1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ጥር 24 2002

አንጎላ ውስጥ የተካሄደው የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ትናንት እንደገና በግብጽ አሸናፊነት ተፈጽሟል። በደቡብ አፍሪቃው የዓለም ዋንጫ ዋዜማ ውድድሩ የቀደምቱን አገሮች ብቃት መለኪያና መመዘኛ ሆኖ ነው የታየው።

https://p.dw.com/p/Lojo
ምስል AP

የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር

አንጎላ ውስጥ የተካሄደው 27ኛው የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ትናንት እንደገና በግብጽ አሸናፊነት ተፈጽሟል። ግብጽ ለዚህ ክብር የበቃችው የፍጻሜ ተጋጣሚዋን ጋናን 1-0 በመርታት ነው። ብቸኛዋን የድል ጎል ግጥሚያው ሊያበቃ አምሥት ደቂቃዎች ሲቀሩት ያስቆጠረው ተቀያሪው ተጫዋች ሞሕመድ ናጊ ነበር። ሃያሉ የግብጽ ቡድን ባለፈው ሕዳር ወር በአልጄሪያ ተሸንፎ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ዕድሉን ማጣቱ ሲታወስ የትናንቱ ድል መበረታቻ እንደሚሆነው አንድና ሁለት የለውም። ቡድኑ ለፍጻሜ የደረሰውም በተለይ ያችኑ አልጄሪያን በግማሽ ፍጻሜ ግጥሚያው 4-0 ቀጥቶ ከሽኘ በኋላ ነበር። የትናንቱ የአፍሪቃ ዋንጫ ድል ለግብጽ በተከታታይ ሶሥተኛው ሲሆን ይህም በውድድሩ ታሪክ ውስጥ እስካሁን አቻ ያልታየለት ነው።
በነገራችን ላይ ብሄራዊው ቡድን ባለፉት 19 የአፍሪቃ ዋንጫ ማጣሪያና ፍጻሜ ግጥሚያዎች አንዴም አልተሽነፈም። ይህም ሌላው የጥንካሬ ምልክቱ ነው። የግብጽ ብሄራዊ ቡድን በውድድሩ ሂደት ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ያሳየው ልዕልናና የአጨዋወት ስክነት ሲታሰብ አገሪቱ በመጪው የደቡብ አፍሪቃ የዓለም ዋንጫ ውድድር ክፍለ-ዓለሚቱን ከሚወክሉት አንዷ ለመሆን አለመብቃቷ ታዲያ ጥቂትም ቢሆን ቅር ማሰኘቱ አይቀርም። መለስ ብሎ ለማስታወስ ያህል ግብጽ ውድድሩ እ.ጎ.አ. በ 1957 ከተጀመረ ወዲህ ከትናንቱ ጋር ሰባት ጊዜ የዋንጫ ባለቤት በመሆን በአፍሪቃ ቀደምቷ ናት። በጎል አግቢነትም አምሥት በማስቆጠር ዘንድሮ ግንባር ቀደም የሆነው ትናንት የድል ግቧን ያስቆጠረው ሞሐመድ ናጊ ነበር።

ወጣቱ የጋና ብሄራዊ ቡድን በአንጻሩ በመጀመሪያ ግጥሚያው በአይቮሪ ኮስት 3-1 ሲሽነፍና ከዚያም የቼልሢው ኮከብ ማይክል ኤሢየንና ሌሎች ጠንካራ ተጫዋቾቹ ሲቆስልበት ለፍጻሜ ይደርሳል ብሎ የጠበቀ ብዙ አልነበረም። የአገሪቱ የስፖርት ጋዜጠኛ አዬዪ ሮክሣን ሣይቀር ሁኔታውን እንዲህ ነበር የገለጸው።

