1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ የካቲት 1 2002

ኡክራኒያና ፖላንድ በሁለት ዓመት ተኩል ገደማ በሕብረት ለሚያስተናግዱት የአውሮፓ እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ትናንት ዋርሶው ላይ የምድብ ዕጣዎች ወጥተዋል።

https://p.dw.com/p/LvpS
ምስል AP

የቦስተን የአዳራሽ ውስጥ አትሌቲክ ውድድር

ከትናንት በስቲያ አሜሪካ ውስጥ ተካሂዶ በነበረው 15ኛው የቦስተን የአዳራሽ ውስጥ አትሌቲክስ ውድድር የኢትዮጵያ አትሌቶች በመካከለኛና ረጅም ርቀት ሩጫ ግሩም ውጤት ሊያስመዘግቡ በቅተዋል። በተለይም የኦሎምፒክ ድርብ ድል ባለቤት የሆነችው ጥሪነሽ ዲባባ እንደቀድሞዋ የማትበገር ነበረች። ጥሩነሽ በአምሥት ሺህ ሜትር ሩጫ ምንም እንኳ እንዳለመችው ለአዲስ ክብረ-ወሰን ባትበቃም የዓመቱን ፈጣን ጊዜ በማስመዝገብ አሸናፊ ሆናለች። ድንቋ አትሌት ሩጫውን በ 14 ደቂቃ ከ 44,53ሤኮንድ ስትፈጽም ከዓለም ክብረ-ወሰን ላይ ለመድረስ የቀሯት ሃያ ሤኮንዶች ብቻ ነበሩ። ኬንያዊቱ ሤሊይ ኪፕየጎ ስምንት ሤኮንዶች ያህል ዘግይታ በመግባት ሁለተኛ ሆናለች።

Olympia 2008 Äthiopien Gold für Tirunesh Dibaba 10000 m Lauf
ምስል picture-alliance/ dpa

የኢትዮጵያ ሴቶች ድል በጥሩነሽ ብቻ አልተወሰነም። በሶሥት ሺህ ሜትር ሩጫ እንዲያውም ድርብ ድል ነው የተገኘው። በዚሁ የኢትዮጵያውያን ግሩም ፉክክር በታየበት ሩጫ የ 18 ዓመቷ ወጣት ቃልኪዳን ገዛኸኝ አንደኛ ስትወጣ ገንዘቤ ዲባባ ደግሞ አሜሪካዊቱን ሼሞን ሮውበሪይን አስከትላ ሁለተኛ ለመሆን በቅታለች። በወንዶች አምሥት ሺህ ሜትር ምንም እንኳ ከኬንያ የመነጨው አሜሪካዊ አትሌት በርናርድ ላጋት በዚህ ርቀት ባደረገው የመጀመሪያ ውድድር የአሜሪካን ሬኮርድ ሰብሮ ቢያሸንፍም ደጀን ገ/መስቀልና በካና ዳባ በተመሳሳይ ጊዜ ሁለተኛና ሶሥተኛ በመሆን ከቀደምቱ መካከል መሆናቸውን አስመስክረዋል። በተረፈ በማይል ሩጫ ባለፈው ዓመት ተደርጎለት ከነበረ የቀዶ ጥገና ሕክምና አገግሞ የተመለሰው የኒውዚላንዱ የቤይጂንግ ኦሎምፒክ የ 1,500 ሜትር ብር ሜዳይ ተሸላሚ ኒክ ዊሊስ አሸናፊ ሆኗል። ያስመዘገበው ግሩም ጊዜ በአዲሱ ዓመት ፈጣኑ መሆኑ ነው። አሜሪካውያኑ ዊል ሊር ሁለተኛ፤ እንዲሁም ዴቪድ ቶራንስ ሶሥተኛ በመሆን ሩጫውን ፈጽመዋል።
ሰንበቱ በዚህ በጀርመን የሽቱትጋርት ከተማ የአዳራሽ ውስጥ ውድድርም የኢትዮጵያ አትሌቶች ገነው የታዩበት ሆኖ ነው ያለፈው። በ 1,500 ሜትር ሩጫ ገለቴ ቢርቃ ሩሢያዊቱን አና አልሚኖቫን አስከትላ ስታሸንፍ በሶሥት ሺህ ሜትር ደግሞ መሠረት ደፋርና ስንታየሁ እጅጉ አንደኛና ሁለተኛ በመውጣት ባለድል ሆነዋል። በወንዶች 1,500 ሜትር ደረሰ መኮንን ኬንያዊውን ዊሊያም ታኑዊን ቀድሞ አንደኛ ሲሆን በሶሥት ሺህ ሜትር ታሪኩ በቀለ ኬንያዊውን ኤሊዩድ ኪፕቾጌን ተከትሎ ሁለተኛ ወጥቷል። በዱስልዶርፍ በሣምንቱ አጋማሽ ላይ ተካሂዶ በነበረ ውድድር ደግሞ የኩባው የ 110 ሜትር መሰናክል የዓለም ሻምፒዮን ዴይሮን ሮብልስ በ 60 ሜትር መሰናክል የወቅቱን ሁለተኛ ፈጣን ሰዓት አስመዝግቧል። የ 23 ዓመቱ ወጣት ከወር ገደማ በኋላ በሚካሄደው የአዳራሽ ውስጥ የዓለም ሻምፒዮና አቻ የማይገኝለት ነው የሚመስለው።

