተመልካች አልነበረም። ሆኖም አርሰናል ብዙዎች ታዛቢዎችን ሲያስደንቅ የመልሱ ግጥሚያ ለባርሣ ፈታኝ መሆኑ የሚቀር አይመስልም።
የነገው ሁለተኛ ግጥሚያ በሞስኮና በኢንተር-ሚላን መካከል የሚካሄድ ሲሆን ኢንተር በመጀመሪያው ግጥሚያ ያገኘው ድል ይብቃው አይብቃው የሚታይ ይሆናል። ሢ.ስ.ኬ.ኤ.ሞስኮ በተለይ በአገሩ ቀላል ተጋጣሚ አይሆንም። በማግሥቱ ረቡዕ ምሽት ትልቁ ግጥሚያ በማንቼስተር ዩናይትድና በባየርን ሙንሺን መካከል የሚካሄደው ነው። ባየርን ባለፈው ሣምንት በሜዳው 2-1 ቢያሽንፍም ቀላል የመልስ ግጥሚያ አይጠብቀውም። በሌላ በኩል ለማንቼስተር-ዩናይትድም የአጥቂው የዌይን ሩኒይ መቁሰል በጣም የሚያጎለው ሊሆን የሚችል ነው። ሌላው የፈረንሣይ ክለቦች የእርስበርስ ግጥሚያ በቦርዶና በኦላምፒክ ሊዮን መካከል ይካሄዳል። ሊዮን በመጀመሪያው ግጥሚያ 3-1 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

Formel 1 Sebastian Vettel Flash-Galerie
ምስል AP

የአውቶሞቢል እሽቅድድም

ትናንት ማሌይዚያ ውስጥ የተካሄደው ሶሥተኛ የፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል እሽቅድድም አሸናፊ የ 22 ዓመቱ ወጣት ጀርመናዊ ዜባስቲያን ፌትል ሆኗል። ዜባስቲያን ፌትል በዘንድሮው ውድድር ሲያሸንፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን የሜርሤዲሱ ዘዋሪ የሰባት ጊዜው የዓለም ሻምፒዮን ሚሻኤል ሹማኸር በአንጻሩ በ 11ኛው ዙር ተሰናክሉ ቀርቷል።

በውድድሩ አውስትራሊያዊው ማርክ ዌበር ሁለተኛ ሲወጣ ጀርመናዊው ኒኮ ሮዝበርግ ደግሞ ሶሥተኛ ሆኗል። እስካሁን በተካሄዱት ሶሥት ውድድሮች በጠቅላላ ነጥብ ብራዚላዊው ፌሊፔ ማሣ በ 39 የሚመራ ሲሆን የስፓኙ ፌርናንዶ አሎንሶና ዜባስቲያን ፌትል በ 37 ነጥቦች ይከተላሉ። በእኩል 35 ነጥቦች አራተኛና አምሥተኛውን ቦታ የያዙት ደግሞ የብሪታኒያው ጄሰን ባተንና የጀርመኑ ኒኮ ሮዝበርግ ናቸው። የዘንድሮው ውድድር ገና 16 እሽቅድድሞች የሚቀሩት ሲሆን ጉዞው ገና ረጅም ነው።

ጤኒስ

Andy Roddick beim Wimbledon-Finale 2009
ምስል AP

ማያሚ ላይ ሲካሄድ የሰነበተው የሶኒይ-ኤሪክሰን-ኦፕን ዓለምአቀፍ የቴኒስ ውድድር በወንዶች በአሜሪካዊው በኤንዲይ ሮዲክ አሸናፊነት ተፈጽሟል። ሮዲክ የቼክ ሬፑብሊክ ተጋጣሚውን ቶማስ ቤርዲችን ጠንካራ አጨዋወት በማሳየት 7-5, 6-4 በሆነ ውጤት ሲያሸንፍ ከአራት ዓመታት ቆይታ በኋላ እንደገና ለማስተርስ ድል በቅቷል። ለቀድሞው የዓለም አንደኛ አሜሪካዊ የትናንቱ ድሉ በጠቅላላው 29ኛው መሆኑም ነው።
በሴቶች ደግሞ የቤልጂጓ ኪም ክላይስተርስ የአሜሪካዊቱ የቬኑስ ዊሊያምስ የ 15 ግጥሚያዎች የድል ጉዞ እንዲቋረጥ በማድረግ በፍጹም የበላይነት አሸንፋለች። ኪም 6-2, 6-1 በሆነ ውጤት በለየለት ሁኔታ ስታሸንፍ ከ 58 ደቂቃዎች የበለጠ ጊዜ አላስፈለጋትም። ክላይስተርስ በወሊድ ምክንያት ለሁለት ዓመታት ያህል ከቴኒሱ መድረክ ከተለየች በኋላ የተመለሰችው ባለፈው ዓመት ነበር።

MM/DW/RTR/AFP/dpa

Negash Mohammed