“የብላክ-ስታርስ፤ የጥቁር ኮከቦች አጨዋወት አስከፊ ነው ለማለት እወዳለሁ። ወደፊት ሌላ ሆነን መቅረብ ይኖርብናል”
እርግጥም የጋና ብሄራዊ ቡድን ለመጠናከር ብዙ ጊዜ አልወሰደበትም። ባለፈው ዓመት ከሃያ ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ውድድር አሸናፊ የነበሩትን ስምንት ተጫዋቾች ያቀፈው የጥቁር-ኮከቦች ቡድን በተለይም በድንቅ ተጫዋቹ በአሣሞአህ ጊያን አማካይነት እየጠነከረ በመሄድ አስተናጋጇን አንጎላን በሩብ ፍጻሜ አሸንፎ ያሰናብታል።

ጋና በግማሽ ፍጻሜው ናይጄሪያን በተመሳሳይ ውጤት በማሰናበት ለፍጻሜ ስትደርስ ዋንጫው ይቅርባት እንጂ ከግብጽ ጥንካሬ አንጻር ሁለተኝነቱም ያን ያህል የከፋ ውጤት አይሆንም። ለዓለም ዋንጫው ውድድር በሚገባ እንድትዘጋጅ የመንፈስ ብርታት የሚሰጣት ነው። በረኛው ሪቻርድ ኪንግሰን “ዓለም ጋናን የዓይኑ ማረፊያ ማድረግ አለበት” ሲል ነው በተለይም ጀርመንን በመሳሰሉት የዓለም ዋንጫ የምድብ ተጋጣሚዎቹ አቅጣጫ ቡድኑ ዋዛ እንደማይሆን ማስጠንቀቂያ የሰነዘረው።

ሌሎቹ ለዋንጫ ባለቤትነት ከፍተኛ ዕድል ተሰጥቷቸው የነበሩት ካሜሩንና አይቮሪ ኮስት በውድድሩ የተጠበቁትን ያህል አልነበሩም። ካሜሩን ገና በመጀመሪያ የምድብ ግጥሚያዋ በጋቦን 1-0 መረታቷ የሚታወስ ሲሆን እንደምንም ለሩብ ፍጻሜ ትድረስ እንጂ ግብጽን አልፋ ልትራመድ አልቻለችም። 3-1 በመሸነፍ በዚያው በሩብ ፍጻሜው ነበር ስንብት ያደረገችው። ዲዲየር ድሮግባን የመሳሰሉ ከዋክብትን ያሰባሰበው የአይቮሪ ኮስት ቡድንም እንዲሁ በሩብ ፍጻሜው በአልጄሪያ ተሸንፎ መቅረቱ ግድ ነው የሆነበት። ታዲያ የነዚህ ቀደምት ቡድኖች በውድድሩ ደክሞ መታየት በመጪው የደቡብ አፍሪቃ የዓለም ዋንጫ ከአፍሪቃ ተሳታፊዎች መካከል እስከ ሩብ ፍጻሜ እንኳ የሚዘልቅ መገኘቱን ቢቀር በወቅቱ የማይመስል ነገር ነው ያደረገው። ሆኖም ለምሳሌ የአልጄሪያው ተጫዋች ካሪም ማትሙር እንዳለው በአንጎላው ውድድር የተገኘው ልምድ ለተሻለ ዝግጅትና ተጠናክሮ ለመመለስ ጠቃሚ ድርሻ ሊኖረው ይችላል።

“የመጀመሪያ ውድድራችን በመሆኑ ጥቂት ልምድ መቅሰማችን አልቀረም። ቡድናችን ገና ወጣት ሲሆን በአጠቃላይ በዝግጅቱና በተናጠልም በያንዳንዱ ግጥሚያ ላይ በማተኮር ብዙ ትምሕርት ነው ያገኘነው። ምናልባት በሆነ ወቅት አንድ ዋንጫ ልንወስድ እንችል ይሆናል”

ከካሜሩን በኩልም እንዲሁ ተመሳሳይ አስተያየት ተሰምቷል። እንደ ካሪም ማትሙር ሁሉ በዚህ በጀርመን ቡንደስሊጋ የሚጫወተው የካሜሩን ብሄራዊ ቡድን ባልደረባ ማሃማዱ ኢድሪሱም የወደፊቱን በተሥፋ ነው የሚመለከተው።