ከዚሁ ሌላ ሩሢያዊው ዩሪ ቦርዛኮቭስኪ በ 800 ሜትር ሩጫ ሲያሸንፍ ኬንያዊው ፓውል ኮች ደግሞ በአምሥት ሺህ ሜትር በዓለም ላይ እስካሁን አምሥተኛው በሆነው ፈጣን ጊዜ ለድል በቅቷል። ኬንያን ካነሣን ጆናታን ኪፕኮሪር ትናንት በጃፓን የቤፑ-ኦኢታ ማራቶን 42ቱን ኪሎሜትር በ 2 ሰዓት ከ 10 ደቂቃ ከ 50 ሤኮንድ በማቋረጥ አሸናፊ ሆኗል። ኪፕኮሪርና ሁለተኛ የወጣው ሌላው ኬንያዊ ብርቱ ፉክክር ሲያሣዩ ሩጫው የለየለት በመጨረሻዎቹ ሁለት ኪሎሜትሮች ውስጥ ነበር። የአውስትራሊያው ጄፍሪይ ሃንግ ሶሥተኛ ሲሆን የኢትዮጵያው ተወዳዳሪ ጫላ ለሚ ደግሞ ሰባተኛ ወጥቷል። ከዚህ ሌላ ሞስኮ ላይ በተካሄደ የአትሌቲክስ ውድድር ሩሢያዊቱ የምርኩዝ ዝላይ ንግሥት የለና ኢዚንባየቫ 4 ሜትር ከ 85 ከፍታን በማቋረጥ አሸንፋለች። ሆኖም የራሷን ክብረ-ወሰን ማሻሻሉ ግን አልተሳካላትም። ኢዚንባየቫ ከአንድ ዓመት በፊት ኡክራኒያ-ዶኔትስክ ላይ 5,1̂1 ሜትር የአዳራሽ ውስጥ የዓለም ክብረ-ወሰን ስታስመዘግም ባለፈው ነሐሴ ደግሞ ዙሪክ ላይ የውጭ 5,6 ሜትር ሬኮርድ ባለቤት ለመሆን መብቃቷ የሚታወስ ነው።

የአውሮፓ እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ዕጣ

በኡክራኒያና በፖላንድ የጋራ አስተናጋጅነት የሚካሄደው የአውሮፓ እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ሁለት ዓመት ተኩል ገደማ ቀርቶት ሳለ ትናንት ዋርሶው ላይ የማጣሪያው ዙር የምድቦች ዕጣ ወጥቷል። በመጀመሪያው ምድብ ጀርመን ከቱርክ፣ አውስትሪያ፣ ቤልጂግ፣ ካዛክስታንና አዘርባይጃን ስትደለደል በአገሪቱ እግር ኳስ ፌደሬሺን ዕምነት ፈተናው የሚታለፍ ነው። ይሁንና የቡድኑ አሠልጣኝ ዮአሂም ሉቭ በተለይ ቱርክን ከባድ ተፎካካሪ አድርጎ ነው የሚመለከተው።

“ምድቡ ጀርመንኛ ተናጋሪዎች ያሉበት ምድብ ነው። ብዙዎቹ አሠልጣኞች ጀርመንኛ ተናጋሪ ወይም ጀርመኖች ናቸው። እናም ይሄው ማራኪ ያደርገዋል። ሆኖም ግን ጀርመን ከቱርክ ጋር የምድቡ ቀደምት ትሆናለች ብዬ አስባለሁ”