“እግር ኳስ ትምሕርታዊ ሂደት ያለው ነገር ነው ብዬ አምናለሁ። እና እኛም በዚህ የአፍሪቃ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ብዙ ጠቃሚ ነገሮችን አይተናል። አሁን ታዲያ ለመጪው የዓለም ዋንጫ ለመዘጋጀት ጊዜውን በሚገባ መጠቀማችን ግድ ነው”

27ኛው የአፍሪቃ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር አስከፊ ገጽታም የጋረደው ነበር። ገና በዋዜማው ካቢንዳ ውስጥ በቶጎ ብሄራዊ ቡድን ላይ የተቃጣው የዓማጺያን ጥቃት ከመክፈቻው ስነ-ስርዓት ይልቅ ዓለምን ብዙ ሲያነጋግር ከአንጎላ ዘልቆ የደቡብ አፍሪቃን የዓለም ዋንጫ መስተንግዶ ብቃትም አጠያያቂ እስከማድረግ ነበር የደረሰው። ለማንኛውም ውድድሩ ይህን ሁሉ አልፎ በሰላም ተፈጽሟል። አጠያያቂ ነገር ቢኖር የአፍሪቃ እግር ኳስ ኮንፌደሬሺን የቶጎ መንግሥት ጥቃቱን አስመልክቶ ተጫዋቾቹ ወደ አገር እንዲመለሱ በማድረጉ አገሪቱን ከሁለት የአፍሪቃ ዋንጫ ውድድሮች ማገዱ ነው። ይህ ውሣኔ በተለይ ለተጫዋቾቹ መሪር እንደሚሆን አንድና ሁለት የለውም።

ዓለምአቀፍ አትሌቲክስ

ባለፈው ሣምንት ከአውሮፓ እስከ አሜሪካ የተለያዩ የአትሌቲክስ ውድድሮች ሲካሄዱ በኦሣካ ዓለምአቀፍ የሴቶች ማራቶን አማኔ ጎበና ግሩም በሆነ አራሯጥ ለማሸነፍ በቅታለች። ኢትዮጵያዊቱ አትሌት ለድል የበቃችው የፖርቱጋል የቅርብ ተፎካካሪዋን ማሪሣ ባሮስን አራት ኪሎሜትር ሲቀር ጥላ በመሄድ ነበር። አማኔ ጎበና ሩጫውን በሁለት ሰዓት ከሃያ-አምሥት ደቂቃ አሥራ-አራት ሤኮንድ በመፈጸም የራሷን ፈጣን ጊዜ ለማሻሻልም ችላለች። ባሮስ ሁለተኛ ስትወጣ ሶሥተና የሆነችው ጃፓናዊቱ ማሪ ኦሣኪ ነበረች።
በዚህ በጀርመን ካርስሩኸ ውስጥ በተካሄደ የአዳራሽ ውስጥ ውድድር ደግሞ ገለቴ ቡርቃ የ 1,500 ሜትር አሸናፊ ሆናለች። በወንዶች በተመሳሳይ ርቀር ኬንያዊው ጊዴዎን ጋቲምባ ሲያሸንፍ ገ/መድህን መኮንን ደግሞ ሁለተኛ ወጥቷል። ከዚሁ በተጨማሪ በሶሥት ሺህ ሜትር ሩጫ በወንዶች የካታሩ ሣኢፍ-ሣአድ-ሻሄን ሲያሽንፍ በሴቶች ኬንያዊቱ ሢልቪያ ኪቤት ቀዳሚ ሆናለች። በኒውዮርክ 103ኛ የሜልሮዝ የአዳራሽ ውስጥ ጨዋታ ደግሞ ከኬንያ የመነጨው አሜሪካዊ በርናርድ ላጋት በተለይ የመጨረሻውን ሩብ ርቀት በፍጥነት በመጨረስ የማይል አሸናፊ ሆኗል። ላጋት ያሽነፈው የኦሎምፒኩን የ 1,500 ሜትር ሻምፒዮን ኬንያዊ አስቤል ኪፕሮፕን ከኋላው በማስቀረት ነው።

Australian Open Serena Williams Tennis
ምስል AP

ቴኒስ፤ አውስትሬሊያን-ኦፕን

በዓለም ላይ ቀደምት ከሆኑት የቴኒስ ውድድሮች አንዱ አውትሬሊያን-ኦፕን ትናንት የስዊሱ ሮጀር ፌደረርና አሜሪካዊቱ ሤሬና ዊሊያምስ በየፊናቸው የነገሱበት ሆኖ አልፏል። ፌደረር ብርቱ ተጋጣሚውን ኤንዲይ መሪይን በማሸነፍ ብሪታኒያ ከ 74 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ለግራንድ-ስላም ድል ለመብቃት የጣለችውን ተሥፋ ከንቱ አድርጎታል። በዓለም ቴኒስ የማዕረግ ተዋረድ ላይ ቀደምቱ ለሆነው ለሮጀር ፌደረር በአንጻሩ የትናንቱ 16ኛው የታላቁ ውድድር ድል መሆኑ ነበር። የአውስትራሊያና የብሪታኒያ ጋዜጦች በየፊናቸው የዘገቡት ለሁለቱ ተወዳዳሪዎች ያላቸውን አድናቆት በመግለጽ ነው።

የአውስትሬሊያው-ኦፕን በሴቶች ደግሞ የሤሬና ዊሊያምስን ልዕልናና የቤልጂጓን የቀድሞ የዓለም አንደኛ አንደኛ የጁስትን ሄኒንን አስደናቂ በሆነ መልክ ተጠናክሮ መመለስ ያረጋገጠ ሆኖ ነው ያለፈው። ሤሬና ዊሊያምስ ሄኒንን በሶሥት ምድብ ጨዋታ 2-1 ስታሸንፍ ሆኖም የቤልጂጓ ኮከብ የቀድሞ ቅልጥፍናና ጥበቧን ጨርሶ እንዳልረሳች አስመስክራለች። በውድድሩ ሂደት ሲያነጋግር የሰነበተ ሌላ አስደናቂ ነገር ቢኖር የቻይና ተጫዋቾች ዕርምጃ ጎልቶ መታየት ነበር። ሁለቱ ተወዳዳሪዎች ሼንግ-ጂና ሊ-ና እስከ ግማሽ ፍጻሜው ለመዝለቅ በቅተዋል። የዓለም ቴኒስ ማሕበር ሃላፊ ስቴሢይ አላስተር ታሪካዊ በማለት ነው የቻይናን ዕርምጃ ያወደሱት። በተረፈ በወንዶች-ጥንድ አሜሪካውያኑ ቦብና ማርክ ብራያን ሲያሸንፉ በሴቶች-ጥንድም እንዲሁ ቬኑስና ሤሬና ዊልያምስ ለድል በቅተዋል።

በተቀረ አውስትሪያ ውስጥ ሲካሄድ የሰነበተው የአውሮፓ የዕጅ ኳስ ሻምፒዮና ውድድር ትናንት በፈረንሣይ አሸናፊነት ተጠቃሏል። የኦሎምፒክና የዓለም ሻምፒዮን የሆነችው ፈረንሣይ ለዚህ ሶሥተኛ ታላቅ ድል የበቃችው ክሮኤሺያን 25-21 በሆነ ውጤት ከረታች በኋላ ነበር። ፈረንሣይ ባለፈው ዓመትም ዛግሬብ ላይ ይህችኑ ተጋጣሚዋን በመርታት የዓለም ሻምፒዮን መሆኗ ይታወሣል። እናም ለክሮኤሺያ የትናንቱ ሽንፈት ሲበዛ መሪር መሆኑ አልቀረም።

MM/DW/RTR/AFP/dpa

Negash Mohammed