በተቀረው ዕጣ በምድብ-ሁለት ሩሢያ ከስሎቫኪያና ከአየርላንድ ጋር ስትደለደል በምድብ-ሶሥት ኢጣሊያን ሰርቢያን፣ ሰሜን አየርላንድንና ስሎቬኒያን የመሳሰሉ ብርቱ ተፎካካሪዎች ይጠብቋታል። በምድብ-አራት ፈረንሣይ ከሩሜኒያ፣ ከቤላሩስና ከቦስና የምትገናኝ ሲሆን በምድብ-አምሥት የኔዘርላንድ ዋነኛ ተፎካካሪ ስዊድን ናት። ምድብ-ስድሥት ውስጥ ክሮኤሺያና ግሪክ ቀደምቱ ሲሆኑ በምድብ-ሰባት እንግሊዝን ስዊትዘርላንድ፣ ቡልጋሪያ፣ ዌልስና ሞንቴኔግሮ ይጠብቋታል። በተቀሩት ሁለት ምድቦች ፖርቱጋል ዴንማርክንና ኖርዌይን የመሳሰሉ ጠናካራ ተፎካካሪዎች ሲገጥሟት የአውሮፓ ሻምፒዮኗ የስፓኝ የምድብ ተጋጣሚዎች ደግሞ ቼክ ሬፑብሊክ፣ ስኮትላንድ፣ ሊቱዋኒያና ሊሽተንሽታይን ናቸው። ሁለቱ አስተናጋጅ አገሮች ኡክራኒያና ፖላንድ ያለማጣሪያ በቀጥታ የፍጻሜው ተሳታፊዎች ይሆናሉ።

የዓለም እግር ኳስ ፌደሬሺኖች ማሕበር በበኩሉ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ለሚከፈተው የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ከየክፍለ-ዓለሙ የተውጣጡ ዳኞችንና የመሥመር ዳኞችን በሣምንቱ መጨረሻ ላይ ሰይሟል። ከአፍሪቃ 12 ዳኞች ሲመረጡ እነዚሁም ከአልጄሪያ፣ ከግብጽ፣ ከማሊ፣ ከሞሮኮ፣ ከአንጎላና ከደቡብ አፍሪቃ፤ እንዲሁም ከሩዋንዳ ከሤይሼልስና ከካሜሩን የተውጣጡ ናቸው። በዋና ዳኝነት ከአውሮፓ አሥር፣ ከደቡብ አሜሪካ ስድሥት፤ ከእሢያ፣ ከአፍሪቃና ከሰሜን-ማዕከላዊ አሜሪካ ኮንካካፍ አካባቢ አራት አራት፤ እንዲሁም ከኒውዚላንድ ሁለት ተሰይመዋል። ብዙዎችን ያስደነቀ ነገር ቢኖር ፊፋ ፈረንሣይ በዕጅ በገባች ጎል አየርላንድን አልፋ ለዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ተሳትፎ የበቃችበትን አከራካሪ ማጣሪያ ግጥሚያ የመሩትን የስዊድን ዳና ማርቲን ሃንሶንን ለደቡብ አፍሪቃ መምረጡ ነው።

በተረፈ አንጎላ ውስጥ ተካሂዶ በነበረው የአፍሪቃ ዋንጫ ውድድር በውጤታቸው ያልረኩት ናይጄሪያ ቤኒን አሠልጣኞቻቸውን አባረዋል። በዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ተሳታፊ የሆነችው ናይጄሪያ ምንም እንኳ የክፍለ-ዓለሙን ውድድር በሶሥተኝነት ብትፈጽምም አሠልጣኙ ሻኢቡ አሞዱ ከስንብት ሊያመልጡ አልቻሉም። አሞዱ በተመሳሳይ ሁኔታ ከአሠልጣኝነት ሲወገዱ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን የናይጄሪያ እግር ኳስ ፌደሬሺን ቴክኒካዊ ኮሚቴ እስከያዝነው ወር መጨረሻ ድረስ አዲስ አሠልጣኝ ፈልጎ እንዲያቀርብ ጊዜ ተሰጥቶታል። ቤኒንም እንዲሁ በአፍሪቃው ዋንጫ ደካማ አቀራረቧ የተነሣ ፈረንሣዊ አሠልጣኟን ሚሼል ዱሱየን አሰናብታለች። ብሄራዊው ቡድን በመጀመሪያ የምድብ ግጥሚያዎቹ በሁለቱ ተሸንፎ አንዴ ብቻ እኩል ለእኩል በመውጣት ከውድድሩ ቀድሞ መሰናበቱ የሚታወስ ነው።

ባየርን ሙንሺን
ባየርን ሙንሺንምስል AP


የጀርመን ቡንደስሊጋ/አውሮፓ

በጀርመን ቡንደስሊጋ ቀደምቱ ሌቨርኩዘን ከቦሁም ጋር ባካሄደው ግጥሚያ አቻ ለአቻ በሆነ ውጤት ብቻ በመወሰኑ ከታች ወደ ላይ እየገሰገሰ የመጣው ባየርን ሙንሺን በነጥብ ደርሶበታል። ባየርን ሙንሺን ግሩም በሆነ ጨዋታ ያለፈውን የውድድር ወቅት ሻምፒዮን ቮልፍስቡርግን 3-1 ሲሸኝ ከሌቨርኩዝን የሚለየው የሁለት ጎሎች ልዩነት ብቻ ነው። የቡንደስሊጋው ሬኮርድ ሻምፒዮን ባየርን ሙንሺን በሰንበቱ ድሉ የልብ ልብ ሲያገኝ በአንጻሩ ሌቨርኩዝን በአስደናቂ ሁኔታ ሲመራ ከቆየ በኋላ ብርክ እንዳይይዘው ያሰጋዋል። እርግጥ ባየርን ሙንሺንም ቢሆን ቤልጂጋዊ ተከላካዩ ቫን-ቡይተን እንዳለው ያልሆነ ስህተት እንዳይሰራ ገና ብዙ መጠንቀቅ ይኖርበታል።

“ከራሳችን መጠንቀቅ አለብን። ራሳችንን ልንረታ የምንችለው እኛው ራሳችን ብቻ ነን። መቶ በመቶ ትኩረት ሳንሰጥ ዛሬ ቀላል ሊሆን ይችላል ብለን የገመትነው አንድ ጨዋታ ቢያጋጥመን እጅግ አደገኛ ነው የሚሆነው። እናም ራሳችንን ማሸነፍ የምንችለው እኛው ነን ማለት ነው’”

በኢጣሊያ ሊጋ ካልጋሪን 3-0 ያሸነፈው ኢንተር ሚላን በተከታታይ አምሥተኛ ሻምፒዮና አቅጣጫ ማምራቱን እንደቀጠለ ሲሆን በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ደግሞ ቼልሢይ አርሰናልን 2-0 በማሽነፍ አመራሩን መልሶ ይዟል። ማንቼስተር ዩናይትድ ሁለት ነጥቦች ዝቅ ብሎ ሁለተኛ ነው። በስፓኝ ላ-ሊጋ ጌታፌን 2-0 የረታው ባርሤሎና ሬያል ማድሪድን በአምሥት ነጥቦች ልዩነት በርቀት እንዳስከተ ይመራል። በፈረንሣይና በኔዘርላንድ ሊጋዎች ደግሞ ቦርዶና አይንድሆፈን በየፊናቸው በሶሥት ነጥቦች ልዩነት ቁንጮ ሆነው እንደቀጠሉ ነው።

ቴኒስ፤ የፌደሬሺን ዋንጫ ውድድር

ያለፈው የቴኒስ ፌደሬሺን ዋንጫ ባለቤት ኢጣሊያ ትናንት ኡክራኒያን 4-1 በመርታት ወደ ግማሽ ፍጻሜ ለመዝለቅ ችላለች። ቀጣይዋ የኢጣሊያ ተጋጣሚ ጀርመንን 3-2 ያሽነፈችው ቼክ ሬፑብሊክ ናት። ሩሢያም ሰርቢያን ቤልግሬድ ላይ 3-2 ስታሸንፍ በግማሽ ፍጻሜ የምትገናኘው ፈረንሣይን ካስወጣችው ከአሜሪካ ጋር ነው። በሌሎች ዓለምአቀፍ ግጥሚያዎች የክሮኤሺያው ተወላጃ ማሪን ቺሊች ዛግሬብ ውስጥ በተካሄደ የአዳራሽ ውስጥ ፍጻሜ ግጥሚያ ጀርመናዊውን ሚሻኤል ቤረርን 2-1 በማሸነፍ ያለፈውን ድሉን ደግሞታል። በደቡብ አፍሪቃ-ኦፕን ፍጻሜ ደግሞ የስፓኙ ፌሊቺያኖ ሎፔዝ የፈረንሣይ ተጋጣሚውን ስቴፋን ሮበርትን በሁለት ምድብ ጨዋታ በመርታት ለሁለተኛ የ ATP ድሉ በቅቷል።

መስፍን መኮንን/DW/AFP/RTR

ሸዋዬ ለገሠ